2015 ኤፕሪል 8, ረቡዕ

ጋዜጠኝነት፣ ጽንፍና ኢትዮጵያ (ሙያ፣ ወገንተኝነትና ሀገር) ፩

ጋዜጠኝነት፣ ጽንፍና ኢትዮጵያ
(ሙያ፣ ወገንተኝነትና ሀገር)
የህዝብ ልሳንና አንደበት መሆን መታደል ነው፡፡ የህዝብን ብሶትና ምስጋና ለማስተጋባት ያለአንዳች ሀፍረት በእውነት ለእውነት ለማቅረብ መመረጥም እንዲሁ ነው፡፡ ህዝብ ብዙ ያስባል፡፡ ህዝብ ብዙ ይመኛል፡፡ ህዝብ የመበርከቱን ያህል ሀሳቡም እንዲሁ ሊሆን ግድ ነው፡፡ የተለያዩ ሀሳቦች፤ የተለያዩ ምልከታዎች፤ የተለያዩ እውነቶች፤ የተለያዩ ማንነቶችም ጭምር፡፡ በእነዚህ ውስጥ ታዲያ የህዝብ አንደበት የመሆን አደራ የሚጣልበት፤ በተለይም አንደበታቸው ለተያዘ/ለተገታ ብርቱ አንደበት የመሆን ድርሻ የሚጣልበት፤ አደራውን በግብሩ እንዲያሳይ የሚጠበቅበት አንዳች ባለሙያ አለ፤ ጋዜጠኛ፡፡

ጋዜጠኝት ያለውን እውነት ተቀብሎ ለህዝብ መልሶ የማቅረብ፤ ብሎም ህዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች የማስተጋባት፤ አዲስ የተፈጠሩ ክስተቶችን የማሳወቅ እና አድማጭ፣ አንባቢውና ተመልካቹ በሚመለከቱት ጉዳዮች ላይ የበቃ መረጃ እንዲኖረው ለማድረግ የሚከወን ሙያ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ታዲያ የአድማጭ፣ አንበባ ወይም ተመልካቹን ቀልብ ለመግዛትና የእርሱን ሀሳብ እያስተጋባ እንዳለ ለማሳወቅ፤ ጋዜጠኛው ብርቱ ፈተና ይጠብቀዋል፡፡ እንዲህ ባለውም ጊዜም ስህተቶች እንዳይከሰቱ የጋዜጠኝነት መሠረታዊያንን ጠንቅቆ መረዳትና መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ 

እኒህም የጋዜጠኝነት መሠረታዊያውን የተለያዩ ጸሐፍት በተለያየ ቁጥር ቢያስቀምጧቸውም፤ በዋናነት ግን ገለልተኝነትና፣ በእውነት ላይ የተመሰረቱ መሆንን፣ ሚዛናዊነት ወይም ከወገንተኝነት መጽዳትን እና ገለልተኝነትን፣ የተለያዩ ሀሳቦችን ወይንም ምልከታዎችን ማስተናገድን፣ ከህዝብ ጋር መቀራረብን ብሎም ቁርኝት ያለውን ጉዳይ በትኩረት መስራትን በዋናነት ሁሉም ይስማሙባቸዋል ለማለት ይቻላል፡፡

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ ጽሁፎች እንደሚያስረዱት ከሆነ፤ ጋዜጠኞች ኦፊሴላዊ የሆኑትን መረጃዎች እንደወረዱ መቀበል የለባቸውም ብለው ይከራከራሉ፡፡ ጋዜጠኞች የህዝብ አይንና ጆሮ ናቸው፡፡ ስለሆነም ሁሉንም ነገር እንዲጠይቁ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም በስልጣን ላይ ያሉትን፡፡ ምክንያቱም ስልጣናቸውን ለማቆየት/የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ሲሉ ያለውን እውነት እነርሱ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ ዘወር አድርገው ስለሚያቀርቡት፡፡ ስለሆነም ጋዜጠኞች ጠንካራና በሳል ጥያቄዎችን/መጠይቆችን በማቀረብ ሁነቱን ለህዝብ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ጋዜጠኞች ስለሚጠይቁት ጉዳይ መለስተኛ ዳሰሳ በማካሄድ ተጠያቂዎች በፍጹም የማይፈልጉትን አይነት መጠይቆች ማንሳታቸው ይጠበቃል፡፡ ይህ ሁሉ እንዲሆንም የጋዜጠኛው ተገቢ የሚባለውን አስተሳሰብ ተላብሶ፤ ሁለንተናዊ ዝግጁነቱን ጠብቆ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡

ሙያዊ ስነምግባራትን ጠብቆ፤ ከወገንተኝነት በጸዳ መልኩ ሥራዎችን ማከናወን ከየትኛውም ጋዜጠኛ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ጋዜጠኛው ወደደም ጠላም፤ ሁኔታው እርሱን (በግል) ይመልከትም አይመልከትም ነጻ ሆኖ ሁኔታዎችን ለህዝብ፤ የማድረስ ግዴት ይጣልበታል፡፡ ይህንን ግዴታ ነው እንግዲህ በቅጡ መወጣት የሚገባው፡፡ በዚህ መካከል ታዲያ እንቅፋቶች ይጠፋሉ ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከጋዜጠኛውም አቅም በላይ የሆኑ እርሱን በጣም ሊፈትኑ የሚችሉ ነገሮች ሊገጥሙት እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሁኔታዎች በጥንቃቄና የሙያውን ክብር በጠበቀ መልኩ ማለፍ ይጠይቀዋል፡፡

በተለያዩ ሀገሮች ጋዜጠኞች ይዋከባሉ፡፡ ጋዜጠኞች ላይ እንግልት ይደርሳል፡፡ ድብደባውም አይቀርም፡፡ ጥድፊያውም እንደዚያው ነው፡፡ በአንዳንዶች ላይ የሚኖረው እምነት ሠፋ ያለ ነው፡፡ አንዳንዶችም አይታመኑም፡፡ አንዳንዶች በዕውቀት ይሰሩታል፡፡ አንዳንዶችም በድፍረት፡፡ ማይክራፎኑንና አየር ሞገዱን ስላገኙ ብቻ ጋዜጠኛ የሚባሉ፡፡ ብዕርን ከወረቀት አዋደድኩ ብለው፤ አንባቢ ነኝ ብለው ስለሚያስቡ ነገሮችን አጣቅሰው ስለጻፉ ብቻም ጋዜጠኛ የሚል ማዕረግ የተጫነላቸው አሉ፡፡

(ይቀጥላል)

ሚያዚያ 01 ቀን 2007 ዓ.ም.
© አብርሃም ተስፋዬ

2015 ፌብሩዋሪ 27, ዓርብ

ስደት ዕጣ የሆነው ትውልድ

አድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል፡፡ እውነት ነው፡፡ አለም ወደደም ጠላም ያወቀው ድል፡፡ እኩይ ተግባር የተሸነፈበት ድል፡፡ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ክፍላተ አለም ላሉ ጭቁን ህዝቦች እንዲህም ይቻላል ብለው ማሠብ እንዲችሉ ያስቻለ ድል ተጎናጽፈዋል፡፡ ደስ የሚል እውነት፡፡ ደስ የሚል ታሪክ፡፡ የእውነት ኢትዮጵያዊ ድል፡፡ 

ሠሞኑን ብዙሀን መገናኛዎቻችንም እኛም ስለአንድ ነገር ብቻ ማውራት ይዘናል፡፡ የአድዋ ድል፡፡ ግን ሠሞነኞች ነን፡፡ ከአመት አመት ማስተጋባትና መዘከር እየተገባን ሁለትና ሶስት ቀን ብቻ እናወራዋለን፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በርካቶቻችን አድዋ ሲነሣ ኢትዮጵያዊነታችን ደርሶ ይሰማናል፡፡ ደርሰን ወኔያም እንሆናለን፡፡ አድዋ! 

ሰሞኑን የማነባቸው ጽሁፎች ግርም ቢሉኝ ነው ይህችን ልበል ማለቴ፡፡ ወራሪን መመከት የቻለ ኢትዮጵያዊ ስደትን መርጧል፡፡ አድዋ ላይ ድል ያደረገው ኢትዮጵያዊ ባርነትን ሽቷል ነው ያነበብኳቸው ጽሁፎች መንፈስ፡፡ እንደኔ ግን በርካቶች በተለይም ኢትዮጵያውያን ስደትን ለምን መረጡ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው ዋናውና መሠረታዊው ጉዳይ፡፡ ስደትማ እንደሚያንገሸግሽ ስደትማ እረፍት እንደማይሰጥ ለኢትዮጵያዊ ለመንገር መሞከር ለቀባሪው ማርዳት አይነት ይሆናል፡፡ በሀገር መኖር' በሀገር ማጌጥ' በሀገር መስራትና መበልጸግ የማይፈልግ ማን አለ; ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህንን የሚጠላ አይመስለኝም፡፡ 

ሠዎች ነንና ሌሎች ያደረጉትን አይተን ከነሱ ጥሩ የምንለውን ወስደን መተግበር እንፈልጋለን፡፡ ህይወታችን በድህነት የታጠረ ነውና ብዙዎቻችን ቤተሰቦቻችን እኛን ለማሳደግና ለማኖር ብሎም ለማቆየት የከፈሉትን ዋጋ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን (ምንም እንኳ የነርሱን (የቤተሰቦቻችንን ማለቴ ነው) ያህል ባይሆንም) ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ 

ብዙ ጊዜ ደግሞ በአቅራቢያችን ያሉና ከሀገር ውጭ ያሉ ወንድምና እህቶቻችን ናቸው ይህንን ሲያደርጉ የምናየው፡፡ ስለሆነም በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ከሀገር መሠደድ ያስመርጠናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለይ አሁን እንደ ቀበሌ (ወረዳ) ባሉ አገልግሎት መስጫ ተsማት አካባቢና በየመንደሩ ባሉ የገዢው ፓርቲ #ሁነኛ$ ሰዎች ነን ብለው በሚያስቡና የፖለቲካ እውቀት ባሉበትም ያላለፈ በርካታ ሰዎች እየፈጠሩ ያሉት ተጽዕኖም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ለእያንዳንዱ በዜግነታችን ብቻ ማግኘት ለሚገባን አገልግሎት ከብዙ ቢያንስ በአንዱ የቀበሌና የራሳቸው ብቻ ግለሰቦቹ በሚፈጥሯቸው አደረጃጀቶች ውስጥ መታቀፍ #ያልተጻፈ ህግ$ ሆኖ ያገለግላል፡፡ 

ከአድዋ ድል 100 ኛ ዓመት ክብረ በዓል ጋር ተያይዞ ከድሮ ጀምሮ አብሮን የመጣውን ወኔ ቀመስ ሁነት ሁሉም መወርወር ይዟል፡፡ #ጣሊያንን ያባረረ ኢትዮጵያዊ እንዴት አሁን ስደትን ይመርጣል;$ ነው የብዙዎቹ ይዘት፡፡ 

በእርግጥ ኢትዮጵያውያን አድዋ ላይ ድል አድርገዋል፡፡ እውነት ነው ኢትዮጵያውያን አልነካ ብለው ሆ ብለው ለወረራ የመጣውን ጠላት አባረዋል፡፡ ግን ዛሬ ላይም አሁን ያለውን ወጣት ለምን ተሰደድክ ብሎ ከመውቀስ የዘለለ አንዳች ሌላ አማራጭ ማቅረብ አለመቻሉ ያስገርመኛል፡፡ ለምን ብሎ መጠየቅ በሚያስወግዝበት ሁነት& ሀገር ውስጥ መቆየት ምናልባት አያስደስትም ይሆናል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ብዙዎች መሠደድን የሚመርጡት፡፡ 

ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ዜጎች አሁን ያላቸው ብቸኛ አማራጭ የገዢው ፓርቲ አባል መሆን ብቻ እንደሆነ አምነው ወደ ህይወት መድረክ ብቅ ማለት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ህይወት እንኳ ከብዙ በጥቂቱ በፓርቲ ሥራ የሚጠመዱ ወጣቶች በርካቶች መሆናቸውን ይናገራል፡፡ እያየንም ነው፡፡ አሁን አሁንማ የቅጥር ማስታወቂያዎች እንኳ ከዕውቀት በዘለለ ከትምህርት ማስረጃ ይልቅ የቀበሌ የድጋፍ ደብዳቤ ይመርጡ ይዟል፡፡ 

ሀገሬ በእኔ ላይ ብዙ ኃብት (Resource) አፍስሳለች፡፡ እኔ ደግሞ ተምሬ ላገለግላት ካልቻልኩ እኔ ብቻ ሳልሆን ሀገሬም ባክናለች ማለት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ አሁን አሁን በዜጎች ላይ የምናየው በራስ መተማመን ማጣት በነጻነት የፈለግነውንና ያሰብነውን እንዳንከውን ያደርገናል፡፡ 

ስደትን ባላበረታታም የሚሠደዱ ዜጎችን እንደሀገር ከዳተኛ መቁጠር ግን አልደፍርም፡፡ አልደግፍምም፡፡ በትምህርት ቤቶችም ቢሆን መምህራን ጊዜያቸውን በቀበሌዎች እንደሚያሳልፉ ይስተዋላል፡፡ በጊዜው ያላስተማሯቸው ልጆች ቤት ገብተው ግራ ሲጋቡ ማየት የተለመደ ነው፡፡ የትምህርት ጥራት ከምን ይጀምራል; የሚለውን በሌላ ጊዜ ብመለስበት ይሻላል፡፡ 

ግን እኔ መምህራን በየትኛውም የትምህርት መስክ ሊሆን ይችላል (አለማዊውንም መንፈሳዊውንም) የእውነት አባቶች እንዲሆኑ እሻለሁ፡፡ መሻት ብቻ አይደለም አምናለሁም፡፡ በራሱ የሚተማመን ሀገሩን የሚወድና ጠንካራ ትውልድ መፍጠር የሚችል& በቅቶ የሚያበቃ - መምህር፡፡ 

አሁን ግን እየሆነ ያለው የተለየ ይመስለኛል፡፡ መምህራኑ በሌላ ሥራ ከተጠመዱ እንዴት ነው; የትምህርትስ ጉዳይ; ስደት የመምረጣችን አንዱ ምክንያት ምናልባትም ተስፋ ማጣት ሊሆን የሚችለው ለዚህ ይሆናል፡፡ 

መምህራን ብቁ ዜጋ ከመፍጠር ይልቅ አማራጮችን ከማቅረብ ይልቅ ብቸኛ መንገድ የሚሉትን መስመር ማሣየት መጀመራቸው ተማሪዎቻቸው በተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎች ከሚያገኙት መረጃ ጋር በማነጻጸር ውጭን አስመርጦም ይሆናል፡፡ ለነገሩ አካላችን እንጂ መንፈሳችን ከሸፈተ ሰንበትበት ብLDል፡፡ የምናገኘው መረጃ እንኳ የውጭውን ካልሆነ ለብዙሃን መገናኛዎቻችንም ቢሆን ጆሮም አይንም ከልክለናቸዋል፡፡ 

ልባዊ የሀገር ፍቅር ስሜት በሁላችንም ዘንድ ቢኖር ይመረጣል፡፡ ካልሆነ ትውልድ ይኮላሻል፡፡ በርካታ ጀግኖች ነበሯት ኢትዮጵያ፡፡ ጅግንነቱ የት ገባ; ምላሹን እንግዲህ ለሁላችንም በየራሳችን እንየው፡፡ ግን ከላይ የጠቀስኳቸው ነገሮች ሳስብ እንደው ጠቅለል ለማድረግ በራስ መተማመን ማጣትና ፍርሃት ይመስሉኛል ለስደታችን ዋነኛ ምክንያቶች፡፡ 

ፈሪ ትውልድ ደግሞ ለማንም አይበጅም፡፡ የፈሪ ትውልድ ታላቅ ግብር ፈርቶ ማስፈራራት ብቻ ነው፡፡ እናት ጀግና ትውለድ፡፡ ለዛውም ኢትዮጵያ፡፡ ለዛውም ኢትዮጵያዊ እናት ከጀግናም ጀግና መውለድ ትችልበታለች፡፡ 

በርካቶች ብንመኝም ጥቂቶች ባለው ስለተደሰቱ ቢመርጡትም እንኳ፡፡ ሀገር ለሀሉም እኩል ናት፡፡ ይህንን ከጽንሰ ሀሳብ በዘለለ በተግባር ማየት የሁላችንም ምኞትና ፍላጎት መሆን አለበት፡፡ ስደተኛ ትውልድ እያሉ መውቀስ ትርጉም የለውም፡፡ ቅኝ አልተገዛንም ብሎ ማውራት ትርጉም የለውም፡፡ አሁን አሁን በእጅ አዙር ቅኝ ስላለመገዛታችን ማሣያ እየጠፋ ነው፡፡ ስለስደት ሲነሣ መሠደድን ከመውቀስና ከማብጠልጠል የዘለለ ለምን ስደት እንደብቸኛ አማራጭ ተወሰደ ብለን ለመፍትሔው ብንረባረብ ሳይሻል እንደማይቀር ይሠማኛል፡፡ 

ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ተገቢውን ክብርና ነጻነት ማግኘት ይፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ በሀገሩ መሸማቀቅ የሚፈልግ የለም፡፡ ሀገራችን ከማንም በላይ ተከብረን የምንኖርባትና የምንኖርላት ብትሆን ይመረጣል፡፡ ለነጻነታችን ከሀገራችን በላይ ማንንም አንመርጥም፡፡ ሀገራችን ከማንም በላይ በየኛነት ስሜት የምንኖርባት ብትሆን መልካም ነው፡፡ ለእኔ ከተመቸኝ ምን ገዶኝ የሚል ስግብግብነት የፈሪ ትውልድ መለያ ነው፡፡ 

ከፈሪ ትውልድ ይሰውረን፡፡ ለምን ብሎ የሚጠይቅ ትውልድ ያስፈልጋታል ኢትዮጵያ፡፡ የሚያየውን ያልተገባ አካሄድ የሚቃወም አማራጮችን የሚያመላክት ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚያስብ ትውልድ ያሻታል፡፡ ካልሆነ አደጋው የከፋ ነው፡፡ ዛሬን እንጂ ነገን የማያስብ ትውልድ የሚያጋጥመውን ላለማወቅ የሚፈልግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከፍርሃት የመነጨ ነው፡፡ ምክንያቱም በጥቂቱም ቢሆን ሲያስብ የሚያጋጥመውን አዘቅት ያውቀዋል፡፡ ከዚህ ፍርሃትና ጭንቀት ለመውጣት እንደብቸኛ መፍትሔ የተያያዝነው ደግሞ ስደትን ነው፡፡ 

እርግጥ ነው ሀገር ሀገር ለሚል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የስደት ጉዳይ አንገብጋቢ ነው፡፡ ሀገር ላይ አለመከበር ያሳምማል፡፡ ክብርና ኩራት ብለን የምንፎክርበት ኢትዮጵያዊነት በፍርሃትና ልፍስፍስነት ተተክቷል፡፡ ስደትን መፍትሔ ማድረግ ይዘናል፡፡ መወቃቀስ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ለምን ብለን መጠየቁ ነው የተሻለው፡፡ ሲደረግ እያየን ስላልተደረገልን ለምን ብለን ብንጠይቅ ቁጣ አያሻውም፡፡ 

ስደትን እያበረታታሁ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን ያለኛ ማሠብ አይደለም ለማሠብ መሞከር በራሱ ሀጢያት ይሆንብኛል፡፡ ግን የምናያቸው ነገሮች ያስገደዱንም ይመስለኛል፡፡ ለነገሮች ብቃት ኖሮን አለመመረጣችን ያሳምመኛል፡፡ መገፋት ማንንም አያስደስትም፡፡ እንሰደድ ባልልም ቢያንስ ለውድድር ብንቀርብና በአንድ አይነት የውድድር መስፈርት ብንመዘን መልካም መሆኑን ሳልገልጽ አላልፍም፡፡ ማንም መድሎ ሲደረግብት እያየ መቀመጥ አይፈልግም፡፡ ለዚህም ስደትን ያስመርጠዋል፡፡ 

የኤርትራው ፕሬዜዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ አንድ ጊዜ ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የሰጡትን መልስ አስታወስኩ፡፡ ዜጎች ከኤርትራ በየቀኑ ወደ ጎረቤት ሀገሮች ይሠደዳሉ፡፡ ሀገርዎን የወከሉ ስፖርተኞች እንኳ በሄዱበት ቀርተዋል ለምንድነው; ብላ ጠየቀች ጋዜጠኛዋ፡፡ ፕሬዜዳንት ኢሣያስ ተገረሙ፡፡ ይሄ ለእኔ አዲስ ነው ብለው መለሱ፡፡ ለነገሩ ማንም ሠው የተሻለ ነገር ፍለጋ የትም ቢሄድ እንደማይገረሙ አከሉበት፡፡ 

© አብርሃም ተስፋዬ  
This article was publish in "Awramba Times" newspaper on March 12, 2011.

2015 ፌብሩዋሪ 4, ረቡዕ

“ወደራቁት ሴቶች ምዕራፍ 8000 ÷…”


"እኛም አለን ሙዚቃ"

 “እናንት በዚያ ያላችሁ ሆይ! እነሆ እርቃናችሁን ትሆኑ ዘንድ የተፈቀደ፤ ወንድሞቻችሁንም በወሲብ ፍላጎት ትፈትኑ ዘንድ የተወደደ ቢሆን ጊዜ ይኸው እርቃን መሆናችሁ ተፈቀደ’’ የተባለበት ቦታ ያለ መሰለኝ፡፡ ከዚህ ከአዲስ አበባ አንዳች ነገር ገብቶ ይሆናል፡፡ እርቃን መሆን ሳይፈቀድ አልቀረም፡፡ ግን ስለምን እንዲህ እንዲሆን እንደተፈረደ/እንደተፈቀደ አላውቅም፡፡
ከቅርብ ወዳጄ ጋር ጫማችንን ለማስጠረግ ከአንድ ካፍቴሪያ በር ላይ ቁጭ ብለናል፡፡ ከእኛ በስተግራ አቅጣጫ ሁለት ሴቶች ይመጣሉ፡፡ ለአቀማመጣችን ከታች ወደ ላይ አይነት ጉዞ ነው፡፡ ሁለቱም በጣም ያጠሩ ቀሚስ መሰል ጨርቆችን በላያቸው ጣል አድርገዋል፡፡ ብጣሽ ጨርቅ ነገር ልበልው ይሆን?

እንደ"ሽሮፕ"….
እያወሩ ነው፡፡ ምን እንደሚያወሩ በግልጽ አይሰማም፡፡ ስለሆነም እርሱን መገመት ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን እንቅስቃሴያቸው ጤነኝነት ካለው አላውቅም፡፡ በተለይ አንደኛዋ ትውረገረጋለች፡፡ እየሄዱም ይደነሳል፡፡ በመንገድም ለካ ውዝዋዜ አለ፡፡ ንቅናቄዋ መስመር ያለፈ አይነት ነው፡፡ ይህ ዘመንኛው የእነእንቶኔ <ድመታዊ> አካሄድ ከሆነ ብዬም አሰብኩ፡፡ (ሞዴል ምናምን ነን የሚሉት ወ……. ያመጡብንን ነገር እያሰብኩ ነው፡፡ በቅርቡ እንደውም በብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ የተመለክቱት ነገር ትውስ አለኝ፡፡ ወደታች እመለስበታለሁ፡፡) ነገር ግን ከእርሱም ለየት ይላል፡፡ ይህንን ስል በእርግጥም በእዚህች ሴት ላይ ብቻ አይቸው አይደለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተመለከትን ያለውን ሰውነትን እንደ አዲስ ሽሮብ የመበጥበጥ አካሄድ በሴቶቻችን ዘንድ እንደልማድ እየተወሰደ ያለና በጣም በብርቱ እየተከተሉት ያለ ነገር ስለሆነብኝ ነው፡፡ በእርግጥ ከበርካቶችም ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ሳወራ እንዳስተዋሉት ለመረዳት ችያለሁ፡፡ በጉዞዋ ላይ……… ግን እንደው ልክ የምትቀመጥበት አልያም ሌላ ማረፊያ ስታገኝ እንዴት ልትቀመጥ እንደምትችል አሰብኩት፡፡ አንዳንድ ጊዜም ምናልባትም አንዳንዶች ከካፊቴሪያዎች ቶሎ የማይወጡት እንዲህ ባለው አካሄድ የተነሳ ድካም ገብተው፤ እረፍት ከመሻት የመነጫ ይሆን? እየሄዱም መንቀጥቀጥ.....

ለወላጅ ማፈሪያ

አፍታም አልቆየም ሌላ ደግሞ ትዕይንት፡፡ እምብረትና ጡት መለየት የተሳናት አይነት አንዲት ራቁት ደግሞ መጣች፡፡ ራቁት ነው፡፡ ምንም ልብስ የለም፡፡ ከወገብ በላይ አንዲት ቢጢል ያለች የሆነች ነገር ብቻ ጣል አድርጋለች፡፡ በጣም ገራሚ አይነት ነው፡፡ ወዳጆችዋ አብረዋት አሉ፡፡ አይ ዘመናዊ ወዳጅ! እንዲህ ያለውንም ለማረቅ ጊዜ የሌለው አይነት፡፡ የሚያስጠላውን ለመንገር የማይደፍር፡፡ የማይመርጥም፡፡ብኩን ወዳጅ፡፡ እርቃነ ስጋዋን በአሸናፊነት መንፈስ (መንፈስም ቆሌም ሞራልም ያላት አይመስለኝም) ትንቀሳቀሳለች፡፡ በእርሳ ውስጥ ደግሞ ያለው የራስ ክህድት ከባድ ነው፡፡ (ራስን መካድ ማለቴ በእምነት ቢሆን የሚወደደውን አይደለም፡፡ ራስን አለመሆንን ለመግለጽ እንጂ)፡፡ በራስ መተማመን እንዳልለው እርቃን መታየት……ስልጣኔ እንዳልለው ልብስ እያለ አለመልበስ……. ማወቅ እንዳልለው ብርዱም…….አለማወቅም እንዳይሆን ሌሎች አብረው አሉ……. ግራ ነው፡፡ በዚህም ቅጽበት አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች የሚሉት ነገር ትውስ አለኝ፡፡ አሰዳቢ፡፡

ወዳጅማ ቢኖር እንዲህ ባለው እብደት ውስጥ ባንገኝ፡፡ እራስንም ትቶ ሌሎችን ስለሚሆነው በእርግጥም ትክክለኛውን መንገር፤ መምከርና መገሰጽ ያስፈፈልግ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል አልሆነም፡፡

"ትዳር ማለት"

በአንድ ወቅት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ፤ የስነ ጾታና ተዋልዶ ስልጠና ይሰጣቸው ተብሎ ከምንማርበት ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ኮሌጅ ተገኝተናል፡፡ ሥልጠናውን የሚሰጡን ዶክተር ሴት ናቸው፡፡ (አሁን ለጊዜው ስማቸውን አላስታውሰውም):: “ትዳር ማለት ምን ማለት ነው?” ብለው ጠየቁ፡፡ “ትዳር ማለት ክቡር ነው፡፡……… ትልቅ የሆነውን ሀገር ለመመስረት የምንጀምረው እዚህ ነው፡፡ …………” እና ሌሎችም ሰፋ ያሉ ሀሳቦች ተንሸራሸሩ፡፡ ተማሪዎች ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ዶክተር ምላሹን ይመዘግባሉ፡፡ ትዕይንቱ ቀጠለ፡፡ በመጨረሻም ሀሳቦችን ሰብስበው ሲጨርሱ፡፡ “ያላችሁት ሁሉ እውነት ነው” አሉ ዶክተር፡፡ “ግን ቀለል ባለ ሁኔታ እወቁልን፤ ወሲብ በእኔና በእርሱ/በእርሳ መካከል መሆኑ አይግረማችሁ፡፡ አርግዛም ብታይዋት አትደነቁ ማለት ነው፡፡ ማሳወቂያ ነገር፡፡ እውቅናን የመሻት ጉዳይ ነው፡፡” ብለው መለሱልን፡፡ ይህ እንግዲህ በወቅቱ በነበረው ስልጠና የተሰጠው ትርጉም ነው፡፡

መሠረታዊው እውነት ታዲያ እውቅናውን ማህበረሰው ይሰጣል ማለት ነው፡፡ ይህ ማህበረሰብ የሚሰጠውን እውቅና ግን ማዋረድ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ማርገዝ ከትክክለኛው ሰው ከሆነ ክብር ነው፡፡ የትውልድን ቀጣይነት የምናረጋግጥበት ጸጋ፡፡ ለብቻ በሚሆን የተዘጋጀ፡፡ የተሰናዳ፡፡ ክብርን የሚሻ፡፡ የሚገባውም ሁሉ ነው፡፡ መጸነስ፡፡ ይህንን ጸጋ ማዋረድና ማራከስ ግን የአንዳንድ ሴቶች ግብር ከሆነ ሰነባበተ፡፡ በተለይ በተለይ……. እነ እከሌ፡፡ ራቁት ለመሄድ በጣም በቀረበ አለባበስ እርግዝናቸውን ቆሌ አሳጥተው ክብረቢስ ያደረጉ ሴቶች በከተማው አሉ፡፡ ፋሽን ነው በሚል ይሁን አልያም በሌላ እንዲህ ያለውን ዋልጌነት መከተል ጤንነት አይመስለኝም፡፡

በአንድ አጋጣሚ በተወሰኑ አመታት በፊት ያገጠመንን ጉዳይ ላጫውታችሁ፡፡ አዲስ አበባ፡፡ አንዲት ወዳጃችን አርግዛለች፡፡ እናም የማታ ትምህርት ትከታተል ነበርና አንዳች ሰፋ ያለ ለእርጉዝ ሴቶች የሚሆን ልብስ ብቻ ለብሳ ወደ ትምህር ቤት ትመጣለች፡፡ ከላይ የሚለበሰውንና ሱሪውን ለብሳ ደብተር ይዛ፤ በመንገዱ ሰከም ሰከም እያለች ሳለ፤ “ውይ!” አንዲት ሴት ቁጣና እልህ በተቀላቀለበት ሁኔታ ይገላምጡዋታል፡፡ ደነገጠች፡፡ “ምነው እንዲህ ክብር አሳጣችሁት?” ሴትየዋ ጠየቁ፡፡ “ምናለ እንደው ትንሽ ሻርፕ ብትደርቢ፤ በይ እንኪ ይህንን ሻርፕ” ሴትየዋ ሻፓቸውን አወለቁ፡፡ “ቀልብ የላችሁ መቼም፡፡ ሸፈን ይደረጋል፡፡ ነውር ነው፡፡” ብስጭት ብለው ሄዱ፡፡ ሁሌም የሴትየዋ ነገር ይገርመኛል፡፡ ምናልባት እንደሌላው ሰው ዝም ብለው ተገርመው፤ በውስጣቸው ተሳድበው ማለፍ ባለመፈለጋቸው ይሆናል፡፡ እናትነታቸው ላቀብኝ፡፡ ሁሌም አስባቸዋለሁ፡፡ በተለይ እንዲህ ያለውን ነገር ሳይ፡፡ ዛሬ ደግሞ ያሉትን እርጉዞች ሲያዩ (በተለይ አንዳንዶቹን) ምን ይሉ ይሆን/ነበር?
እማማ እኔ ደግሞ በተለይ ባለፈው ያዩሁዋትን አልነግርዎትም፡፡

የእርግዝና መቅለል

እርግዝና የምን ውጤት እንደሆነ መደስኮር ቁብ አይሰጥም፡፡ በየትኛውም አግባብ እንካ ቢሆን፤ በልጅነታችን ጀምሮ ስለነገሩ እንዲህ ነው ተብሎ ማውራት ስለማይቻል ቃላት ተመርጠውለት ይጠራል፡፡ በጣም በርክቶ የሚሰማው ግን የባለጌ ነገር የሚለው ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያዊያን አተያይ ነው፡፡ እኛም ብንሆን የዚህ ማህበረሰብ ውልድ በመሆናችን፤ ወሲብ ለእኛ የብልግና/የባለጌ ነገር ነው ማለት ነው፡፡ ይህንን የባለጌ ነገር ደግሞ ማንም አያበረታታውም፡፡ ስለሆነም በግልጽ የሚፈጸም ሆኖ አይታይም፡፡ ነውርም ነው፡፡ ስልጣኔው እዛ እስኪያደርሰው ድረስ፡፡ (ይህንን ስል ታዲያ አንዳንድ ስነምግባር የጎደላቸው ነውርን አያደርጉም ማለቴ አይደለም፡)

ይቀጥላል፡፡

ተጻፈ ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ሌሊት 8፡00 ሠዓት

© አብርሃም ተስፋዬ