2018 ዲሴምበር 8, ቅዳሜ

‹‹በቆረጥከው ዱላ….፣ በመረጥከው ዳኛ....››

ሀገራችን እስካሁን በመጣችባቸው ሂደቶች በርካታ ውጣ ውረዶችን ማስተናገዷ እሙን ነው፡፡ በእነዚህ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህልና ወግ ብሎም የተጻፈም ይሁን ያልተጻፈ ‹ህግ› በወቅቱ በነበሩ መሪዎች ወይንም ገዢዎች እየተሰናዱ አንድም ለእነዚሁ ግለሰቦችና ስርዓታቸው ማቆያ የተሰናዱ፤ አንዳንድ ጊዜም የህዝቡን ስነልቦና ባህልና ወግ ብሎም እምነት የተከተሉ፤ በሌላ ጊዜም ደግሞ ከህዝቡ ስነልቦናና እምነት ወግና ልማድ በወጡ አኳኸን ያሰናዷቸው ቢመስሉም፤ የህዝቡን በአንድ አቅጣጫ (ካለው የራሱ እምነትና ህሊናዊ ፍርድ ባሻገር) ለመምራት አልያም ለመግዛት ሲጠቀሙባቸው እንደነበር ታሪክ ያወሳል፡፡

ሰው የማክበርን ባህል ኢትዮጵያዊ (በሌሎች ሀገሮች የለም እያልኩ እንዳልሆነ ልብ ይሏል) በመሆን ብቻ የወረስነው፤ ሲወርድ ሲዋርድ የመጣ ልማድና ሰው የመሆን እውነተኛ ማሳያ ከመሆኑም በላይ ከዕምነትም አንጻር ሲስተዋል ከፈጣሪ ትዕዛዛት መካከል አንዱ ነውና በሀገሬ በርከት ያሉ ሰዎች ሰውን በማክበር ሲያምኑ ለማስተዋል ቀላል ሆኖ ይታያል፡፡ በየትኛውም የእምነት አስተምርሆዎችም ይኸው ተደጋግሞ እንደእምነት ህግጋት ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰበክ ይሰማል፡፡

በህግ የመዳኘቱ ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ህዝቡ ባለበት አካባቢና ከየብሔሩ ባህላዊ ልማድ አንጻር ሲስተዋል ከተለያዩ እውነቶች ጋር ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ህዝቡን ባማከለ ስነልቦናዊ ልኬት የሚራመድ፤ ህግና ስርዓትን ለማክበር የመንግስትን ወይም የአስተዳዳሪዎችን መልካም ፈቃድ የማይሻ ስነምግባራዊና አእምሮዋዊ ብሎም ልቦናን ባገናዘበ መጠን ተቀባይነት የነበራቸው በርካታ እውነቶች ይስተዋሉበት የነበረ ማህበረሰብ እንደነበር ለማወቅ ቀደም ያሉ ጽሁፎችንና ታላላቆች እና ወላጆችን ጠይቆ መረዳት ይቻላል፡፡

ሀገር ከድንጋይ ቁልል ባሻገር፤ ከሲሚንቶ ግግር ወዲያ፤ ከቴክኖሎጂ ምጥቀት በላይ፤ ከፖለቲካዊ አንድምታና እወደድ ባዮች ገቢር የሌለው ቀረርቶ ባሻገር፤ ለግብሩ አጋዥ የሆኑ ቀደም ሲሉ የነበሩንና አሁንም ጨርሰው ያልጠፉትን የህገልቦና ብሎም የግብረገብ አስተምርሆዎች እንደሚያስፈልጓት ለመረዳት አሁን በየአካባቢው እየተከሰተ ያለውን ሁነት ተከትሎ እየሆነ ያለውን ነገር በማየት መረዳት ቀላል ሆኖ ይታየኛል፡፡

በነገራችን ላይ የህግን ጉዳይ በተመለከተ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም በአንድ ጽሁፋቸው ያነሱትን ነገር እዚህ ለመጠቀም ልሞክርማ፤
‹‹ በየትኛውም ጥንታውያን አገሮች እንደነበረው ሁሉ በኢትዮጵያም በሕግ ከለላ የተሰጣቸው፣ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ በደል ያደረሱ እንደ ባሪያ ንግድና እንደ ባለርስትና ጭሰኛ የመሳሰሉ አጸያፊ ሥርዓቶችና ሕጋዊ ግንኙነቶች እንደነበሩ አይካድም። ይህም ሆኖ ግን ጥንታውያን ሕጎች፣ የኃይማኖት ድንጋጌዎችና ባህላዊ ሕጎች መኖርና በሥራ ላይ መዋል በጥቅሉ በሀገራችን ፍትሃዊነት በህዝብ አዕምሮ እንዲሰርጽ አድርገዋል። ህዝቡ ለሕግ ከበሬታ እንዲኖረውና ግፍና በደልን እንዲጠላ፣ በጠቅላላው ፍትሃዊነት እንደ አንድ ብርቅዬ ዕሴት እንዲቆጠር በህዝብ እምነት ውስጥ ተቀርጿል።
 ህዝቡ ለሕግ ከፍተኛ ከበሬታ እንደነበረው የሚገልጹ አያሌ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ሁለት ባላጋራዎች መንገድ ላይ ቢገናኙ ተበደልኩ ባዩ ምንም ኃይል ሳይጠቀምበሕግ አምላክ ቁም!” በማለት ብቻ ባላጋራውን አስቁሞ የነጠላዎቻቸውን ጫፍ ቋጥረው (ተቆራኝተው) ያለ ፖሊስ አጃቢ ወደ መረጡት ዳኛ ዘንድ ሄደው ፍርዳቸውን ይቀበሉ ነበር። ለዚህም ነው እስከዛሬበቆረጥከው ዱላ ብትመታ፣ በመረጥከው ዳኛ ብትረታእንዲቆጭህ አይገባም የሚባለው።በሕግ አምላክ!” ሲባል ውሃ እንኳን ይቆማል ይባል ነበር።››

አሁን አሁን ግን በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ ያለው የደቦ ፍርድ ምናልባትም ከላይ ከጠቃቀስናቸው ኢትዮጵያዊ ዕሴቶች ወጣ ያሉ ብሎም የህዝቡን መልካም ስነልቦና የማይወክሉ ሆነው ይታያሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን፤ እንዲህ ያሉ ሁነቶችን በአደባባይ ማውገዝም ሆነ፤ ጉዳዩ በሚፈጸምባቸው ቦታዎች ላይ ማህበረሰቡ ‹ተው/ተይ/ተዉ› የሚል ‹ከልካይ› መጥፋቱ ምን ይባል እንደሁ ለእኔ ግራ ነው፡፡

በሀገራችን ካለው በርካታ ‹ሐፍረት› መካከል ቀደም ሲልም ይደረግ እንደነበረው፤ አሁንም ከዶ/ር ያዕቆብ ጽሁፍ እንደጠቀስኩት ጥፋት ተሰርቶ እንደሁ እንኳ ‹በሕግ አምላክ› የሚለው ቃል ክብር ነበረው፡፡ ይህ እንግዲህ ህግና ስርዓት ምን ያህል ቦታ ይሰጣቸውን እንደነበር ማሳያ ነው፡፡

እንዲሁ በተለምዶም  ቢሆን፤ እናቱ ‹በጡቴ› ብላ የልመና ጥሪዋን በምታሰማበት ወቅት የሚኖረውን የልጅ ስሜት መቀዝቀዝ ብሎም ከእናት መስመር ያለመውጣት ሁናቴ፤ በሌላም ሁኔታ ‹ስለባንዲራው› የሚል ምልጃና ልመና የነበረበት ሀገር መሆኑን፤ የእናቶች ነጠላ ዘርግቶ ሰው የመገላገልና የመሸምገል፤ የመዳኘት ሁነቶች ከተወሰኑ አመታት ወዲህ ሲስተዋሉ አይታይም፡፡ ወግና ልማድን በአንድ በኩል፤ ስልጣኔን በሌላ በኩል ማስታረቅ አቅቶን እንደህዝብ አንዳች አዙሪት ውስጥ ገብተን ስንቃትት ይታያል፡፡

ይህም እንደሀገር ሐፍረታችንን ጥለን በሌላ አቅጣጫ እየተጓዝን ስለመሆኑ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ከሕግ አንጻር ሊታዩ የሚገባቸውን ጉዳዮች ሁሉም በየፊናው ፍርድ መስጠት ከጀመረ ግን፤ ዛሬም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሌላ አስጸያፊ፤ ሌላ ደግሞ ወደፊት አንዳች ጥግ ይዞ እነዚህን ዛሬ የተከወኑ ጉዳዮች እያነሳ ‹መጥፎ› ታሪክ ሊጽፍ እንዲችል እንዳይሆን ያስፈራል፡፡

በተለይም እንዲህ ያሉ የደቦ ፍርዶች ድግግሞሽ ማህበረሰቡንም እንደህዝብ፤ ኢትዮጵያንም እንደሀገር የታመነ መንግስታዊ ስርዓት፤ ብሎም በየደረጃው ያሉ የፍትህ አካላትን መኖር እንድናጠይቅ ያደርገናል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያሉ ተግባራት በማህበረሰቡ ውስጥ በተደጋጋሚ ሊታዩ የሚችሉት፤ ህዝቡ በመንግስት ተቋማት ላይ ያለው እምነት በሚሸረሸርበት፤ ወይንም ወደህግ በመሄዱ የሚፈልገውን ፍትሐዊነት እንሚያጣጥምና በእስካሁኑ ቆይታው ያስተናገዳቸውን እውነቶች በማካተት ሊሆን እንደሚችል ስለደቦ ፍርድ የተጻፉ ጥናታዊ ጽሁፎች ያስረዳሉ፡፡

ይሁንና በማናቸውም መለኪያ እንዲያሉ የደቦ ፍርዶች ሰብዓዊነት የሚያራክሱ፤ የመኖርን ትርጉም የሚያሳንሱና በማናቸውም ሁኔታ በየትኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ላይ ሊከወኑ የማይገባቸው እንደሆኑ በርካታች ይስማማሉ፡፡

ለዛም ነው በማናቸውም መመዘኛ መንግስት በተለይም አሁን ባለው ሁኔታ የፍትህ አካላትንና ተቋማትን በህዝቡ አመኔታ እንዲያድርባቸው መስራት፤ እንዲሁም እንዲህ ያሉት የደቦ ፍርዶች ጉዳት እንዳላቸው ማህበረሰቡን የማንቃት ስራ ተደጋግሞ ሊሠራ ይገባል፡፡

‹ሀገርና ጩኸት›


ዝም የምንልበት ሳይሆን የምንወያይበት ጊዜ ነው

ሀገር የማቅናት ፈተና ውስጥ ነን፡፡ መንግስት በአንድ በኩል አረገብኩ ሲል በሌላ በኩል ድምጽ አለ፡፡ እዚህ ሰፈር ሲሰክን፤ እዚያ ሰፈር ይደፈርሳል፡፡ ሀገሬ እንዲህ ባለው ሙቀት እየታመሰች አለች፡፡ እውነት ነው ለአመታት በዚህ አዙሪት ውስጥ ነው ያለፈችው፡፡ የሥልጣን ሽግግር ከተካሄደ ወዲያም ቢሆን እዚህም እዚያም ያለው ድምጽ አንዳንዴም ሲያውክ፤ አንዳንዴም ሲያበሳጭ፤ አንዳንዴም ሲያሳስብ፤ ብቻ ባለብዙ መልክ ሆኖ ቀጥሎ ይስተዋላል፡፡

ሀገር በጩኸት ብትፈርስ፤ ኢትዮጰያ የኢያሪኮን ታሪክ በደገመችው ነበር፡፡ አዋቂ የበዛበት ዘመን ሆኗል፡፡ በተፈለጉ ዘመን ያልነበሩ ‹ምሁራን› አሁን በየቴሌቪዥን መስኮቱ ይታያሉ፤ ትንታኔያቸው ሀገርን በ‹እውቀት› ሙላት ሊግቱ ሲታትሩ ይስተዋላሉ፡፡ የመታመን መጠናቸውን ለጊዜው ለመመዘን ባልችልም፡፡ ሀገር እንዲህ ባለው ጊዜ ሁነኛ ተዓማኒ የመረጃ ምንጭ ቢያስፈልጋትም፤ ከግልብ የሚነዱ በርካቶች አሉና የእነዚሁ ጋላቢዎች ቁርስ ራት መሆናቸው ግድ ነበር፤ ነውም፡፡

በተለይም እንዲህ ባለው ወቅት ሚዲያው ያለው ሚና ለክፉም ለደግም ቅርብ ነውና በርካቶቹ ጉዳዮች ጥንቃቄ ከመፈለግም ባሻገር ትዕግስት የሚፈትኑ አይነት እንዳይሆኑ በአንክሮ መከታተል ያሻል፡፡ ለህብረተሰቡ አጀንዳ በመቅረጽ የህዝብ ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች ላይ በትኩረት መስራት የሚገባበት ጊዜ ላይ ያለን ይመስለኛል፡፡ ሚዲያው ሀሳቦች የሚንሸራሸሩበት፤ የህዝቡ መንፈስና እሳቤዎች የሚዳሰሱበት እንዲሆኑ ምኞቴ ነበር፡፡ በተለይም በብሮድካስት ሚዲያው አካባቢ ያለው ነገር ከዚህ አንጻር ሲቃኝ አንድም ሚዲያዎቹን የሚመሩ አካላት አልያም ‹ባለሙያ› ነን የሚሉትና ፕሮግራሞች የሚያዘጋጁና የሚያቀርቡት፤ ዜናዎችን የሚያዘጋጁና የሚተነትኑት ግለሰቦች በእርግጥም ሙያውን ስለማወቃቸውና ስለመረዳታቸው ማጠየቅ ግድ ነው፡፡

ተንታኝ በዝቶ ይስተዋላል፡፡ ሁሉም ሰው ፖለቲከኛ ለመሆን ከመጣጣሩ በላይ ጉዳዮችን ለመተንተን የሚመርጠው ርዕሰ-ጉዳይ ከማንነቱ ጋር መነሻ ባደረገ መልኩ መሆኑን ለማስተዋል ረዥም ጊዜ ማጤን አይጠይቅም፡፡ በርካቶች በዚህ የማንነት ጉዳይ ተጠልፈው ሲወድቁ ይታያል፡፡ በ‹ማናለብኝነት› መንፈስ በርካታ ተከታዮች አሉኝ፤ አልያም ብዙዎች ያነቡኛልና ያዳምጡኛል በሚል ‹ፈሊጥ› በርካቶች ሳይታሰብ ጠርዝ ላይ በአንዳች የ‹ግል› አጀንዳ ሳይቀር ቅርቃር ገብተው ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህኛው ቅርቃር እኒህን ግለሰቦች ለማላቀቅ ፈተና በዝቶ ይስተዋላልም፡፡

ጎራ ለይቶ መጠዛጠዙ በርክቶ ይስተዋላል፡፡ የሰው ልጅ ጉዳት ሳይሆን፤ የተጎዳው አካል ከየትኛው ወገን እንደሆነ ማጣራቱ ላይ አበርትቶ ሲሰራ ይስተዋላል፡፡ የተጎጂዎችን ጾታ ሳናውቅ ብሔራቸው ይነገረናል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው በምን መልክ መጠቀም እንደሚገባን የሚሰብኩ የሚመስሉን ግን ደግሞ ከምክራቸው ስሜት ሳንወጣ እነርሱ ራሳቸው በየገጾቻቸው ጠርዝ የረገጡ ጉዳዮችን የሚግቱን በርክተዋል፡፡

ለበርካታ ጊዜያት በተለይም የብሔር ብሔረሰቦችን ጉዳይ የሚያነሳውን አካል ጠባብና ዘረኛ፤ የአንድነትን ጉዳይ የሚያነሱ አካላትን ጉዳይ ደግሞ ‹የአንድነት ኃይል› እየተባሉ ሲፈረጁ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ትርጓሜ ውስጥ በርካታ ሠዎች ለመካተት ሲሹ መስተዋሉ አይካድም፡፡ በተግባር የሆኑት እና የኖሩት ግን ጥቂቶች ቢመስሉም፡፡

አንድነት ማለት ሀገራዊ መሠረት ባደረጀ ሁናቴ ልዩነቶችን አቻችሎ በሚያግባቡና በሚያመሳስሉ ጉዳዮች ላይ የበለጠውን መልካም ነገር ጨምሮ ለመኖር የሚደረገው ጥረት ሲሆን፤ አንዳንድ ይህንን አንድነት የሚባል ሀሳብ ባልተገባ ሁነት በመተርጎም ወደ አንድ አይነትነት ለመተርጎምና፤ በተግባርም ለማመለካት ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡

ኢትዮጵያ በመሠረቱ ያሏትን በርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እና ህዝቦች፣ ባህሎችና ቅርሶች፣ ወግና ልማዶች፣ ብሎም በርካታ ሁነቶችን ላስተዋለ ሰው፤ በተለይም ባለፉት በርካታ መቶና ሺህ አመታት ነገስታት የነበራቸውን ታሪክ ወደኋላ መለስ ብሎ ለተመለከተ፤ ህዝቦች በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት እንዲገብሩ ሆነዋል ተብሎ የተጻፉ ታሪኮቻችን በተለይም ባለፉት ሶስት አስርት አመታት የተጫናቸው አቧራ አራግፈው በአዲስ መልክ ሲተየቡ ተመልክተናል፡፡

በእነዚህም ታሪኮች ላይ መግባባት ላይ መድረስ ተስኖናል፡፡ ተመሳሳይ የሚመስልም ምልከታዎችን ማግኘት በራሱ ከባድ ሆኖብናል፡፡ የአንድ እንኳ ቢቀር የጋራ የምንለው የምናከብረው ባህል፤ ቀግና ልማድ ብሎም ጀግና ማውጣት ተስኖናል፡፡ ምሁራን የሚባሉትም ግለሰቦች ቢሆኑ፤ ከአንድ ሰፈር ቅርቃር ውስጥ በተቻላቸው መጠን ድምጽና ሙገሳ ለማግኘት ለብሔር ማንነታቸው (በተለይም የራሳቸውን ስምና ዝና ፍለጋ፤ አልያም በአካባቢያቸው ሰው ተቀባይነትን በማግኘት ወደአደባባይ ለመውጣት በማሰብ) ሲታገሉ ተስተውሏል፡፡ የጋራ የሚባለውን ጉዳይ እርግፍ አድርጎ በመተው ልዩነቶች ላይ በብርቱ ሲሰራ ታይቷል፡፡

መንግስትም በተለያዩ አጋጣሚዎች ይህንኑ ሲሰራ ተስተውሎ ሰንብቷል፡፡ ኢትዮጵያዊያንም ባሉበት ሁሉ ሀገርም ውስጥ ይሁን በሌላ ቦታ ከአንድነታቸው ይልቅ ልዩነቶቻቸው ላይ ሲወያዩና በዚሁ መንገድ ሲፈራረጁ ሰንብተዋል፡፡ ሆኖም፤ ይህንኑ ልዩነት ለዘመናት ሲደሰኮር ቢከርምም ማስታረቂያ እና መቻቻያ መንገዱን የሚያሳይ ጠፍቶ እርሱን በማስፋት ሂደት ውስጥ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ምናልባት ንጹህ ነኝ ሊል የሚችል ካለ ይገርመኛል፡፡ ፖለቲከኞቹም ቢሆኑ አጀንዳ እየፈጠሩልን በመሰለን መንገድ እንድንቆራቆዝ ሲታትሩ ከርመዋል፡፡

በዚህ ሁሉ መካከል የዶክተር አብይ መንግስት ስልጣን ከመያዙ አስቀድሞ በተለይም ሀገሪቱ የነበረችበትን ጭንቅ የሚያውቁት፤ በተለይም እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዜጎች ብቻ በቅጡ እንደሚረዱት አስባለሁ፡፡ እንዲያ ያለውን ፈታኝ ጊዜ ሀገር እንዴት ባለ ምጥ ልትወጣው እንደቻለችም ምስክሮቿ ዜጎች ብቻ ናቸው፡፡ እንዲያ የነበሩ ጭንቀቶች የአንድ ወገን ብቻ አልነበሩም፡፡ መልካሙን እንዲያመጣለት ሲመኝ የነበረው ህዝብ በርካታ ነበር፡፡

እዚያው ኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረ ሽኩቻ/ፍትግያ ከበርካታ ሁነቶች ወዲያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ፤ በተለይም የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የነበረው አጣብቂኝ በቅርቡም አቶ ኃይለማርያም በአንድ ሚዲያ ቀርበው እንዳነሱት ከባድ ነበር፡፡

ይህንን ሁሉ ጊዜ አለፍን ብለን የዶክተር አብይን ወደመንበሩ መምጣት ያሳየውን ተስፋ ተከትሎ በርካቶች በተለይም ከመጀመሪያው የፓርላማ ንግግራቸው ጀምሮ ኢትዮጵያንና ህዝቧን የገለጹበት ብሎም በተከታታይ ባደረጓቸው ንግግሮችም ያሳዩት ተስፋ ሰጪ ምልከታዎች ምናልባትም ሀገራችን ወደአንድ መልካም ወደፊት ጉዞ ለመጀመር የታተረች መስሎ እንዲሰማን አድርጎ ነበር፡፡
ይሁንና ወዲያው እዚህም እዚያም ከላይ ያነሳሁት አይነት ኮሽታ መሰማት ሲጀመር፤ ተስፋው በአንድ ጎን እንዳለ ሆኖ ስጋታችንም እያየለ ስለመምጣቱ ግልጽ ይመስለኛል፡፡ በርካቶችም ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው በተለያዩ ሚዲያዎች አንስተው ሲመሰክሩ ማስተዋል ተችሏል፡፡

ጩኸት በበረከተባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ምንድነው ደግሞ ዛሬ እያልን ተስፋችንን ሁሉ ጥለን ስጋትችን እየወረረ ሲያስቸግረን በአንድ በኩል ለሚፈጸሙ ሁሉ ጉዳዮች የመንግስትን (የሚመለከተው አካል) መግለጫ ከመጠበቅ ይልቅ መላምቶቻችን ከፍ እያሉ ህዝቡን ወደባሰ ስጋት ሲከቱት ለማስተዋል የተቻለ ይመስለኛል፡፡

ይህም ይመስለኛል ጩኸቶቻችንን ከጊዜ ወደጊዜ እያባሳቸው፤ ከፍም እያደረጋቸው ያለው፡፡ ትንታኔ የሚሹ ጉዳዮች ባለሙያዎች በትክክል ሁነቶች ላይ አስፈላጊ የሚባሉ መረጃዎችን ሰብስቦ፤ ተንትኖና አጠናቅሮ ከማቅረብ ይልቅ በራሳቸው የግል መላምቶች ተውጠው ለሚያስተውል ሰው፤ “ሀገሬ ከወደየትኛው ነሽ?” ያስብላል፡፡

በባህሪ አስቸጋሪ የሚባል ህዝብ የሌለባት ኢትዮጵያ፤ ለመሪዎችም ሆነ ለገዢዎች በሌሎች ሀገሮች እንደሚታየው አይነት ከመስመር የወጣና አልታዘዝም ባይ ብሎም በብዙ ግፊት የሚናወጥ አይነት ህዝብ የሌላት ኢትዮጵያ ስለምን እንዲህ ባለው ሁነት ውስጥ እንድታልፍ በርካቶች ታተሩ? ስለምንስ ህዝቦችን ወደተለያየ አቅጣጫ ለመምራ ሻቱ? ህዝቡስ (ዜጎች) ስለምን እንዲህ ባሉት አስተምርሆ አቀንቃኞች መዳፍ ወደቀ? ፖለቲካችንስ ስለምን ለጥቂቶች ብቻ የተተወ በርካቶች ጀምረው የማይጨርሱት አይነት ሩጫ ሆነ?

ከላይ ያነሳኋቸው ሀሳቦች እንዳሉ ሆነው፤ ኢትዮጵያ እንደሀገር፤ ህዝቡም እንደዜጋ በተለይም የነበሩትን ባህሎች፤ አብሮ የመኖር ልማዱና እሴቶቹን ስለእኩይ አስተምርሆዎች ስለምን አውልቆ ጣለ? ከሐፍረታችን ባሻገር ያለው ጉዳይ በቅጡ መነገር መወያየትም የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ ሁሉን በዝምታ የምናልፍበት ሳይሆን የምንወያይ የምንነጋገርበት ጊዜም እንደሆነ አስባለሁና፡፡
ካልሆነ አሁን ባለው ጩኸት መጠን እስከመቼስ እንቀጥላለን? ስርዓት ለዘመናት የሚኖር ግብርም በልክ ለመከወን ሁነኛ መንገድ ነውና በኢያሪኮም የሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ቃል ታነቡማላችሁ፡-

‹‹መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ ምዕ. 6፡20
ህዝቡም ጮኹ፤ ካህናቱም ቀንደመለከቱን ነፉ፤ ህዝቡም ቀንደመለከቱን ድምጽ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፤ ቅጥሩም ወደቀ ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ወደፊቱ ወደከተማይቱ ወጣ፤ ከተማይቱንም ወሰዱ፡፡››

ወደፊት ከሐፍረታችን ባሻገር ባልኩዋቸው ሀሳቦች ዙሪያ እመለሳለሁ፡፡ ሰላም!!!

2017 ሴፕቴምበር 8, ዓርብ

‹‹አለህ’ኮ ይሉኛል፤ እውነት አለሁኝ ወይ?›› - ኢትዮጵያዊነት




ወዳጅ በፍቃዱ ኃይሉ ‹‹ኢትዮጵያ ያለ‹ኢትዮጵያዊነት› ልትኖር አትችልም?›› በሚል ርዕስ ለአዲስ አመት መወያያ ጽሁፍ አቅርቦ አነበብኩ፡፡ እነሆ ምልከታዬን ላሰፍር ወደድኩ፡፡
 
ዘመኑ የመሞካሸት ነው፡፡ ኢትዮጵያም ወግ ደርሷት ትሞካሽ ይዛለች፡፡ ወዳጄ በፍቃዱ ኃይሉ አንዳንዱን ጠቅሷል፡፡ እኔ ደግሞ ሰሞንኛውን የ‹ከፍታ› ዘመን ትንቢቷን እጠቅሳለሁ፡፡ ‹ለዘለአለም ትኑር› ‹ይባርካት›ም እየተባለች ያለችውን ኢትዮጵያ፤ አሁን ደግሞ ወደ‹ከፍታ›ው ለመመለስ ጥረት ላይ ያለው ብዙ ነው፡፡
ሀገርኛውን ጉዳይ በብርቱ ማንሳት ተገቢ ነውና እነሆ እኔም ወዳጄ ባነሳው ጉዳይ ላይ የእኔን ምልከታ ለማንሳት ወደድኩ፡፡ በፍቃዱ በአዲስ አመት እንድንወያይበት ያነሳው ጉዳይ መልካም መስሎ ታይቶኛልና ነው ይህንን ማለቴ፡፡
 
ኢትዮጵያ መቼም ከዘመን የናኘ፣ የገዘፈና የበረከተ አመት ታሪክ እንዳላት ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡ በርካቶችም በዚሁ ይስማማሉ፡፡ አንዳንዶች በእርግጥ ይህንን የዕድሜዋን ነገር እንደሚጠራጠሩ ቢታወቅም ማለት ነው፡፡ በአንድ ወቅት በዚሁ ጉዳይ ላይ ሀሳብ ሰንዝሬ ነበርና አልመለስበትም፡፡
 
ኢትዮጵያ እንደሀገር ከተመሠረተችበት ወቅት ጊዜ አንስቶ በርካታ ጊዜያትን አሳልፋለች፡፡ በተለይ ደግሞ አሁን አሁን የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ እያነጋገረ መምጣቱ፤ በጉዳዩ ላይ ጥርት ያለ እውነት ይዞ መውጣት እንደሚያሻ አመላካች ነው፡፡ 
 
በዚህም ረገድ ኢትዮጵያን አንድ ብቻ ሆና የማየት ምኞት ያላቸውና የለም ብሔራችን ቀዳሚውን ድርሻ መያዝ አለበት ብለው የሚያስቡ ልሂቃንና ሌሎችም ተነስተው በተለይም በቅርብ ጊዜ የመነጋገሪያ አጀንዳ አድርገውት መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
 
በመሠረቱ ፖለቲካችን የብሔር እንዲሆን ለምን ሆነ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የብሔር ፖለቲካው እንዴት እንዲህ ሊይብብ ቻለ? ማለትም ተገቢ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ታዲያ በደፈናው ጉዳት አለው ብቻ ብሎ መደምደምስ ተገቢ ነው ወይ? እንዲህ በርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በሚኖሩባት ሀገር፤ የብሔርን ጉዳይ አንስቶ መነጋገር ለሀገር አንድነት አስጊ ነው ብሎ መደምደም በእራሱ የተዳፈነው እንደተዳፈነ ይቆይ፤ አትነካኩ ማለት አይመስልም ወይ? በተለይም አሁን ባለው ሁኔታ በደንብ ልንነጋገርበት ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደአንዳንዶች በደፈናው ሰው መሆንህን ብቻ አስቀድም ብሎ መመጻደቅም ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ደግሞ ከኢትዮጵያዊያን ወዲያ ህያው ምስክር የለም፡፡ አንድ እንሁን ባለ አንደበታቸው የስንቱን ብሔር እያወጡ ሲናገሩ፣ የስንቱንም ጓዳ ጎድጓዳ ሲማስኑ እንደሰነበቱ ለመመልከት ችለናል፡፡
 
ብሔርን ማዕከል ያደረገው አስተሳሰብ ለምን እንዲህ ሊነሳ ቻለ? ከተባለ ዋነኛ ምክንያቱ ጭቆና ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተገቢው አኳኸን ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለተወሰኑት ብሔሮች ብቻ የተመቸች መሆን አለባት ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ እርሱም በእራሱ አደገኛ ነው፡፡ ምቾት ከተባለ ለሁሉም ነው መሆን ያለበት፡፡ በአንደኛው መገፋት ሌላኛው እንዲመቸው መታሰብም የለበትም፡፡ ይህ ግን ታዲያ ብሔርን ለምን ትጠቅሳላችሁ ኢትዮጵያዊነትን ብቻ በደፈናው አራምዱ አይነት ዲስኩር እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡
 
ኢትዮጵያ የሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች መኖሪያ ናት፡፡ ይህች ሀገር ታዲያ ሀገርነቷ ለሁሉም እስከሆነ ድረስ፤ ሁሉም ብሔሮች እምነታቸው፣ ባህላቸው፣ አኗኗራቸው፣ በአጠቃላይ ማንነታቸው ሁሉ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ውስጥ አብሮ መነሳት መቻል አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ‹ኢትዮጵያዊነት› ከንግግር አልፎ ተግባራዊነቱ ጽንፍ ካስያዘ መልካም አይደለም፡፡ በምንናገረው ልክ ተግባራችን መከወን አለበት፡፡ ይህ ደግሞ ግድ ነው፡፡ 
 
አንዳንዶች የብሔር ጉዳይ መነሳቱ ልዩነቶች እየሰፉ መጥተው ኢትዮጵያ የሚለውን ትልቁን የአንድነት ጥላ እንደሚያፈርስና የአገሪቱ ህልውና በክልልና በብሔር ማንነቶች ላይ የተንጠለጠለ እንዲሆን ያደርገዋል ይላል፡፡ እዚህ ላይ ታዲያ ይህችን ሀገር የሰሯት እነማን ናቸው? ሀገሪቱስ ብትሆን የብሔሮቹ ውህድ ውጤት አይደለችም ወይ? አሁንም ቢሆን፤ ማንኛውም ሀገራዊ ነገር ሲከወን ሁሉንም ባማከለና ለሁሉም ብሔሮች ሁለንተናዊ ጥቅም መሆን የለበትም ወይ? በዚህ አግባብስ አሁን ላይ የሚነሱት ብሔርን ያማከሉ እውነቶች ተገቢ አይደሉም ወይ? ነገሮችስ እውነት እንዲሁ እየተዳፈኑ፤ ኢትዮጵያዊነትና አንድነት በሚል የሁሉንም ልብ ሊረታ በሚች ቃል ብቻ እውነቶች ታጭቀው ሳይወጡ መቅረት አለባቸው?
 
ይህ መሆን እንደሌለበት ይሰማኛል፡፡ አንድነት መልካም ቢሆንም፤ ኢትዮጵያዊነት ጥሩ ቢሆንም፤ ከቃል በዘለለ በእውነት ላይ የተመረኮዘ ማንነት ጉዳይ ሲነሳ ታሪክ አታጣቅሱ እንደሚሉት ግለሰቦች መታሰብ የለበትም፡፡
ዛሬ ላይ የምናወራላት ኢትዮጵያ በበርካታ ዜጎች አጥንትና ደም የተገነባች ሀገር ናት፡፡ ይህች ሀገር ታዲያ ሀገር ሆና ለዛሬ እንድትበቃ ዋጋ የከፈሉት አካላት በሙሉ እኩል ሊወደሱ ይገባል፡፡ በሀገር አንድነት ስም ዘር እስከማጥፋት የደረሱት ደግሞ ሊኮነኑ ግድ ነው፡፡ አትንኩብኝ፤ አትንኩብን ተብሎ አይቻልም፡፡ በየትኛውም አጋጣሚ ቢሆን የኢትዮጵያን አንድነት በተሻለ አግባብ መፍጠር የሚቻለው እውነትን እየሸሹ ሳይሆን እየተጋፈጡ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አለሙ ዛሬ ሌላ ነው፡፡
 
በመሠረቱ የብሔር ጥያቄ የማንነት ጥያቄ ተደርጎ መነሳቱ በርካቶችን አስከፍቶ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ብሔርን በትክክል ከፍ ባለ ድምጽ መናገር አዳጋችና አስነዋሪ በሚመስልበት ዘመን ያለፍን እኛ ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይም ብሔርን ለመናገር ከተወሰኑ ብሔር ተወላጆች በቀር ሌላው እንደሌላ ነገር ይታይበት በነበረባት ይህችው ኢትዮጵያ፤ በሀይማኖት፣ በባህልና በኢኮኖሚ የሚጨቆኑ ብሔሮች በነበሩባት ኢትዮጵያ ላይ ሆነን ‹እንደምን ዛሬ ላይ ተነስታችሁ በይፋ ማንነታችሁን ተናገራችሁ?› አይነት ነገር ተገቢ አይሆንም፡፡ በዚህ አግባብም የምትሄድ ኢትዮጵያን ባናስባት የተሻለ ይመስለኛል፡፡
 
በእውኑ፤ ሀገር ማለት ከባድ ትርጉም እንዳለው ማንም መረዳት ያቅተዋል የሚል ምልከታ የለኝም፡፡ ሀገር ደግሞ የማንነት ምሳሌ ስትሆን የእኔንም ባህል፣ ታሪክና ምሉዕነቴን ተቀብላ በእርሷ እንደምወከል ልታሳየኝ ግድ ነው፡፡ ዜግነትን ከማንነት ከቀላቀልነው ችግር የሚሆነው ለዚሁ ነው፡፡ ገጣሚው እንዳለው ‹ሀገር ማለት ረቂቅ ነው ቃሉ›፤ ማንነትም ታዲያ የደምና የአጥንት ዋጋ የተከፈለበት ውስብስብ መሠረት ያለው አንዳች እምቅ የራስ መገለጫ ነው፡፡

ማንነታቸውን በግልጽ የተናገሩና በማንነታቸው ላይ ሀሳባቸውን ያስተጋቡ ግለሰቦች ልዩነትን ለማስፋት እንደሚንቀሳቀሱ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ይህ ደግሞ መልካም አይደለም፡፡ በተጨማሪም ለአንድነት ጸሮች እንደሆኑና ይህንኑ በመናድ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ እንደሚሞክሩ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ 
 
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በተለይም ‹የአንድነት ሀይሎች/አቀንቃኞች› ነን የሚሉት ግለሰቦችና ቡድኖች ብሔርን የተመለከተ ጉዳይ የሚያነሱ ግለሰቦችና ቡድኖች በሙሉ በአንድ ድምጽ ‹ዘረኞች› ተብለው ሲወቀሱና ሲዘለፉ ይታያል፡፡ በእኔ አመለካከት የኢትዮጵያን አንድነት ከመሻት አልያም ከሌላ መንፈስ በመነሳት ብቻ የብሔርን ጉዳይ አንስቶ መናገር ዘረኛ ሊያስብ አይችልም፡፡
 
በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ አይሎ ይሆናል፡፡ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔር የተደራጁ ሆነው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የታሪክ ነገር ሲነሳ ብሔሮች የሚያነሷቸውን እውነቶች በጥቅሉ እየተቃወሙ ስለአንድነት ብቻ እንዘምር መባባሉ ከባድ ይሆናል፡፡
 
ኢትዮጵያን በተመለከተ ከእኛ ወዲያ፣ አንድነት ከምንለው ሰዎች ባሻገር ……. የሚሉትም ቢሆኑ እርሱን ትቶ፤ በእኔ እምነት ኢትዮጵያዊነትን ሳይሆን እራሷን ኢትዮጵያን ብናስቀድም እመርጣለሁ፡፡ ያኔ በመከባበር መንፈስ ስለሀገር ማቀንቀን እንጀምራለን፡፡ ሜዳው እኩል እንዲሆን ባልፈቀድነው ልክ ግን ለመነጋገር ጉዳዩን አሁንም ማለባበስ ይሆንብናል፡፡ በእራሳችን ስጋት ውስጥ ታጭቀን ሌሎችን ለማዳመጥ አለመውደድ ግን ሊታሰብበት ግድ የሚል መሰለኝ፡፡ ስለመሰለኝም ሀሳቤን ለማካፈል ወደድኩ፡፡ ኢትዮጵያን አስቀድሜያለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነቱማ የለም፡፡ ገና ብዙ ልንለፋበት ያስፈልገናል፡፡ በእኛነታችን ላይ መስማማት ያስፈልገናል፡፡ ስለሆነም፤ ‹‹አለህ’ኮ ይሉኛል፤ እውነት አለሁኝ ወይ?›› - ኢትዮጵያዊነት
 
ቸር ያቆየን!
 
አብርሃም ተስፋዬ