2017 ሴፕቴምበር 8, ዓርብ

‹‹አለህ’ኮ ይሉኛል፤ እውነት አለሁኝ ወይ?›› - ኢትዮጵያዊነት




ወዳጅ በፍቃዱ ኃይሉ ‹‹ኢትዮጵያ ያለ‹ኢትዮጵያዊነት› ልትኖር አትችልም?›› በሚል ርዕስ ለአዲስ አመት መወያያ ጽሁፍ አቅርቦ አነበብኩ፡፡ እነሆ ምልከታዬን ላሰፍር ወደድኩ፡፡
 
ዘመኑ የመሞካሸት ነው፡፡ ኢትዮጵያም ወግ ደርሷት ትሞካሽ ይዛለች፡፡ ወዳጄ በፍቃዱ ኃይሉ አንዳንዱን ጠቅሷል፡፡ እኔ ደግሞ ሰሞንኛውን የ‹ከፍታ› ዘመን ትንቢቷን እጠቅሳለሁ፡፡ ‹ለዘለአለም ትኑር› ‹ይባርካት›ም እየተባለች ያለችውን ኢትዮጵያ፤ አሁን ደግሞ ወደ‹ከፍታ›ው ለመመለስ ጥረት ላይ ያለው ብዙ ነው፡፡
ሀገርኛውን ጉዳይ በብርቱ ማንሳት ተገቢ ነውና እነሆ እኔም ወዳጄ ባነሳው ጉዳይ ላይ የእኔን ምልከታ ለማንሳት ወደድኩ፡፡ በፍቃዱ በአዲስ አመት እንድንወያይበት ያነሳው ጉዳይ መልካም መስሎ ታይቶኛልና ነው ይህንን ማለቴ፡፡
 
ኢትዮጵያ መቼም ከዘመን የናኘ፣ የገዘፈና የበረከተ አመት ታሪክ እንዳላት ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡ በርካቶችም በዚሁ ይስማማሉ፡፡ አንዳንዶች በእርግጥ ይህንን የዕድሜዋን ነገር እንደሚጠራጠሩ ቢታወቅም ማለት ነው፡፡ በአንድ ወቅት በዚሁ ጉዳይ ላይ ሀሳብ ሰንዝሬ ነበርና አልመለስበትም፡፡
 
ኢትዮጵያ እንደሀገር ከተመሠረተችበት ወቅት ጊዜ አንስቶ በርካታ ጊዜያትን አሳልፋለች፡፡ በተለይ ደግሞ አሁን አሁን የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ እያነጋገረ መምጣቱ፤ በጉዳዩ ላይ ጥርት ያለ እውነት ይዞ መውጣት እንደሚያሻ አመላካች ነው፡፡ 
 
በዚህም ረገድ ኢትዮጵያን አንድ ብቻ ሆና የማየት ምኞት ያላቸውና የለም ብሔራችን ቀዳሚውን ድርሻ መያዝ አለበት ብለው የሚያስቡ ልሂቃንና ሌሎችም ተነስተው በተለይም በቅርብ ጊዜ የመነጋገሪያ አጀንዳ አድርገውት መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
 
በመሠረቱ ፖለቲካችን የብሔር እንዲሆን ለምን ሆነ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የብሔር ፖለቲካው እንዴት እንዲህ ሊይብብ ቻለ? ማለትም ተገቢ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ታዲያ በደፈናው ጉዳት አለው ብቻ ብሎ መደምደምስ ተገቢ ነው ወይ? እንዲህ በርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በሚኖሩባት ሀገር፤ የብሔርን ጉዳይ አንስቶ መነጋገር ለሀገር አንድነት አስጊ ነው ብሎ መደምደም በእራሱ የተዳፈነው እንደተዳፈነ ይቆይ፤ አትነካኩ ማለት አይመስልም ወይ? በተለይም አሁን ባለው ሁኔታ በደንብ ልንነጋገርበት ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደአንዳንዶች በደፈናው ሰው መሆንህን ብቻ አስቀድም ብሎ መመጻደቅም ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ደግሞ ከኢትዮጵያዊያን ወዲያ ህያው ምስክር የለም፡፡ አንድ እንሁን ባለ አንደበታቸው የስንቱን ብሔር እያወጡ ሲናገሩ፣ የስንቱንም ጓዳ ጎድጓዳ ሲማስኑ እንደሰነበቱ ለመመልከት ችለናል፡፡
 
ብሔርን ማዕከል ያደረገው አስተሳሰብ ለምን እንዲህ ሊነሳ ቻለ? ከተባለ ዋነኛ ምክንያቱ ጭቆና ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተገቢው አኳኸን ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለተወሰኑት ብሔሮች ብቻ የተመቸች መሆን አለባት ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ እርሱም በእራሱ አደገኛ ነው፡፡ ምቾት ከተባለ ለሁሉም ነው መሆን ያለበት፡፡ በአንደኛው መገፋት ሌላኛው እንዲመቸው መታሰብም የለበትም፡፡ ይህ ግን ታዲያ ብሔርን ለምን ትጠቅሳላችሁ ኢትዮጵያዊነትን ብቻ በደፈናው አራምዱ አይነት ዲስኩር እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡
 
ኢትዮጵያ የሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች መኖሪያ ናት፡፡ ይህች ሀገር ታዲያ ሀገርነቷ ለሁሉም እስከሆነ ድረስ፤ ሁሉም ብሔሮች እምነታቸው፣ ባህላቸው፣ አኗኗራቸው፣ በአጠቃላይ ማንነታቸው ሁሉ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ውስጥ አብሮ መነሳት መቻል አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ‹ኢትዮጵያዊነት› ከንግግር አልፎ ተግባራዊነቱ ጽንፍ ካስያዘ መልካም አይደለም፡፡ በምንናገረው ልክ ተግባራችን መከወን አለበት፡፡ ይህ ደግሞ ግድ ነው፡፡ 
 
አንዳንዶች የብሔር ጉዳይ መነሳቱ ልዩነቶች እየሰፉ መጥተው ኢትዮጵያ የሚለውን ትልቁን የአንድነት ጥላ እንደሚያፈርስና የአገሪቱ ህልውና በክልልና በብሔር ማንነቶች ላይ የተንጠለጠለ እንዲሆን ያደርገዋል ይላል፡፡ እዚህ ላይ ታዲያ ይህችን ሀገር የሰሯት እነማን ናቸው? ሀገሪቱስ ብትሆን የብሔሮቹ ውህድ ውጤት አይደለችም ወይ? አሁንም ቢሆን፤ ማንኛውም ሀገራዊ ነገር ሲከወን ሁሉንም ባማከለና ለሁሉም ብሔሮች ሁለንተናዊ ጥቅም መሆን የለበትም ወይ? በዚህ አግባብስ አሁን ላይ የሚነሱት ብሔርን ያማከሉ እውነቶች ተገቢ አይደሉም ወይ? ነገሮችስ እውነት እንዲሁ እየተዳፈኑ፤ ኢትዮጵያዊነትና አንድነት በሚል የሁሉንም ልብ ሊረታ በሚች ቃል ብቻ እውነቶች ታጭቀው ሳይወጡ መቅረት አለባቸው?
 
ይህ መሆን እንደሌለበት ይሰማኛል፡፡ አንድነት መልካም ቢሆንም፤ ኢትዮጵያዊነት ጥሩ ቢሆንም፤ ከቃል በዘለለ በእውነት ላይ የተመረኮዘ ማንነት ጉዳይ ሲነሳ ታሪክ አታጣቅሱ እንደሚሉት ግለሰቦች መታሰብ የለበትም፡፡
ዛሬ ላይ የምናወራላት ኢትዮጵያ በበርካታ ዜጎች አጥንትና ደም የተገነባች ሀገር ናት፡፡ ይህች ሀገር ታዲያ ሀገር ሆና ለዛሬ እንድትበቃ ዋጋ የከፈሉት አካላት በሙሉ እኩል ሊወደሱ ይገባል፡፡ በሀገር አንድነት ስም ዘር እስከማጥፋት የደረሱት ደግሞ ሊኮነኑ ግድ ነው፡፡ አትንኩብኝ፤ አትንኩብን ተብሎ አይቻልም፡፡ በየትኛውም አጋጣሚ ቢሆን የኢትዮጵያን አንድነት በተሻለ አግባብ መፍጠር የሚቻለው እውነትን እየሸሹ ሳይሆን እየተጋፈጡ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አለሙ ዛሬ ሌላ ነው፡፡
 
በመሠረቱ የብሔር ጥያቄ የማንነት ጥያቄ ተደርጎ መነሳቱ በርካቶችን አስከፍቶ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ብሔርን በትክክል ከፍ ባለ ድምጽ መናገር አዳጋችና አስነዋሪ በሚመስልበት ዘመን ያለፍን እኛ ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይም ብሔርን ለመናገር ከተወሰኑ ብሔር ተወላጆች በቀር ሌላው እንደሌላ ነገር ይታይበት በነበረባት ይህችው ኢትዮጵያ፤ በሀይማኖት፣ በባህልና በኢኮኖሚ የሚጨቆኑ ብሔሮች በነበሩባት ኢትዮጵያ ላይ ሆነን ‹እንደምን ዛሬ ላይ ተነስታችሁ በይፋ ማንነታችሁን ተናገራችሁ?› አይነት ነገር ተገቢ አይሆንም፡፡ በዚህ አግባብም የምትሄድ ኢትዮጵያን ባናስባት የተሻለ ይመስለኛል፡፡
 
በእውኑ፤ ሀገር ማለት ከባድ ትርጉም እንዳለው ማንም መረዳት ያቅተዋል የሚል ምልከታ የለኝም፡፡ ሀገር ደግሞ የማንነት ምሳሌ ስትሆን የእኔንም ባህል፣ ታሪክና ምሉዕነቴን ተቀብላ በእርሷ እንደምወከል ልታሳየኝ ግድ ነው፡፡ ዜግነትን ከማንነት ከቀላቀልነው ችግር የሚሆነው ለዚሁ ነው፡፡ ገጣሚው እንዳለው ‹ሀገር ማለት ረቂቅ ነው ቃሉ›፤ ማንነትም ታዲያ የደምና የአጥንት ዋጋ የተከፈለበት ውስብስብ መሠረት ያለው አንዳች እምቅ የራስ መገለጫ ነው፡፡

ማንነታቸውን በግልጽ የተናገሩና በማንነታቸው ላይ ሀሳባቸውን ያስተጋቡ ግለሰቦች ልዩነትን ለማስፋት እንደሚንቀሳቀሱ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ይህ ደግሞ መልካም አይደለም፡፡ በተጨማሪም ለአንድነት ጸሮች እንደሆኑና ይህንኑ በመናድ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ እንደሚሞክሩ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ 
 
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በተለይም ‹የአንድነት ሀይሎች/አቀንቃኞች› ነን የሚሉት ግለሰቦችና ቡድኖች ብሔርን የተመለከተ ጉዳይ የሚያነሱ ግለሰቦችና ቡድኖች በሙሉ በአንድ ድምጽ ‹ዘረኞች› ተብለው ሲወቀሱና ሲዘለፉ ይታያል፡፡ በእኔ አመለካከት የኢትዮጵያን አንድነት ከመሻት አልያም ከሌላ መንፈስ በመነሳት ብቻ የብሔርን ጉዳይ አንስቶ መናገር ዘረኛ ሊያስብ አይችልም፡፡
 
በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ አይሎ ይሆናል፡፡ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔር የተደራጁ ሆነው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የታሪክ ነገር ሲነሳ ብሔሮች የሚያነሷቸውን እውነቶች በጥቅሉ እየተቃወሙ ስለአንድነት ብቻ እንዘምር መባባሉ ከባድ ይሆናል፡፡
 
ኢትዮጵያን በተመለከተ ከእኛ ወዲያ፣ አንድነት ከምንለው ሰዎች ባሻገር ……. የሚሉትም ቢሆኑ እርሱን ትቶ፤ በእኔ እምነት ኢትዮጵያዊነትን ሳይሆን እራሷን ኢትዮጵያን ብናስቀድም እመርጣለሁ፡፡ ያኔ በመከባበር መንፈስ ስለሀገር ማቀንቀን እንጀምራለን፡፡ ሜዳው እኩል እንዲሆን ባልፈቀድነው ልክ ግን ለመነጋገር ጉዳዩን አሁንም ማለባበስ ይሆንብናል፡፡ በእራሳችን ስጋት ውስጥ ታጭቀን ሌሎችን ለማዳመጥ አለመውደድ ግን ሊታሰብበት ግድ የሚል መሰለኝ፡፡ ስለመሰለኝም ሀሳቤን ለማካፈል ወደድኩ፡፡ ኢትዮጵያን አስቀድሜያለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነቱማ የለም፡፡ ገና ብዙ ልንለፋበት ያስፈልገናል፡፡ በእኛነታችን ላይ መስማማት ያስፈልገናል፡፡ ስለሆነም፤ ‹‹አለህ’ኮ ይሉኛል፤ እውነት አለሁኝ ወይ?›› - ኢትዮጵያዊነት
 
ቸር ያቆየን!
 
አብርሃም ተስፋዬ