2014 ማርች 7, ዓርብ

ኦቦ አለማየሁ አቶምሳ በተወለደ በ45 አመቱ አረፈ ስለተባለ!



‹‹ሲታመሙ መታከሚያ ገንዘብ እንኳ የሌላቸው እንደነ አለማየሁ አቶምሳ ያሉ ፖለቲከኞች አሉ›› የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ኦቦ አለማየሁ አቶምሳን አስመልክቶ ተናግረውት ነበር ተብሎ ሰሞኑን እየተነገረ ካለው የተወሰደ ነው፡፡

አንድ ሠው በተለይ እንደኛ አይነት ሀገር ላይ የስልጣን እርካብ ላይ ከወጣ በእርግጥም የሀብት መጠኑ እና የኩራት ጣሪው ገዘፍ እንደሚል ማሰብ አዳጋች አይመስልም፡፡ እንደው ለነገሩ አነሳሁት እንጂ፤ ሀገራዊና ክልላዊ ስልጣን ይቅርና የቢሮ ስልጣንም ስትኮፍሳቸው የምትከርም ግለሰቦች እናውቃለን፡፡ ይህንን ደግሞ ታዲያ በርካቶችን ሲያስከፋ ይስተዋላል፡፡ ኦቦ አለማየሁ ግን በዚህ ብዙም ሲታማ አልሰማሁም፡፡

ይልቁንም፤ ሙስናን ለመዋጋት የነበረውን ቁርጠኛ ፍላጎት ተከትሎ ሰዎች እንዳቄሙበት በሰፊው ይወራ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ዋጋ እንዳስከፈሉትና ይኸውም አሁን በተግባር የታየው የእርሱ ህልፈት የዚሁ ውጤት ስለመሆኑ በደንብ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ንግርቱ ታዲያ በተለይ ህልፈቱ ከተሰማበት ጊዜ ወዲህ በደንብ በርትቶ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡

ግለሰቦች ባሉበት ወቅት ማሞገስና ማመስገን የማይቀናን ለምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ግን ሁል ጊዜም ይገርመኛል፡፡ ሰዎች ሲያልፉ የምናጣው ነገር የሚታወሰን ያን ግዜ ነው መሠለኝ፤ ብዙ ነገር ማንሳት እንወዳለን፡፡  ሙት ላለመውቀስ ይሆን?
የኦቦ አለማየሁ ግን ይለያል፡፡ ስልጣን ላይ ወጣ፡፡ ሥራ ጀመረ፡፡ የተወሰኑ ታላላቅ ለውጦችን መከወን ጀመረ፡፡ ከዚያም ታመመ ተባለ፡፡ ህመሙ ደግሞ ከመመረዝ ጋር ተያያዘ፡፡ መመረዙ ደግሞ ስራ ካልተመቻቸው ግለሰቦች እንደሆነ በሰፊው ውስጥ ውስጡን ይነገር ነበር፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በደንብ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ግን በእርግጥ ከሆነ እውነት ለመናገር በጣም አሳዝኝም አሳፋሪም ነው፡፡ ሥራ ለምን ተሰራ በሚል እንዲህ ያለ ግፍ በአንድ ግለሰብ ላይ መሆኑም ያሳዝናል፡፡ ኦቦ አለማየሁ ለዚህ ካለፈም መስዋዕትነት ነው ብሎ መውሰድ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህንን መስዋዕትነት መክፈል ታላቅነት ነው ብዬም አምናለሁ፡፡ ስለሆነው ሁሉም ከማዘን ውጭ ምን ማድረግ ይቻል ይሆን፡፡

በሀገር ውስጥ ካሉት ባለስልጣናት ላይ የሚነሳው ሀሜት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በርካቶቹ በብዙ ነገር ይጠረጠራሉ፡፡ በርካቶችም ሲታሙ ሰምተናል፡፡ ኦቦ አለማየሁ አቶምሳ ግን በዚህ መልክ ስለመታማቱ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እንደውም በጣም በብርቱ ሲታዘንለት ይሰማል፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም መሞቱን ተከትሎም ቀደም ሲል በህመሙ ወቅት ሲወራ የነበረው ነገር ጎልቶ እየተሰማ ነው፡፡ 45 ዓመት እድሜው የተቀጨው ኦቦ አለማየሁ ከህመሙ ጋር እየታገለ ሀገሩንና ህዝቡን ለማገልገል የነበረው ቁርጠኝነት መልካም የሚባል እንደነበር እየሰማን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከአንድ ምርጥ መሪ የሚጠበቅ ነገር መሆኑን ለመገንዘብ ነብይነት አይተይቅም፡፡ ኦቦ አለማየሁ ማለፉ ሲነገር ከነበረው የህመም ስሜትና ስቃይ አንጻር ከታየ ከእርሱ በግል እረፍት ይመስለኛል፡፡ ሀገርና ህዝብ ግን እንዲህ ያለውን መልካም ሰው ማጣታቸው በእርግጥ ያስቆጫል፡፡ ግን እንዲህ ያለው ነገር እየተሰማ ዝም አይባልም፡፡

ስለሆነም መንግስት ( የክልሉም ይሁን ፌዴራል መንግስት) ስለነገሩ አንዳች አርግጠኛ ነገር ማጣራትና ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ይህ አካሄድ ለሌሎች ባለስልጣናትም አደገኛ ስለሚሆን፡፡ ስለሆነም ቢታሰብበት መልካም ይመስለኛል፡፡ አንድም ነገርየው ሌሎች ባለስልጣናት እንዲፈሩ ያደርጋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳች ነገር በውስጡ ስለሚኖር ተቀብሮ እንዲቀር ምክንያት መሆኑን መታዘብ ይቻላል፡፡ በመሆኑም ነው ታዲያ ጉዳዩ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ ቢሆን መልካም የሚሆነም፡፡ ባይሆን እንካ ለመገማገሚያነት መቅረብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ቢያንስ ወሬው በዚህ ልክ ለምን እንዲወራ እንደሚፈለግ መጣራት አለበት፡፡ መቼም ወሬው ዝም ብሎ ያለአንዳች ፍንጭ ሊወራ እንደማይችል በመጠርጠር ነው ይህንን ማለቴ፡፡ ቅያሜ እንደማይኖራችሁም በማሰብም ጭምር፡፡ (በእርግጠኝነት አትቀየሙኝም አይደል?)

ስለሆነም ኦቦ አለማየሁን ልለው ወደድኩ፡፡ ኦቦ አለማየሁ ሆይ በእርግጥም በዚህ ልክ ተወዶ ማለፍ መልካም ነው፡፡ ስለሰራሀቸው ስራዎች፤ ስለጥሩነት፤ ለጥሩ ነገርና ጥሩ ነገር ለመስራት ስለከፈልከው ዋጋ ሁሉ ክብር ይገባሀል፡፡ ነብስህን እግዚአብሔር በአጸደገነት ያኑራት፡፡ የምትወደው ህዝብህና ሀገርህም መልካሙን ሁሉ ይግጠማቸው፡፡
ሁነቱ ግን የፈጠረብኝ ስሜት ከባድ ነበር፡፡ ቀደም ሲል የኢህዴድ አመራር ለውጥ፤ የእርሱ በእራሱ ፈቃድ መልቀቂያ መጠየቁና መሠል ክዋኔዎች ሲገርሙኝ ሰንብተዋል፡፡ ታሪክ ሰሪው በእራሱ ፈቃድ መልቀቂያ ጠይቆ አረፈ፡፡ ለማንኛውም በእኔ አቅም ሊባል የሚችለውን ልበል መሠለኝ፡፡ በድጋሚ ነብስ ይማር፡፡ ለሶስቱ የስጋ ልጆችህ ለቤተሰብህና ለሌሎችም ሁሉ መጽናናትን ተመኘሁ፡፡



አብርሃም ተስፋዬ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ