2014 ማርች 2, እሑድ

ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁነኛ ሠው ማነው?

ፖለቲካችን እነሆ ዝብርቅርቅ እንዳለ መሬት ሳይነካ፤ እንደተናጠ ምርጫ ደረሰ፡፡ ሁሉም ለእራሱ ግነት ሲፈልግ እነሆ ኢትዮጵያም እንደሀገር እንደቀጠለች አለች፡፡ ነገር በተከወነ ቁጥር ሁሉም ጀብድ ነው ብሎ ያሰበውን ወደእራሱ እንደጎተተ እነሆ ኢትዮጵያም እንደሀገር እንደቀጠለች አለች፡፡ እኛ ነን፤ እኛ ነን እንዳሉ እነርሱ ይሁኑ አይሁኑ ሳይለይ፤ እነሆ ኢትዮጵያም እንደሀገር እንደቀጠለች አለች፡፡ ኢትዮጵያማ ትቀጥላለች አስቀጣይዋ ግን ለማስቀጠል የሚበጅና የሚችል እንዲሆንላት ጥንነቃቄና ብልኸት ያሻው ይሆናል እንጂ፤ ኢትዮጵያማ እንደጉድ ትቀጥላለች፡፡
ለጉድ የፈጠረን እንዳልነው ሁሉ ለጉድ የፈጠራት ሀገር አለችን መሠለኝ፡፡ ስለሆነም ትቀጥላለች፡፡ በይ ኢትዮጵያ ቀጥይ፡፡ በእነዚህ ሁነቶች ሁሉ ታዲያ ፖለቲከኞቻችን ሁነኛ ነን እያሉ ማንነታቸውን ከፍ ከፍ እንድናደርግና እንድናወድስ መንገዱን ለእራሳቸው መጥረጋቸው ይታያል፡፡ በመሠረቱ ለፖለቲካ ተሳትፎና ግልጽነት ትንሽም ቢሆን ቀረት የምንለው ነገር ቢኖርም፡፡ ቀደም ሲል የነበሩት አገዛዞች ግልጽነታችንን እንደዜጋ በተለይም እንደፖለቲከኛ ዜጋ የፈተኑት ይመስለኛል፡፡ ድምጽን ከፍ አድርጎም መናገር ዋጋ ሊያስከፍል ይችል እንደነበር ሲነገር ሰምተናል፤ አንብበንማል፡፡
በዛ ወቅት የነበሩ ፖለቲከኞችም ታዲያ በየወቅቱ በሚጽፉዋቸው መጣጥፎች፣ በሚሰጡዋቸው ቃለ-መጠይቆች፤ ብሎም በሚያሳትሙዋቸው መጻህፍት (አንዳንዶች ኑዛዜ ነው ይሉታል) ማንነታቸውን ለማሰማመር ሲጥሩ ይስተዋላል፡፡ ሁሉም በእነርሱ አገላለጽ መልካም አድርገዋል፡፡ ይህ ከሆነ ታዲያ ችግሩ ከምን ላይ ያርፋል የሚል ጥያቄ ከተነሳ፤ ማሳበቢያ ስለማይጠፋ፤ ስበቡ ሌላኛው ላይ እንዲያርፍ ይደረግና ለተወሰነ ግዜ እረፍት ለመውሰድ ይሞከራል፡፡ በመሠረቱ ግን ሁነኛ ሠው ያጣው ፖለቲካችን ለምን እንዲህ ሊሆን እንደቻለ በርካታ መላምቶች ቢሰጡም፤ በዋነኝነት ፖለቲከኞቻችን እራሳቸው ሁነኛው ሰው ማን እንደሆነ ማሰብ የሚፈቅዱ አይመስለኝም፡፡
ሁሉም ስለሀገር ያነሳሉ፡፡ ሀገር ታዲያ በምን መልኩ ነው የተሻለ መስተጋብር የሚኖራት ለሚለው ጥያቄ መልስ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ቢኖራቸው እመርጣለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በሚል ቃል ሽፋን ውሸት የሚነዙ አይጠፉም፡፡ በርካቶች (ኢትዮጵያ የሚለውን የሚጠቀሙ ፓርቲዎችን ጨምሮ) በብሔር ስም የሚንቀሳቀሱትን ፓርቲዎች ብሔርን ማዕከል ያደረጉ በማለት ለሀገር አንድነት ስጋት አድገው ሲያቀርቡዋች ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን ይህ አመለካከት መቀየር እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ ዜጎች በየትኛውም አግባብ ቢሆን ሊሰባሰቡና ሊደራጁ እንደሚችሉ፤ ብሎም ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል የሚጠቀሙት ፖለቲከኞች ሁሉ እውነተኞችና፤ ብሔርን የሚጠቅሱት የማይጠቅሙ ተደርገው መወሰድ ያለባቸው አይመስለኝም፡፡
ሁነኛውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰው ፍለጋ ላይ ያለን ይመስለኛል፡፡ በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያዊያን በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ይህንን ሰው መፈለግ ላይ መሆናቸውን መገመት አዳጋች አይመስለኛም፡፡ ለዚህም ሊሆን ይችል ይሆናል፤ ፓርቲዎቹ እንዲህ የበረከቱትና በዛው ልክም አባላት (የእውነትም የውሸትም ሊሆን ይችላል) የሚኖራቸው፡፡
ከሰሞኑን ታዲያ የሌንጮ ወደ ሀገር ለመመለስ መወሰን ከባድ ውዝግብ ማስነሳቱን ተከታትያለሁ፡፡ በመሠረቱ ሌንጮ በበርካቶች ተናግሮ የማሳመን ብቃት ያለው እንደሆነ የሚነገርለት፤ ጥሩ የማየት አቅም ያለውና ነገሮች በጥልቀት ለመመርመር ብቁ እንደሆነ የሚመሰከርለት ግለሰብ ቢሆንም፤ አንዳንዶች ደግሞ ቀደም ሲል ከነበረበት የኦነግ አመራርነት ሥልጣን ጋር በተያያዘ ሲኮንኑት ይስተዋላል፡፡ በዚህም አልን በእዛ ሌንጮ መምጣቱ እርግጥ ይመስላል፡፡ አዲሱን ፓርቲውን (የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ወይም በምህጻር ኦዴግ) ይዞ በሀገር ቤት ትግሉን በአዲስ መልክ ለመቀላቀል ያሰበም ይመስላል፡፡
ለዚሁም በርካቶች ሲደሰቱ፤ ሌሎች በርካቶችም ስጋት አድሮባቸዋል፡፡ የተደበላለቀ ስሜት የተሰማቸውም እንዳሉ ይስተዋላል፡፡ ሌንጮ ከቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ጋር (ነገሮች ክርር ብለው መስመር ባልለቀቁበት ዘመን) ጥሩ ግንኙነት እንደነበራቸውም ይወራል፡፡ ዛሬም ላይ ታዲያ ያሉት ጠ/ሚኒሰትር ኃ/ማርያም ጉዳዩን እንደመንግስት እንደሚመረምሩትና ውጤቱም ወደፊት እንደሚታይ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ አሳውቀውናል፡፡
ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አዳጋች ቢሆንም፤ የሌንጮን ወደሀገር ለመመለስ እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት ላየና በዚህም መሀከል እየተስተጋባ ካለው ሁነት ጎን፤ ምናልባት ሌንጮ ዳግም ሁነኛ ሰው ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን› ብዬ ለመጠየቅ ይዳዳኛል፡፡ ለነገሩ ምናልባት ድርድሩ ተሳክቶ ወደሀገርቤት የሚመጣ ከሆነና እንቅስቃሴውን በይፋ ሲጀምር የምናየው ይሆን ይሆናል፡፡
የበርካቶች ግምት እንዳለ ሆኖ፤ ወደፊት የምናየው ስለመሰለኝ ይህንን አልኩ፡፡

ሠላም ሁኑ!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ