2014 ማርች 28, ዓርብ

ዝምታሽ አልበዛም ኢትዮጵያዬ?


‹‹ሀገርን ፍለጋ››


<<የተገነቡትና በመገንባት ላይ ያሉት የመታሰቢያ ሐውልቶች የሠማዕታት ወይስ የቅሱፋን?>> በሚል በሠዓሊ አምሳሉ /ኪዳን አርጋው የተጻፈ የተባለውንና ዕንቁ መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር113 መጋቢት 2006 ..ን ዋቢ ያደረገውን የhttp://www.goolgule.com/monuments-for-martyrs-or-victims/ ጽሑፍ አነበብኩና ዝምታን ለመምረጥ አልወደድኩም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዬ እራስሽን ልጠይቅሽ ባክሽ?
መቼም ታሪክሽ መያዣ መጨበጫ ያጣ ይመስላል፡፡ ሁሉም ተነስቶ የሚጽፈው አይነት ሆኖልሻል፡፡ አንዳች እውነት ውስጡ ለማግኘት በደንብ መበርበር የሚፈልግ፤ አንደኛው የሚጽፈውን ሌላኛው በእርግጥም ድብን አድርጎ አሳማኝ በሆነ ሁኔታ የሚሽርበት አይነት ነው፡፡ ሀገሬ ግን በመሀከል ቤት ቁጭ ብለሽ ታሪክ አልባ እየሆንሽ ያለሽ መሰለኝ፡፡ በ‹‹አዋቂነት እርሾ›› ሰበብ ሁሉም እየተነሳ የሚጽፍብሽ አይነት ሆነሽ፤ ቀራጺውም፤ ሰዓሊውም፤ የታሪክ ምሩቁም፤ ፖለቲከኛውም፤ ለቀስተኛውም፤ አላቃሹም፤ ታሪክ ጸሐፊ ሆኖብሽ የተቸገርሽ መሰለኝ ሀገሬ፡፡ ሀገሬ ምናባቴ ላርግሽ? ምን ይሻልሽ ይሆን? እኔም ታዲያ ልጠይቅሻ፡፡ እንደእናት አንድ በይኝ፡፡ መልስ ስጪኝ እናት አለም፡፡

አንድነትን ሰበብ አድርገው ማንነትን የሚሞግቱ ‹‹አዋቂዎችሽ›› ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡ አሁንም የሚሉት ያላቸው መሰለኝ፡፡ እያሉም ነው፡፡ በመከባበርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ አንድነትሽን የሚናፍቁና ቢሆን የሚወዱ እንዳሉ የተረዱት ‹‹አዋቂዎችሽ›› እናትነትሽ ለእነርሱ እንጂ ለሌላው እንዳልሆነ እየመሰከሩልሽ ነው፡፡ ሌሎችስ ማን አላቸው ያላንቺ? ሀገሬ ይገርምሻል አዋቂ የሚባሉት ሰዎችሽ ለሽምግልናና ለማሳያ የምንጠቀምባቸው የነበሩ ግለሰቦች ነበሩ፡፡ ዘቀጡ፡፡ ለልጆችሽ እልህ እንጂ ታሪክና መሰንበቻውን የሚያቆይሽ ነገር አላስቀምጥልሽ ብለው ይኸው አሰቃዩን፡፡ ‹‹አዋቂዎችሽ›› ግን ምን ነካቸው?

ሀገሬ ግን እውነት ታውቂናለሽ? እኛ በእርግጥም በውስጥሽ አለን? ነው ወይስ ተሳስተሸ ይሆን ያኖርሽን? አሁን መቼም አንቺ ስለሆንሽ እንጂ ሌላ ሀገር ቢሆን እንዲህ ይዘቀጣል? ይግረምሽ ብሎ አንደኛው ሠዓሊሽ ‹‹የታሪክ ምሁር›› ነኝ ብሎ ነው መሰለኝ ለህትመት ያበቃውን አየሁልሽና ከፋኝ፡፡ ስለዚህም እነግርሻለሁ፡፡ ቢያቅርሽም ቅሉ ስሚኝ፡፡ ወደድሽም ጠላሽም ጊዜ ስጪኝ ሀገሬ፡፡
ሠዓሊው ሰውዬሽ የመታሰቢያ ሐውልቶችሽ ለማን እና ለምን እንደሚሰሩ (ጠበቅ ተደርጎ ይነበብ) በሚሞግትበት (ምናልባት በተለይ ለኦሮሞ ህዝብ ያለውን የወረደ የክብር ልክና ስሜት ያሳየበት ይመስላል) ጽሁፉ ሕወሓት/ኢህአዴግን ሀገር አጥፊ ነው እያለ፤ በትጥቅ ትግሉም ግዜ ያለፉትን ታጋዮች በህይወት ካሉት እንደማይለዩ፤ ኢህአዴግ ለወደፊቱም እያኖረ ያለው ነገር መልካም አይደለም ሲል ያክላል፡፡ በዚህ ጽሑፉ ግን የአንቺ አንድነት ያሳሰበው መስሎ ልጆችሽን (በተለይ የኦሮሞ ተወላጆችና ብሔሩን በአጠቃላይ) ሙልጭ አድርጎ ያንቺ እንዳልሆኑ አስረድቶልሻል፡፡ ልጅሽ ከሆነ ገስጪው ሀገሬ፡፡

ሰዓሊው ‹‹ታሪከኛ›› ልጅሽ መሳይ ገንጣይሽ ትምክህቱን አራግፎታል አልኩሽ፡፡ መቼም አይተሽዋል፡፡ ሰምተሽውማል ብዬ አስባለሁ፡፡ እውነቴን ነው ዝም አትበይው፡፡ ጥሩ ልጅሽ አልመሰለኝም፡፡ እውነት ሀገሬ፤ ይህ ነገር ጥሩ አይደለም፡፡ ምን እንዳለ ታውቂያለሽ ኢትዮጵያዬ? አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ በሚል ለጨፈጨፉት ዜጎችሽ መታሰቢያነት የሚቆም ሀውልት ተገቢነቱን ሞገተ፡፡ በተለይ በአርሲ ለተከወነው የቆመውን የአኖሌን ሀውልት ጉዳይ ሲያነሳ፤ ኦሮሞዎችን በጅምላ ታሪካቸውን የማያውቁ ብሎ ተሳለቀባቸው፡፡ ምን ያለው ነው ታዲያ ይሄ ሀገሬ? ንገሪኝ ግድ የለሽም፡፡ እኔ እንደሁ ልጅሽ ነኝ፡፡ ግዴለም ንገሪኝ፡፡ ስለአንቺ አንድነት የሚዘምሩ መስለው መርዛቸውን የሚረጩብሽ በዙ እኮ፡፡ ሀገሬ ዝም አትበይ እንጂ፡፡ ምን ነክቶሻል፡፡ ግዴለም ያልለመደብሽን ዝምታ ከየት አመጣሽው? ቁጣሽ የት ሄደ እናትአለም? ሀገሬ ግድ የለሽም በርትተሽ ተቆጪ፡፡ ወኔሽን ሰለቡት እንዴ? አለን ብለው፤ መስለው አስኮረፉሽ እንዴ?

ሠዐሊው ልጅሽ ነኝ ባይ ‹‹ይታያችሁ ኢትዮጵያ አንድ እንዳትሆን ሲታገሉ ተገቢ እርምጃ የተወሰደባቸው የሀገር ጠላቶች፤ የአንድነት እንቅፋቶች ሆነው እያለ መስዋዕትንት የከፈሉ ይሉዋቸዋል›› ብሎ በግፍ የተጨፈጨፉ ዜጎችሽ ላይ ተሳለቀ፡፡ አንድነትሽ ሲናድ በወቅቱ ለመመለስ የተደረገ ነው ብሎ የሚያምነውን ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ተገቢ ነው ይልሻል፡፡ ቤታችን፣ መኩሪያችን ብለው በእናት መስለው የሚኖሩትን ብሔር ብሔረሰቦችሽን ‹‹ጎጦች›› አላቸው፡፡ ዜጎች ዛሬ ላይ ላሉበት ነገር ዋጋ የከፈሉላቸውን ወንድም እህቶቻቸውን ለማሰብ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ፤ ብሎም የመታሰቢያ ሐውልቶችን መስራታቸውን ሁሉ ‹‹አጥፊ›› ነው ብሎ ፈረጀልሽ፡፡ የእርሱን ስድብና ፉከራ ግን ‹‹ምርቃት›› ነው ሊልሽ ይሆን? እንደሁ ጠይቂልኝ፡፡ እባክሽ ሀገሬ ግድ የለሽም ጠይቂው፡፡

ሀገሬ መቼም አንቺ እንደ ልጅሽ ነይ ባዩ ሠዐሊ ልጆችሽ ታሪካቸውን የሚስቱ/የማያውቁ አይመስልሽም አይደል? እርሱን እርግጠኛ ነኝ፡፡ እንደው ይህ ሠዐሊ ሲስልሽ ባየሁት፡፡ እውነት ግን ሠዐሊ ነው ኢትዮጵያዬ? ግዴለሽም በደንብ አጣሪ፡፡ በአንቺ የዋህነት አይሆንም፡፡ ሠውየው ሌላ አጀንዳ ያለው ይመስላል፡፡ ታሪክን የ‹‹ፈጠራ ወሬ›› ነው ብሎ ይሞግታል፡፡ ፈጠራ ማለት ምንድነው እናት አለም? ሥዕል ሊፈጠር ይችላል፡፡ ታሪክ ግን እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል? ሰውየውን አስረጂልኝማ፡፡ ግዴለም ሠውየው አንዳች ነገር ሆኖ ይሆናል፡፡

ጭራሽ ብሎ ብሎ ኢትዮጵያዬ፤ ኦሮሞ ልጆችሽን ኢትዮጵያዊያን አይደላችሁ ብሎዋቸው አረፈ፡፡ እንግድነታቸውን ነገራቸው፡፡ አይገርምሽም ስላንቺ አንድነት የሚያስብ የሚመስለው ሠዐሊ አንቺን አንድ እንደሆንሽ ሲደሰኩር አርፍዶ ልጆችሽን ግን ያንቺ እንዳልሆኑ ነገራቸው፡፡ ‹‹ታዲያ ሀገራቸው የት ነው?›› ብለሽ ጠይቂው በሞቴ፡፡ እናት አለም እባክሽ ጠይቂው፡፡ በእኔ ሞት ይሁንብሽ ጠይቂው፡፡ ምን እንዳለ ልንገርሽማ ‹‹የኦሮሞ ህዝብ እነዚህን የልብ ወለድ ገጸባህሪያትንና ዓላማቸውን ምሳሌ አርአያ አንዲያደርጉ የሚወተውቱ የኦሮሞን ህዝብ ሊያሳስቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለውን አንድነትና ዝምድና ሊያራርቁ ሊሸረሽሩ፣ ሊያሻክሩ የሚችሉ መርዘኛ የፈጠራ ወሬዎች የሚሰበክበት የጥፋት ማዕከል እንደሚያደርገው በቀላሉ መገመት ይቻላል›› ይላል ስለ አኖሌ ሀውልትና ሙዚየሙ ሲያወሳ፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ያለው አንድነት ነው ልዩነት? ሀገሬ ግዴለም ጠይቂው፡፡ አትፍሪ እናት አለም ብቻ ጠይቀሽው ይውጣልሽ፡፡ ምን ይልሽ ይሆን እንስማው፡፡ ቀጠለና ምን ደግሞ አለ አትይኝም? እርሱ መች ትቶት ኢትዮጵያዬ ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ብዙ ባለአእምሮ ዜጎች ያሉት አስተዋይ የሕዝባችን አካል ነው›› አይል መሰለሽ? ገራሚ ነው፡፡
የኦሮሞን ህዝብ እንግድነት በግልጽ አስፍሮልሻል፡፡ ኢትዮጵያዬ መቼም እንዲህ ታሪክ አልባ የሚያረጉሽን ሠዐሊውንና መሰሎቻቸውን ምን ትያቸው ይሆን? ‹‹ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ባለው የሀገራችን ታሪክ ግን የሌሎቹ ብሔረሰቦች በሀገሪቱ መኖር በአንድም በሌላም አጋጣሚዎች ተጠቅሶ ሲገኝ የኦሮሞዎቹ ግን ጨርሶ የለም›› ይልሻል፡፡ እውነት እነርሱ ብቻ ነበር ያልነበሩት? ጨርሶ ደግሞ ሲያስረግጥልሽ ምን ቢልሽ ጥሩ ነው? ‹‹ይህም የሆነበት ምክንያት በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው በሀገሪቱ ስላልነበሩ ነው፡፡ የግራኝ ወረራ በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ከገቡ በላ ግን በሀገሪቱ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ ሚና ለመጫወት ሲበቁ እንደእንግድነታቸው አልነበረም›› ብሎሽ እርፍ፡፡ አክሎም ተሳትፎ ለማድረግ ፈጣን እንደነበሩ አትቶልሻል፡፡

ተመልሶ ደግሞ አንዳንዶች (በእርሱ አገላለጽ የጥፋት ኃይሎች) ኦሮሚያን እንገነጥላለን፤ ነጻ መንግስት እንመሰርታለን ገለመሌ ሲሉ የቅርብ ግዜ እንግዶች እንደሆኑ ማስታወስ ይኖርበት እንደሁ ይጠይቅማል፡፡ የማንን ሀገር እንደሚገነጥሉም ግራ የገባው መስሎ ይጠይቃል፡፡ ሀገር አልባ ናቸው እንዴ ልጆችሽ? እሰኪ ንገሪያቸው ባክሽ፡፡ ሀገራችሁ አይለሁም ካልሽም፤ የት እንደሁ መሆን የሚገባቸው አሳይያቸው ባክሽ፡፡ ምክንያቱም ልጅሽ ነኝ ባዩ ሠዐሊ ‹‹ኢትዮጵያዊ አይደለንም ካሉ ሀገሪቱን ለቀው ወደመጡበት የመመለስ መብታቸው የተጠበቀ ነው›› ብሎ አዋጅ ነግሮልሻል፡፡ በነገርሽ ላይ ኢትዮጵያዬ እርሱ ግን አዋጅ ነጋሪና ነጋሪት ጎሳሚ ያደረገው ማነው? ሹመት ሰጥተሽው ነው ወይስ? ግዴለም ግን ልጆችሽ ይከፉብሻል፡፡ መከፋታቸው ደግሞ ጥልቅ ይሆን ይመስለኛል፡፡ ይህንን ብሎ ያበቃ መሰለሽ? ‹‹አጼ ምኒልክ አደረጉ የተባለውን ሁሉ እውነት አድርገውት ቢሆን እን£ ልክ ነበሩ›› ብሎ እርፍ፡፡ ሀገሬ የልጆችሽ ጡት ሲቆረጥ አያምሽም እንዴ? እናት አለም ለምን ዝም ትያለሽ? ተናገሪ እንጂ እንዴት በልጆችሽ ቁስል ሲቀለድ ዝም ትያለሽ?

ሰውየው ሀሳቡ ምን እንደሁ እንጃ፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር ልጠቁምሽ እወዳለሁ፡፡ ካንቺ ባላቅ ሀገሬ፤ አንድነትሽን እየሰበኩ ልዩነትሽን የሚያሰፉ ልጆች ነን ባዮች እየበዙልሽም እየበዙብሽም ነው፡፡ አንድ ብትያቸው መልካም ይመስለኛል፡፡ ኦሮሞ ልጆችሽ ‹‹በሌለና ባልነበረ ቅዠትና የተረት ተረት ታሪክ እየፈጠሩ›› እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ግድየለም ሀገሬ ዝምታሽ እውነት ለመናገር ደስ አላለኝም፡፡
ታዲያ ሠዐሊው ሰውዬ ‹‹ከዘመን በፊት ኢትዮጵያዊ ያላቸው ሆኖ ለመገኘት ያላቸውን ቅን ፍላጎት ብናደንቅም ማንነት ባልነበረና በሌለ ታሪክ ላይ አይመሰረትምና እናዝናለን›› ብሎ አረፈው፡፡ አሁን አማረ አለ የሀገሬ ሰው፡፡ ምን ማለት ነው ታዲያ ኢትዮጵያዬ? ግዴለሽም ሠውየው ሌሎችን ይላል እንጂ እርሱ እራሱ ከእውቅ የሥነ-ልቦና ሐኪሞችሽ በአንዱ መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ እኔ አልድገመው እንጂ ሰውየው ብዙ ስድብም ተሳድቦ ነበር፡፡ ለነገሩ እዛው ታይዋለሽ፡፡ ‹‹የጨለማ እድሜ ጸሐይ እስክትወጣ ድረስ ነው›› ብሎ ዛቻ ቢጤም አስፍሮዋል፡፡ ማን እንደሁ እንጃ፡፡ እንደፍቅር ሠባኪም ያደርገዋል፡፡ እንዴት ነው ግን እናት አለም በስምሽ የሚነገደው? አስበሽዋል አንድነትሽን በማሳበብ እንዴት እንደሚዘባበቱብሽ? አይተሽ ዝም አትበያቸው ባክሽ፡፡ የደም እንባ የሚያነቡ መኖራቸውንም ተናግሮዋል፡፡ ነገ የእርሱና የመሰለቹ መሆኑን ይናገራል፡፡

ሲደመድም ደግሞ መድኃኔአለም ልቡና ይስጣችሁ ብሎ ነበር፡፡ ልቡና ተሰጥቶት የጻፈ ነው የሚመስለው፡፡ ግን ይመስልሻል ሀገሬ? እውነት ልቡና ያለው ሠው እንዲህ ይጽፋል? ዘላለማዊ ክብር እንደሻማ ቀልጠው ይህቺን ሀገር (አንቺን ማለቱ እኮ ነው፡፡ ድንቄም) ከነጻነትሽ ጋር ላቆዩ ለአርበኞቹ እናት አባቶቻችን ይሁን ይላል፡፡ ይህኛው አገላለጽ ከልብ ቢሆን ደግ ሀሳብ ነበር፡፡ ነገር ግን አይመስልም፡፡ ሰውየው ምን እንደነካው እንጃ፤ ብዙ ዘላበደ፡፡
ሀገሬ ልጅሽ መሆኑን፤ ካንቺ አብራክ መውጣቱን ተጠራጠርኩ፡፡ አንድነትሽን የሚፈትነው እራሱ እያለ፤ ሌሎችን አስታኮ የልቡን ነገረሽ እኮ፡፡ እርሱ እንደሻማ ቀለጡ የሚላቸው እነማንን እንደሆነ አልነገረንም፡፡ እውነት እውነት ግን ሀገሬ፤ እኔ ደስ አላለኝም፡፡ ለምን እንደሆነ መቼም ይገባሻል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይህንን በማለቱ አልተደሰትሽም፡፡

እኔ የሚገርመኝ ባንቺ አንድነት ላይ የሚከራከሩት ሰዎች ሌሎችን ማሰብ አይፈልጉም፡፡ አንድነትሽን የሚመኙና የሚያስቡት እነርሱ ብቻ እንደሆኑ ያስቡና ሌላውን ከጨዋታው ውጪ ያደርጉታል፡፡ ፓርቲዎችሽም ቢሆኑ እንዲሁ ይመስሉኛል፡፡ በስመ ተቃዋሚ ከያሉበት ይጠራሩና ስለአንድነትሽ የሚዘምሩ መስለው ልዩነትሽን የሚያፈካ መነጽር ያጠልቁልናል፡፡ ለምን እንዲህ እንድናስብ እንደሚወዱ አላውቅም፡፡ ግን በቃ እንዲህ ናቸው፡፡

አሁን አሁን ደግሞ አዋቂ ነን ባዮችሽ፤ ህዝብሽን የሚከፍል፤ የሚሰነጥቅና የጎሪጥ የሚያተያይ ሀሳብ ያራምዱ ይዘዋል፡፡ እኔ ግን ዝምታሽን እሞግታለሁ፡፡ ለምን ዝም ትያቸዋለሽ? ግድየለም ንገሪያቸው ስለልጆችሽ፡፡ እንግድነት የመጣህ ነህ፤ ቤተኛው እኔ ነኝ እየተባባሉ የሚዛለቁ ይመስልሻል? ግዴለም ሀገሬ አንድ ነገር አድርጊ እንጂ? ዝምታሽን ልሞግተው እማ፡፡

ክፉሽ መቼም ቢሆን አይመረጥም፡፡ ልጆችሽም መልካም ቢሆኑልሽ እመርጣለሁ፡፡ አሁን ግን መከፋቴ ባሰ መሰለኝ፡፡ ስላንቺ ያወሩ የመሰሉኝ ሰዎች ሁሉ ያሳምሙኛል፡፡ ከ80 በላይ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንዳሉ ንገሪያቸውማ፡፡ እኒህ ህዝቦች ተዋልደው እየኖሩ እንደሆነ ንገሪልኝማ፡፡ አይሆንም ካሉሽ ግን ሌላ ነገር እንዳይሆንብሽ እሰጋለሁ፡፡ መከፋትሽን እገምታለሁ፡፡ ለመኖር ግን እራስን መፈለግ ግድ የሚልበት ሁኔታ እንዳለ አለማውቅ፤ ልጆችሽ በእርሱ ተጠምደው እራሳቸውን ሲፈልጉ፤ አንድነትሽን የሰበኩ እየመሰላቸው ልጆቼ ብለሽ የምትናገሪላቸውን የሚያስቀይሙብሽን አንድ ካላልሽ ራስን በመፈለግ ውስጥ አንቺን እንዳያጡሽ እፈራለሁ፡፡ ታሪክ አዋቂ ነን ተብሎ የሚደሰኮረው፤ እሳት ሆኖ እንዳይበላሽ እፈራለሁ፡፡ ግን እኔ እልሻለሁ፤ ፖለቲካዊ ምልከታው የቱንም ያህል ይሁን ስፋቱ፤ አንቺነትሽን ለጥርጥር የሚዳርጉ የበረከቱ አዋቂዎችሽ ግን ብቅ ብለዋል፡፡ ትልልቅ ተብዬዎቹም ሆኑ ትንንሾቹ አዋቂዎችሽ ልብ ያሉት ያልመሰለኝ ነገር አለ፡፡ ሀገሬ በይ እንግዲህ ዝም አትበይ....ግድ የለም ዝም አትበይ.....እንደውም በዚህ ሙቀት ውስጥ ሀገርን ፍለጋ መሄድ ምኑ ላይ ይሆን ክፋቱ? ምክንያቱም ኢትዮጵያዬ አንደኛው ገጣሚ ልጅሽ እንዳለው፤
‹‹ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ
ሀገር ውስብስብ ነው ውሉ››
እኔ ግን እልሻለሁ ዝምታሽ የበዛ መሠለኝ፡፡ ቸር ያቆይሽ፡፡ እኔም ቸር መሆን ምኞቴ ነው፡፡ ስለሆነም ደህና ይግጠምሽ፡፡



አብርሃም ተስፋዬ

2014 ማርች 17, ሰኞ

ጉዞ ጎንደር (የተማሪነት) አጭር ማስታወሻ (ክፍል አንድ)

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ አመቱን ሊያከብር ነው፡፡ ልዩ ነው አቦ፡፡ እን£ን አደረሰን፡፡ ምናልባት ከቻልኩ እገኛለሁ፡፡ እርግጠኛ ነኝ በርካቶቻችን በዚህ ጊዝ እንደምንገናኝ አስባለሁ፡፡ የቀድሞ ተማሪዎች በዚህ ፕሮግራም ላይ ብትገኙ ደስ ይለኛል፡፡ እኔ በእርግጥም ከልቤ እሞክራለሁ፡፡ ስለሆነም ተውስ አለኝና ለምን ይህችን አልልም ብዬ ተነሳሁ፡፡ ከጉዞዬ ልጀምርና ስለጎንደር ከዚህ ጀምሮ በቻልኩትና ባስታወስኩት ብሎም በማስታወሻዬ ባገኘሁት ልክ እላለሁ፡፡ እነሆ የጎንደር ማስታወሻዬ አንድ ብሎ ቢጀምርስ፡፡

የዛሬ በርካታ ዓመት ወደ|ላ ብዬ የምናገረው ታሪክ ስለኖረኝ ደስ ብሎኛል፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ ከተወለድኩባት አዲስ አበባ 734 ኪሎ ሜትር ልንቀሳቀስ ነው፡፡ ጎዞ ጎንደር እነሆ ሊጀመር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የትምህርት ዕድል ነው፡፡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስጄ እድል እጣዬ ከጎንደር አድርሶኛል፡፡ በርካቶች በወቅቱ የት እንደሚደርሰን እንመርጥ በነበረበት በእዛ ሰዓት እኔ በእርግጥም ጎንደር የሚል ነገር አለመምረጤን አስታውሳለሁ፡፡ ከአዲስ አበባ ወጥቼ ስለማላውቅ አዲስ አበባ እንዲደርሰኝ በመመኘት፡፡

ነገር ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነ፡፡ በወቅቱ ባልሳሳት (በእኛ ግዜ ምደባ በጋዜጣ ይታወቅ ስለበር) ጥቅምት 18 ይመስለኛል ጋዜጣ ላይ ስሜን ያየሁት፡፡ ከዛ በፊት በነበሩት ተከታታ;ይ ሳምንታት በየቀኑ ስሜን ምዕራብ ሆቴል አጠገብ የነበረ ጋዜጣ አዙዋሪ ደንበኛዬ ጋር እየተመላለስኩ የማየው፡፡ ለጋዜጣ ማንበቢያ የምትሆነውን ሳንቲም ደግሞ አባቴ ይሰጠኝ ነበር፡፡ ለነገሩ ጋዜጣ አዙዋሪው፤ ቀደም ሲል አባቴ ይልከኝ ስለነበርና ፖሊስና እርምጃው የሚባለውን ጋዜጣ እየሄድኩ እገዛው ስለነበር አንዳንድ ቀን ሳንቲሙን አይቀበለኝም ነበር፡፡ እኔመ፣ ታዲያ ያቺን ሳንቲም አልተቀበለኝም ብዬ አልመልስም ነበር፡፡ ብቻ ያን ጊዜ፡፡

ከብዙ ጭንቀት ወዲያ ጥምቅምት 18 ቀን ወጣልኝና ስሜን በጋዜጣ አይሁት፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሚለው ውስጥ ዝርዝሬ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ብሎ አለሁበት፡፡ ስሜን በምን ፍጥነት እንዳየሁት አላውቅም፡፡ ግን አይሁት፡፡  በጣም ልዩ ስሜት ነበረው፡፡ ወላጅ አባቴን የት እንደደረሰኝ ለመንገር በየቀኑ ፈልጌ ግን ስላልወጣ አልነገረው ስለነበር፡፡ በውስጤ ምደባው አልፎኝ ይሆን እንዴ ብዬ መስጋቴ አልቀረም፡፡ ደርሼ ስመለስ አባቴ ይጠይቀኛል፡፡ አልወጣም የእኔ ብዬ እመልስለታለሁ፡፡ እንድጊህ ነገ ይወጣ ይሆናል ይለኛል፡፡ ይሆናላ እለዋለሁ፡፡ ስሜቴ እንዳይቀየር ያደርግ የነበረው ጥንቃቄ ዛሬም ድረስ ይገርመኛል፡፡ አባቴ በእርግጥም ልዩ ሰው ነበር፡፡ ሀይለኝነቱ ለእኔ ሲሆን አይሰራም ነበር፡፡ ብዙ ስሜቴ እንዲጎዳበት አይፈልግም ነበር፡፡ ስለሆነም ሁሌም ብርታቴ ነበር፡፡ የእናቴን ነገርማ አታንሱት፡፡ ስለእነርሱ ሌላ ጊዜ ብንጨዋወት ይሻላል፡፡

ብቻ እለቱ ደርሶ ስሜም ወጣ፡፡ ህዳር 27 መንቀሳቀሻ ቀን እንደሆነ ይናገራል ጋዜጣው፡፡ አስፈላጊ ያላቸውን ጉዳዮችም ያትታል፡፡ በጣም ምጥን ያለ አሪፍ ማስታወቂያ ነበር፡፡ ብርድልብስ፤ አንሶላ፤ የስፖርት ትጥ፤ ሌሎችም እንዲኖሩ ያዛል፡፡ ትራስ ግን እንዳት;ይዙ፤ ይትራስ ልብስ እንጂ ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡ (ለነገሩ ትራስ ይዞ የመጣም ነበር፡፡ የፍሬሽ ነገር)

ቤት ሄድኩ፡፡ እንደወጣ ተናገርኩኝ፡፡ ጎንደር እንደደረሰኝም ተናገርኩ፡፡ ይሄኔ ትንሽም ቢሆን ድንጋጤ በቤቱ ሰፈነ፡፡ ግን ግድ ነው፡፡ የሚ;ያስፈልጉ ነገሮች ተናገርኩ፡፡ በቃ፡፡ የጎንደር ልጅ ልሆን የቀረኝ ወር አካባቢ ነው፡፡ በመሀከሉ ግን ዩኒቨርሲቲው አዲስ ማስታወቂያ አወጣ፡፡ ወደ ታህሳስ 12 ተቀየረ፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ኮሜድያን ተስፋዬ ካሣ ያረፈበት ጊዜ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡  አንድ ሴት የኦሮምኛ ሙዚቀኛም ሙት አመት ታስቦ ይውል ነበር፡፡ እኒህ ክስተቶች ትውስ ይሉኛል፡፡
ጉዞ ጎንደር ታህሳስ 10 ቀን ሆነ፡፡ በዚሁ ዕለት ታዲያ መንገደኛ በመሆኔ አውቶብስ ተራ ከለሊቱ 11 ሰዓት ደርሻለሁ፡፡ መድረስ ብቻ አይደለም ነቃ ብያለሁም፡፡ ከት/ቤት ¹ደኞቼ ጋር ነኝ፡፡ እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ በመንገዱ ሁሉ ልናወራ፡፡ የእናቴንና የአባቴን የመጨረሻ ሽኝት አልረሳውም፡፡ ጉዞ ሆነ፡፡ በርካቶች ከወላጆቻቸው ጋር ሆነው ነበር፡፡ እኔና ¹ደኞቼ ግን ብቻችንን ነበርን፡፡ ስለሆነም ሄድን፡፡

ምሳ በላን፡፡ አሁንም ጉዞ፡፡ በነገራችሁ ላይ አባይ በረሃ ሁለት ሰዓት ወሰደብን፡፡ ተጠምዝዘን እዛው፡፡ ሄደን ሄደን እዛው፡፡ ምንም አይነቃነቅም፡፡ ከባድ ጉዞ፡፡ በእድሜም ልጅነት ስለነበረኝ ነገሮች ሁሉ ይገርሙኝ ነበር፡፡ ግራሞቴ ሳያበቃ ታዲያ ሌላ ግራሞት፡፡  መንገዱ ሰንሰለታማ ነው፡፡ ተራራ እና ገደሉን ማየት ከባድ ነው፡፡ ታንኮች በየቦታው አርጅተው ተጣመው ይታያሉ፡፡ የመኪናችን ረዳቶች (ሁለት ነበሩ) ማብራሪያ እየሰጡን ጉዞ ቀጥለናል፡፡ በውስጤ የቀሩ በርካታ ነገሮች ስላሉ በሌላ ጊዜ እንመለስበት ይሆናል፡፡ ነገር ግን የት ኖራ የሚባል ቦታ ያሉውን ሜዳማ መሬት አይቼ ጠየኩኝ፡፡ ሜካናይዝድ እርሻ እንደነበር ነገሩኝ፡፡ አሁንም ቢሆን ስል አሰብኩ፡፡ አሁን ያለበትን ሁኔታ አላውቅም፡፡ ነገር ግን በቅርቡ ወደ ጅግጅጋ ስሄድ፤ ከጅግጅጋ አልፎ ወደ ሶማሌ ላንድ ባለው መንገድ ላይ አውበሬ ይምትባል ቦታ እስከምደርስ ድረስ ያየሁትን ሜዳ አይቼ፤ ሜካናይዝድ እርሻን ስመኝ፤ የትኖራ ትዝ ብላኝ ነበር፡፡ ግሩም ነበር አቦ፡፡ ጎዞ ጎንደርን ጨርሰን ጎንደር ገብተና፡፡ ታህሳስ 11 ምሽት ላይ ጎንደር ገባን፡፡


በታሪኬ ለመጀመሪያ ጊዜ የሁለት ቀን ጎዞ ተጉዤ ጎንደር ገባሁ፡፡ ምሽት በመሆኑ፤ አብሮኝ የነበረው ወንድወሰን ለታ (ወንዴ) ማደሪያ እስኪፈልግ እቃ እንድጠብቅ ነግሮኝ ግለጋ ሄደ፡፡ ተመልሶ መጣ፡፡ አሁን ዕቃችንን ይዘን ወደ ማደሪያችን ልንሄድ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ መመስገን የሚገባቸው አካላት ነበሩ፡፡ ጉዞዋችን አድካሚ ቢሆንም፤ በወቅቱ የነበሩ ተማሪዎች እኛን ለመርዳት ያሳዩት ቁርጠኝነት ሀያል ነበር፡፡ ምስጋና ብቸራቸው ደስ ይለኛል፡፡ አደረጃጀቱ ምንም ይሁን ምን፤ እርዳታ ያስፈልገን ነበርና ተባብረውናል፡፡ እቃችንን ከማደሪያችን ካኖርን ወዲያ በወቅቱ ሞባይል ስላልነበረኝ በሰላም መድረሳችንን ለቤተሰብ አሳውቀን፡፡ ከዛም ጥቅልል ብለን ገብተን ተኛን፡፡ 

ሲነጋ ከነበረው ደግሞ እንቀጥላለን፡፡ የእዛ ሠው ይበለን፡፡

አብርሃም ተስፋዬ

2014 ማርች 7, ዓርብ

ኦቦ አለማየሁ አቶምሳ በተወለደ በ45 አመቱ አረፈ ስለተባለ!



‹‹ሲታመሙ መታከሚያ ገንዘብ እንኳ የሌላቸው እንደነ አለማየሁ አቶምሳ ያሉ ፖለቲከኞች አሉ›› የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ኦቦ አለማየሁ አቶምሳን አስመልክቶ ተናግረውት ነበር ተብሎ ሰሞኑን እየተነገረ ካለው የተወሰደ ነው፡፡

አንድ ሠው በተለይ እንደኛ አይነት ሀገር ላይ የስልጣን እርካብ ላይ ከወጣ በእርግጥም የሀብት መጠኑ እና የኩራት ጣሪው ገዘፍ እንደሚል ማሰብ አዳጋች አይመስልም፡፡ እንደው ለነገሩ አነሳሁት እንጂ፤ ሀገራዊና ክልላዊ ስልጣን ይቅርና የቢሮ ስልጣንም ስትኮፍሳቸው የምትከርም ግለሰቦች እናውቃለን፡፡ ይህንን ደግሞ ታዲያ በርካቶችን ሲያስከፋ ይስተዋላል፡፡ ኦቦ አለማየሁ ግን በዚህ ብዙም ሲታማ አልሰማሁም፡፡

ይልቁንም፤ ሙስናን ለመዋጋት የነበረውን ቁርጠኛ ፍላጎት ተከትሎ ሰዎች እንዳቄሙበት በሰፊው ይወራ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ዋጋ እንዳስከፈሉትና ይኸውም አሁን በተግባር የታየው የእርሱ ህልፈት የዚሁ ውጤት ስለመሆኑ በደንብ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ንግርቱ ታዲያ በተለይ ህልፈቱ ከተሰማበት ጊዜ ወዲህ በደንብ በርትቶ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡

ግለሰቦች ባሉበት ወቅት ማሞገስና ማመስገን የማይቀናን ለምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ግን ሁል ጊዜም ይገርመኛል፡፡ ሰዎች ሲያልፉ የምናጣው ነገር የሚታወሰን ያን ግዜ ነው መሠለኝ፤ ብዙ ነገር ማንሳት እንወዳለን፡፡  ሙት ላለመውቀስ ይሆን?
የኦቦ አለማየሁ ግን ይለያል፡፡ ስልጣን ላይ ወጣ፡፡ ሥራ ጀመረ፡፡ የተወሰኑ ታላላቅ ለውጦችን መከወን ጀመረ፡፡ ከዚያም ታመመ ተባለ፡፡ ህመሙ ደግሞ ከመመረዝ ጋር ተያያዘ፡፡ መመረዙ ደግሞ ስራ ካልተመቻቸው ግለሰቦች እንደሆነ በሰፊው ውስጥ ውስጡን ይነገር ነበር፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በደንብ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ግን በእርግጥ ከሆነ እውነት ለመናገር በጣም አሳዝኝም አሳፋሪም ነው፡፡ ሥራ ለምን ተሰራ በሚል እንዲህ ያለ ግፍ በአንድ ግለሰብ ላይ መሆኑም ያሳዝናል፡፡ ኦቦ አለማየሁ ለዚህ ካለፈም መስዋዕትነት ነው ብሎ መውሰድ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህንን መስዋዕትነት መክፈል ታላቅነት ነው ብዬም አምናለሁ፡፡ ስለሆነው ሁሉም ከማዘን ውጭ ምን ማድረግ ይቻል ይሆን፡፡

በሀገር ውስጥ ካሉት ባለስልጣናት ላይ የሚነሳው ሀሜት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በርካቶቹ በብዙ ነገር ይጠረጠራሉ፡፡ በርካቶችም ሲታሙ ሰምተናል፡፡ ኦቦ አለማየሁ አቶምሳ ግን በዚህ መልክ ስለመታማቱ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እንደውም በጣም በብርቱ ሲታዘንለት ይሰማል፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም መሞቱን ተከትሎም ቀደም ሲል በህመሙ ወቅት ሲወራ የነበረው ነገር ጎልቶ እየተሰማ ነው፡፡ 45 ዓመት እድሜው የተቀጨው ኦቦ አለማየሁ ከህመሙ ጋር እየታገለ ሀገሩንና ህዝቡን ለማገልገል የነበረው ቁርጠኝነት መልካም የሚባል እንደነበር እየሰማን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከአንድ ምርጥ መሪ የሚጠበቅ ነገር መሆኑን ለመገንዘብ ነብይነት አይተይቅም፡፡ ኦቦ አለማየሁ ማለፉ ሲነገር ከነበረው የህመም ስሜትና ስቃይ አንጻር ከታየ ከእርሱ በግል እረፍት ይመስለኛል፡፡ ሀገርና ህዝብ ግን እንዲህ ያለውን መልካም ሰው ማጣታቸው በእርግጥ ያስቆጫል፡፡ ግን እንዲህ ያለው ነገር እየተሰማ ዝም አይባልም፡፡

ስለሆነም መንግስት ( የክልሉም ይሁን ፌዴራል መንግስት) ስለነገሩ አንዳች አርግጠኛ ነገር ማጣራትና ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ይህ አካሄድ ለሌሎች ባለስልጣናትም አደገኛ ስለሚሆን፡፡ ስለሆነም ቢታሰብበት መልካም ይመስለኛል፡፡ አንድም ነገርየው ሌሎች ባለስልጣናት እንዲፈሩ ያደርጋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳች ነገር በውስጡ ስለሚኖር ተቀብሮ እንዲቀር ምክንያት መሆኑን መታዘብ ይቻላል፡፡ በመሆኑም ነው ታዲያ ጉዳዩ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ ቢሆን መልካም የሚሆነም፡፡ ባይሆን እንካ ለመገማገሚያነት መቅረብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ቢያንስ ወሬው በዚህ ልክ ለምን እንዲወራ እንደሚፈለግ መጣራት አለበት፡፡ መቼም ወሬው ዝም ብሎ ያለአንዳች ፍንጭ ሊወራ እንደማይችል በመጠርጠር ነው ይህንን ማለቴ፡፡ ቅያሜ እንደማይኖራችሁም በማሰብም ጭምር፡፡ (በእርግጠኝነት አትቀየሙኝም አይደል?)

ስለሆነም ኦቦ አለማየሁን ልለው ወደድኩ፡፡ ኦቦ አለማየሁ ሆይ በእርግጥም በዚህ ልክ ተወዶ ማለፍ መልካም ነው፡፡ ስለሰራሀቸው ስራዎች፤ ስለጥሩነት፤ ለጥሩ ነገርና ጥሩ ነገር ለመስራት ስለከፈልከው ዋጋ ሁሉ ክብር ይገባሀል፡፡ ነብስህን እግዚአብሔር በአጸደገነት ያኑራት፡፡ የምትወደው ህዝብህና ሀገርህም መልካሙን ሁሉ ይግጠማቸው፡፡
ሁነቱ ግን የፈጠረብኝ ስሜት ከባድ ነበር፡፡ ቀደም ሲል የኢህዴድ አመራር ለውጥ፤ የእርሱ በእራሱ ፈቃድ መልቀቂያ መጠየቁና መሠል ክዋኔዎች ሲገርሙኝ ሰንብተዋል፡፡ ታሪክ ሰሪው በእራሱ ፈቃድ መልቀቂያ ጠይቆ አረፈ፡፡ ለማንኛውም በእኔ አቅም ሊባል የሚችለውን ልበል መሠለኝ፡፡ በድጋሚ ነብስ ይማር፡፡ ለሶስቱ የስጋ ልጆችህ ለቤተሰብህና ለሌሎችም ሁሉ መጽናናትን ተመኘሁ፡፡



አብርሃም ተስፋዬ

2014 ማርች 2, እሑድ

ደግሞ ምርጫ መጣ?!

ለነገሩ የምርጫ ሰሞን ፖለቲከኞቻችን እነሆ መነቃቃት እንዲይዛቸው በርካቶች እየታተሩላቸው ነው፡፡ ቀስቃሽ የሚሹ ፖለቲከኞቻችን ዛሬም ሌላ መነቃቂያ እና የሚያነቃ ይፈልጋሉ መሰለኝ፡፡
እሹሩሩ የሚላቸው፡፡ ወፌ ቆመች የሚላቸው የሚሹ ይመስላሉ፡፡ ይህ ታዲያ ለመቼውም ቢሆን የሚጠቅም አልመሰለኝም፡፡ ስለሆነም ልላቸው ወደድኩ፡፡ ሁላችሁም ብትሆኑ የት ገባችሁ?
እኔ በደንብ ስለማውቀውና በኢትዮጵያ ታላቅ ነው ብዬ የማስበውን የዴሞክራሲያዊ ክዋኔ (ተዓምር) ሁሌም እናፍቀዋለሁ፡፡ በተለይም በወቅቱ እኔ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበርኩ በመሆኑ፡፡ 1997 ዓ.ም. ለእኔ ልዩ ነበር፡፡ የነጻነት አመት ይመስለኛል፡፡ በፖለቲካ ትርክት ውስጥ ኢትዮጵያ ታላቅ ነገር አየች ከተባለ ለእኔ ከዋነኞቹ ታሪካዊ ትርክቶች መካከል የወቅቱ የምርጫ ሂደት አንዱ ነበር ለማለት እወዳለሁ፡፡ እኔ በነበርኩበት ዩኒቨርሲቲም ታዲያ የነበረው ድባብ ዛሬም ድረስ ትውስ ይለኛል፡፡ እውነት ለመናገር ክርክራችን ልዩ ነበር፡፡ ለሁሉም ወንድሞቻችን ክብር አለኝ፡፡
በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የነበሩ ከተለያዩ ብሔሮችን ብሔረሰቦች የተውጣጡ ተማሪዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ልዩነት ላይ ተንተርሰው ያሳዩ የነበሩት ነገር ዛሬም ድረስ ትርጉም አለው ለእኔ፡፡ በተለይ በጊዜው በርካታ ነገሮች ሲከወኑ እንመለከት ነበርና ግ-ር-ም ይለኛል፡፡ በተለይ ደግሞ በተለያዩ የወቅቱ ፓርቲዎች መሪዎች የሚሰጡትን መግለጫ እያሳደዱ ማዳመጥ ትንታኔ መስጠትና መከራከር ልዩ መለያችን ነበር፡፡ በግቢው ውስጥ በፖለቲካ ልዩነት ይነሱ የነበሩ አንዳንድ አላስፈላጊ ነገሮች የነበሩ ቢሆንም፤ ሁሉም ለአመለካከቱ ይከፍል የነበረው ዋጋ ልዩ ነበር በእነዚህ ጊዜያት ታዲያ በወቅቱ የነበሩት ወንድሞቼና እህቶቼ ትዝ ይሉኛል፡፡ በተለይ እንዲህ ምርጫ አጀንዳ ለመሆን በሚዳዳባቸው ጊዜያት ሁሉ ትውስ ይለኛል፡፡
የአመለካከት ልዩነታችን እንዳለ ሆኖ፤ ደጋግ ወንድሞቻችን እንደነበሩ ሁሉ አሳልፎ መሥጠት የሚወዱ አንዳንድ ተማሪ ወንድሞቻችን እንደነበሩም አስታውሳለሁ፡፡ ነገር ግን ሁሉም አለፈ፡፡ ይህ ሁሉ በሆነ ግዜ ታዲያ በርካታ ሁነቶች ታልፈው ለዛሬ በቅተናል፡፡ በወቅቱ በነበሩ ግርግሮች መነሻነት እስር ቤት ተገብቶ የተገባበት፤ ጥቁር መልበስም የተከለከለበት ጊዜ ሁሉ ነበር፡፡ የፓርቲ መሪዎች ምግብ አልበላንም ባሉን ግዜ ጮኸናል፡፡ ከለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ብርድ ላይ እንድንቀመጥ ተፈርዶብን በብርድ ተቀጥተናል፡፡ ምናልባት ምርጡ ጊዜ ነው፡፡ በወቅቱ ያሳለፍናቸውን ሁነቶች ዛሬ ላይ ሆኖ ማሰብ ደስ የሚል ነገር ይፈጥራል፡፡ ግና ሁሉም አለፈ ዛሬ፡፡
ለማንኛውም በቀጣይ ሁነቶቹንና ሌሎችንም አንስተን እንጨዋወታለን፡፡ ግን ደግሞ ምርጫን አስመልከቶ ከተቀለዱ ቀልዶች መካከል አንዱ ትውስ አለኝ፡፡ የሰማውን የነገረኝ አንድ ወዳጄ ነው፡፡  
በቀደመው ግዜ ከነበሩት ምርጫዎች በአንዱ ሆነ ያሉትን እያነሳ ይነግረኛል፡፡ በመሠረቱ ምርጫው እየተካሄደ ነው፡፡ ከዚያም አንደኛው መራጭ መርጦ ይወጣል፡፡ ምርጫውን አጠናቆ ካበቃ ወዲያ ወደጉዳዩ ለማቅናት መንገድ ሲጀምር ሌላ ወዳጁን ያገኝና ማንን እንደመረጠ በጠየቀው ግዜ ሰውየው ተቃዋሚዎችን መምሩጡን ይነግረዋል፡፡ ሆኖም፤ ሰውየው ለምን ኢህአዴግን አልመረጥክም ብሎ ይሞግተዋል፡፡ ከብዙ ክርክር ወዲያ እርሱም በቃ እንግዲህ ምን ላድርግ አንድ ግዜ መርጫለሁ፤ አሁን ምን ማድረግ አለብኝ ኢህአዴግን ለመምረጥ ብሎ ይጠይቃል፡፡ ወዳጁ መለሰለት፡፡ ለምን ሄደህ ምርጫ ታዛቢዎችን አታማክራቸውም ብሎ፡፡ ወዲያውም ሄደ፡፡ ከዚያም ለታዛቢዎቹ የሆነውን አስረዳቸው፡፡ ምርጫውን ማስተካከል እንደሚፈልግ፡፡ ነገር ግን እንዴት ማድረግ እንዳለበት እንዳላወቀ፡፡ ምን እናድርግ ታዲያ ብለው ጠየቁት አሉ፡፡ ሰውየውም ለማስተካከል አንድ እድል ስጡኝ ማለት፡፡ ይሄኔ አንደኛው ታዛቢ ፈጠን ብሎ ይመልሳል፡፡ ለማንኛውም ለሌላ ግዜ እንዳትሳሳት፡፡ ለዛሬው ቀድመን አስተካክለንልሃል፡፡
ምርጫችንን አውቆ ቀድሞ ከስህተታችን የሚያስተካክለን ይስጠን ብለን ብንጸልይስ? ጸሎታችንን ሰምቶ አምላክ ቢሰጠንስ? እውነት ለዚህ የተዘጋጀ ፓርቲ ይኖር ይሆን?

ሠላም ሁኑ!

አብርሃም ተስፋዬ

ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁነኛ ሠው ማነው?

ፖለቲካችን እነሆ ዝብርቅርቅ እንዳለ መሬት ሳይነካ፤ እንደተናጠ ምርጫ ደረሰ፡፡ ሁሉም ለእራሱ ግነት ሲፈልግ እነሆ ኢትዮጵያም እንደሀገር እንደቀጠለች አለች፡፡ ነገር በተከወነ ቁጥር ሁሉም ጀብድ ነው ብሎ ያሰበውን ወደእራሱ እንደጎተተ እነሆ ኢትዮጵያም እንደሀገር እንደቀጠለች አለች፡፡ እኛ ነን፤ እኛ ነን እንዳሉ እነርሱ ይሁኑ አይሁኑ ሳይለይ፤ እነሆ ኢትዮጵያም እንደሀገር እንደቀጠለች አለች፡፡ ኢትዮጵያማ ትቀጥላለች አስቀጣይዋ ግን ለማስቀጠል የሚበጅና የሚችል እንዲሆንላት ጥንነቃቄና ብልኸት ያሻው ይሆናል እንጂ፤ ኢትዮጵያማ እንደጉድ ትቀጥላለች፡፡
ለጉድ የፈጠረን እንዳልነው ሁሉ ለጉድ የፈጠራት ሀገር አለችን መሠለኝ፡፡ ስለሆነም ትቀጥላለች፡፡ በይ ኢትዮጵያ ቀጥይ፡፡ በእነዚህ ሁነቶች ሁሉ ታዲያ ፖለቲከኞቻችን ሁነኛ ነን እያሉ ማንነታቸውን ከፍ ከፍ እንድናደርግና እንድናወድስ መንገዱን ለእራሳቸው መጥረጋቸው ይታያል፡፡ በመሠረቱ ለፖለቲካ ተሳትፎና ግልጽነት ትንሽም ቢሆን ቀረት የምንለው ነገር ቢኖርም፡፡ ቀደም ሲል የነበሩት አገዛዞች ግልጽነታችንን እንደዜጋ በተለይም እንደፖለቲከኛ ዜጋ የፈተኑት ይመስለኛል፡፡ ድምጽን ከፍ አድርጎም መናገር ዋጋ ሊያስከፍል ይችል እንደነበር ሲነገር ሰምተናል፤ አንብበንማል፡፡
በዛ ወቅት የነበሩ ፖለቲከኞችም ታዲያ በየወቅቱ በሚጽፉዋቸው መጣጥፎች፣ በሚሰጡዋቸው ቃለ-መጠይቆች፤ ብሎም በሚያሳትሙዋቸው መጻህፍት (አንዳንዶች ኑዛዜ ነው ይሉታል) ማንነታቸውን ለማሰማመር ሲጥሩ ይስተዋላል፡፡ ሁሉም በእነርሱ አገላለጽ መልካም አድርገዋል፡፡ ይህ ከሆነ ታዲያ ችግሩ ከምን ላይ ያርፋል የሚል ጥያቄ ከተነሳ፤ ማሳበቢያ ስለማይጠፋ፤ ስበቡ ሌላኛው ላይ እንዲያርፍ ይደረግና ለተወሰነ ግዜ እረፍት ለመውሰድ ይሞከራል፡፡ በመሠረቱ ግን ሁነኛ ሠው ያጣው ፖለቲካችን ለምን እንዲህ ሊሆን እንደቻለ በርካታ መላምቶች ቢሰጡም፤ በዋነኝነት ፖለቲከኞቻችን እራሳቸው ሁነኛው ሰው ማን እንደሆነ ማሰብ የሚፈቅዱ አይመስለኝም፡፡
ሁሉም ስለሀገር ያነሳሉ፡፡ ሀገር ታዲያ በምን መልኩ ነው የተሻለ መስተጋብር የሚኖራት ለሚለው ጥያቄ መልስ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ቢኖራቸው እመርጣለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በሚል ቃል ሽፋን ውሸት የሚነዙ አይጠፉም፡፡ በርካቶች (ኢትዮጵያ የሚለውን የሚጠቀሙ ፓርቲዎችን ጨምሮ) በብሔር ስም የሚንቀሳቀሱትን ፓርቲዎች ብሔርን ማዕከል ያደረጉ በማለት ለሀገር አንድነት ስጋት አድገው ሲያቀርቡዋች ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን ይህ አመለካከት መቀየር እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ ዜጎች በየትኛውም አግባብ ቢሆን ሊሰባሰቡና ሊደራጁ እንደሚችሉ፤ ብሎም ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል የሚጠቀሙት ፖለቲከኞች ሁሉ እውነተኞችና፤ ብሔርን የሚጠቅሱት የማይጠቅሙ ተደርገው መወሰድ ያለባቸው አይመስለኝም፡፡
ሁነኛውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰው ፍለጋ ላይ ያለን ይመስለኛል፡፡ በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያዊያን በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ይህንን ሰው መፈለግ ላይ መሆናቸውን መገመት አዳጋች አይመስለኛም፡፡ ለዚህም ሊሆን ይችል ይሆናል፤ ፓርቲዎቹ እንዲህ የበረከቱትና በዛው ልክም አባላት (የእውነትም የውሸትም ሊሆን ይችላል) የሚኖራቸው፡፡
ከሰሞኑን ታዲያ የሌንጮ ወደ ሀገር ለመመለስ መወሰን ከባድ ውዝግብ ማስነሳቱን ተከታትያለሁ፡፡ በመሠረቱ ሌንጮ በበርካቶች ተናግሮ የማሳመን ብቃት ያለው እንደሆነ የሚነገርለት፤ ጥሩ የማየት አቅም ያለውና ነገሮች በጥልቀት ለመመርመር ብቁ እንደሆነ የሚመሰከርለት ግለሰብ ቢሆንም፤ አንዳንዶች ደግሞ ቀደም ሲል ከነበረበት የኦነግ አመራርነት ሥልጣን ጋር በተያያዘ ሲኮንኑት ይስተዋላል፡፡ በዚህም አልን በእዛ ሌንጮ መምጣቱ እርግጥ ይመስላል፡፡ አዲሱን ፓርቲውን (የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ወይም በምህጻር ኦዴግ) ይዞ በሀገር ቤት ትግሉን በአዲስ መልክ ለመቀላቀል ያሰበም ይመስላል፡፡
ለዚሁም በርካቶች ሲደሰቱ፤ ሌሎች በርካቶችም ስጋት አድሮባቸዋል፡፡ የተደበላለቀ ስሜት የተሰማቸውም እንዳሉ ይስተዋላል፡፡ ሌንጮ ከቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ጋር (ነገሮች ክርር ብለው መስመር ባልለቀቁበት ዘመን) ጥሩ ግንኙነት እንደነበራቸውም ይወራል፡፡ ዛሬም ላይ ታዲያ ያሉት ጠ/ሚኒሰትር ኃ/ማርያም ጉዳዩን እንደመንግስት እንደሚመረምሩትና ውጤቱም ወደፊት እንደሚታይ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ አሳውቀውናል፡፡
ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አዳጋች ቢሆንም፤ የሌንጮን ወደሀገር ለመመለስ እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት ላየና በዚህም መሀከል እየተስተጋባ ካለው ሁነት ጎን፤ ምናልባት ሌንጮ ዳግም ሁነኛ ሰው ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን› ብዬ ለመጠየቅ ይዳዳኛል፡፡ ለነገሩ ምናልባት ድርድሩ ተሳክቶ ወደሀገርቤት የሚመጣ ከሆነና እንቅስቃሴውን በይፋ ሲጀምር የምናየው ይሆን ይሆናል፡፡
የበርካቶች ግምት እንዳለ ሆኖ፤ ወደፊት የምናየው ስለመሰለኝ ይህንን አልኩ፡፡

ሠላም ሁኑ!