2018 ዲሴምበር 8, ቅዳሜ

‹ሀገርና ጩኸት›


ዝም የምንልበት ሳይሆን የምንወያይበት ጊዜ ነው

ሀገር የማቅናት ፈተና ውስጥ ነን፡፡ መንግስት በአንድ በኩል አረገብኩ ሲል በሌላ በኩል ድምጽ አለ፡፡ እዚህ ሰፈር ሲሰክን፤ እዚያ ሰፈር ይደፈርሳል፡፡ ሀገሬ እንዲህ ባለው ሙቀት እየታመሰች አለች፡፡ እውነት ነው ለአመታት በዚህ አዙሪት ውስጥ ነው ያለፈችው፡፡ የሥልጣን ሽግግር ከተካሄደ ወዲያም ቢሆን እዚህም እዚያም ያለው ድምጽ አንዳንዴም ሲያውክ፤ አንዳንዴም ሲያበሳጭ፤ አንዳንዴም ሲያሳስብ፤ ብቻ ባለብዙ መልክ ሆኖ ቀጥሎ ይስተዋላል፡፡

ሀገር በጩኸት ብትፈርስ፤ ኢትዮጰያ የኢያሪኮን ታሪክ በደገመችው ነበር፡፡ አዋቂ የበዛበት ዘመን ሆኗል፡፡ በተፈለጉ ዘመን ያልነበሩ ‹ምሁራን› አሁን በየቴሌቪዥን መስኮቱ ይታያሉ፤ ትንታኔያቸው ሀገርን በ‹እውቀት› ሙላት ሊግቱ ሲታትሩ ይስተዋላሉ፡፡ የመታመን መጠናቸውን ለጊዜው ለመመዘን ባልችልም፡፡ ሀገር እንዲህ ባለው ጊዜ ሁነኛ ተዓማኒ የመረጃ ምንጭ ቢያስፈልጋትም፤ ከግልብ የሚነዱ በርካቶች አሉና የእነዚሁ ጋላቢዎች ቁርስ ራት መሆናቸው ግድ ነበር፤ ነውም፡፡

በተለይም እንዲህ ባለው ወቅት ሚዲያው ያለው ሚና ለክፉም ለደግም ቅርብ ነውና በርካቶቹ ጉዳዮች ጥንቃቄ ከመፈለግም ባሻገር ትዕግስት የሚፈትኑ አይነት እንዳይሆኑ በአንክሮ መከታተል ያሻል፡፡ ለህብረተሰቡ አጀንዳ በመቅረጽ የህዝብ ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች ላይ በትኩረት መስራት የሚገባበት ጊዜ ላይ ያለን ይመስለኛል፡፡ ሚዲያው ሀሳቦች የሚንሸራሸሩበት፤ የህዝቡ መንፈስና እሳቤዎች የሚዳሰሱበት እንዲሆኑ ምኞቴ ነበር፡፡ በተለይም በብሮድካስት ሚዲያው አካባቢ ያለው ነገር ከዚህ አንጻር ሲቃኝ አንድም ሚዲያዎቹን የሚመሩ አካላት አልያም ‹ባለሙያ› ነን የሚሉትና ፕሮግራሞች የሚያዘጋጁና የሚያቀርቡት፤ ዜናዎችን የሚያዘጋጁና የሚተነትኑት ግለሰቦች በእርግጥም ሙያውን ስለማወቃቸውና ስለመረዳታቸው ማጠየቅ ግድ ነው፡፡

ተንታኝ በዝቶ ይስተዋላል፡፡ ሁሉም ሰው ፖለቲከኛ ለመሆን ከመጣጣሩ በላይ ጉዳዮችን ለመተንተን የሚመርጠው ርዕሰ-ጉዳይ ከማንነቱ ጋር መነሻ ባደረገ መልኩ መሆኑን ለማስተዋል ረዥም ጊዜ ማጤን አይጠይቅም፡፡ በርካቶች በዚህ የማንነት ጉዳይ ተጠልፈው ሲወድቁ ይታያል፡፡ በ‹ማናለብኝነት› መንፈስ በርካታ ተከታዮች አሉኝ፤ አልያም ብዙዎች ያነቡኛልና ያዳምጡኛል በሚል ‹ፈሊጥ› በርካቶች ሳይታሰብ ጠርዝ ላይ በአንዳች የ‹ግል› አጀንዳ ሳይቀር ቅርቃር ገብተው ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህኛው ቅርቃር እኒህን ግለሰቦች ለማላቀቅ ፈተና በዝቶ ይስተዋላልም፡፡

ጎራ ለይቶ መጠዛጠዙ በርክቶ ይስተዋላል፡፡ የሰው ልጅ ጉዳት ሳይሆን፤ የተጎዳው አካል ከየትኛው ወገን እንደሆነ ማጣራቱ ላይ አበርትቶ ሲሰራ ይስተዋላል፡፡ የተጎጂዎችን ጾታ ሳናውቅ ብሔራቸው ይነገረናል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው በምን መልክ መጠቀም እንደሚገባን የሚሰብኩ የሚመስሉን ግን ደግሞ ከምክራቸው ስሜት ሳንወጣ እነርሱ ራሳቸው በየገጾቻቸው ጠርዝ የረገጡ ጉዳዮችን የሚግቱን በርክተዋል፡፡

ለበርካታ ጊዜያት በተለይም የብሔር ብሔረሰቦችን ጉዳይ የሚያነሳውን አካል ጠባብና ዘረኛ፤ የአንድነትን ጉዳይ የሚያነሱ አካላትን ጉዳይ ደግሞ ‹የአንድነት ኃይል› እየተባሉ ሲፈረጁ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ትርጓሜ ውስጥ በርካታ ሠዎች ለመካተት ሲሹ መስተዋሉ አይካድም፡፡ በተግባር የሆኑት እና የኖሩት ግን ጥቂቶች ቢመስሉም፡፡

አንድነት ማለት ሀገራዊ መሠረት ባደረጀ ሁናቴ ልዩነቶችን አቻችሎ በሚያግባቡና በሚያመሳስሉ ጉዳዮች ላይ የበለጠውን መልካም ነገር ጨምሮ ለመኖር የሚደረገው ጥረት ሲሆን፤ አንዳንድ ይህንን አንድነት የሚባል ሀሳብ ባልተገባ ሁነት በመተርጎም ወደ አንድ አይነትነት ለመተርጎምና፤ በተግባርም ለማመለካት ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡

ኢትዮጵያ በመሠረቱ ያሏትን በርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እና ህዝቦች፣ ባህሎችና ቅርሶች፣ ወግና ልማዶች፣ ብሎም በርካታ ሁነቶችን ላስተዋለ ሰው፤ በተለይም ባለፉት በርካታ መቶና ሺህ አመታት ነገስታት የነበራቸውን ታሪክ ወደኋላ መለስ ብሎ ለተመለከተ፤ ህዝቦች በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት እንዲገብሩ ሆነዋል ተብሎ የተጻፉ ታሪኮቻችን በተለይም ባለፉት ሶስት አስርት አመታት የተጫናቸው አቧራ አራግፈው በአዲስ መልክ ሲተየቡ ተመልክተናል፡፡

በእነዚህም ታሪኮች ላይ መግባባት ላይ መድረስ ተስኖናል፡፡ ተመሳሳይ የሚመስልም ምልከታዎችን ማግኘት በራሱ ከባድ ሆኖብናል፡፡ የአንድ እንኳ ቢቀር የጋራ የምንለው የምናከብረው ባህል፤ ቀግና ልማድ ብሎም ጀግና ማውጣት ተስኖናል፡፡ ምሁራን የሚባሉትም ግለሰቦች ቢሆኑ፤ ከአንድ ሰፈር ቅርቃር ውስጥ በተቻላቸው መጠን ድምጽና ሙገሳ ለማግኘት ለብሔር ማንነታቸው (በተለይም የራሳቸውን ስምና ዝና ፍለጋ፤ አልያም በአካባቢያቸው ሰው ተቀባይነትን በማግኘት ወደአደባባይ ለመውጣት በማሰብ) ሲታገሉ ተስተውሏል፡፡ የጋራ የሚባለውን ጉዳይ እርግፍ አድርጎ በመተው ልዩነቶች ላይ በብርቱ ሲሰራ ታይቷል፡፡

መንግስትም በተለያዩ አጋጣሚዎች ይህንኑ ሲሰራ ተስተውሎ ሰንብቷል፡፡ ኢትዮጵያዊያንም ባሉበት ሁሉ ሀገርም ውስጥ ይሁን በሌላ ቦታ ከአንድነታቸው ይልቅ ልዩነቶቻቸው ላይ ሲወያዩና በዚሁ መንገድ ሲፈራረጁ ሰንብተዋል፡፡ ሆኖም፤ ይህንኑ ልዩነት ለዘመናት ሲደሰኮር ቢከርምም ማስታረቂያ እና መቻቻያ መንገዱን የሚያሳይ ጠፍቶ እርሱን በማስፋት ሂደት ውስጥ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ምናልባት ንጹህ ነኝ ሊል የሚችል ካለ ይገርመኛል፡፡ ፖለቲከኞቹም ቢሆኑ አጀንዳ እየፈጠሩልን በመሰለን መንገድ እንድንቆራቆዝ ሲታትሩ ከርመዋል፡፡

በዚህ ሁሉ መካከል የዶክተር አብይ መንግስት ስልጣን ከመያዙ አስቀድሞ በተለይም ሀገሪቱ የነበረችበትን ጭንቅ የሚያውቁት፤ በተለይም እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዜጎች ብቻ በቅጡ እንደሚረዱት አስባለሁ፡፡ እንዲያ ያለውን ፈታኝ ጊዜ ሀገር እንዴት ባለ ምጥ ልትወጣው እንደቻለችም ምስክሮቿ ዜጎች ብቻ ናቸው፡፡ እንዲያ የነበሩ ጭንቀቶች የአንድ ወገን ብቻ አልነበሩም፡፡ መልካሙን እንዲያመጣለት ሲመኝ የነበረው ህዝብ በርካታ ነበር፡፡

እዚያው ኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረ ሽኩቻ/ፍትግያ ከበርካታ ሁነቶች ወዲያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ፤ በተለይም የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የነበረው አጣብቂኝ በቅርቡም አቶ ኃይለማርያም በአንድ ሚዲያ ቀርበው እንዳነሱት ከባድ ነበር፡፡

ይህንን ሁሉ ጊዜ አለፍን ብለን የዶክተር አብይን ወደመንበሩ መምጣት ያሳየውን ተስፋ ተከትሎ በርካቶች በተለይም ከመጀመሪያው የፓርላማ ንግግራቸው ጀምሮ ኢትዮጵያንና ህዝቧን የገለጹበት ብሎም በተከታታይ ባደረጓቸው ንግግሮችም ያሳዩት ተስፋ ሰጪ ምልከታዎች ምናልባትም ሀገራችን ወደአንድ መልካም ወደፊት ጉዞ ለመጀመር የታተረች መስሎ እንዲሰማን አድርጎ ነበር፡፡
ይሁንና ወዲያው እዚህም እዚያም ከላይ ያነሳሁት አይነት ኮሽታ መሰማት ሲጀመር፤ ተስፋው በአንድ ጎን እንዳለ ሆኖ ስጋታችንም እያየለ ስለመምጣቱ ግልጽ ይመስለኛል፡፡ በርካቶችም ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው በተለያዩ ሚዲያዎች አንስተው ሲመሰክሩ ማስተዋል ተችሏል፡፡

ጩኸት በበረከተባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ምንድነው ደግሞ ዛሬ እያልን ተስፋችንን ሁሉ ጥለን ስጋትችን እየወረረ ሲያስቸግረን በአንድ በኩል ለሚፈጸሙ ሁሉ ጉዳዮች የመንግስትን (የሚመለከተው አካል) መግለጫ ከመጠበቅ ይልቅ መላምቶቻችን ከፍ እያሉ ህዝቡን ወደባሰ ስጋት ሲከቱት ለማስተዋል የተቻለ ይመስለኛል፡፡

ይህም ይመስለኛል ጩኸቶቻችንን ከጊዜ ወደጊዜ እያባሳቸው፤ ከፍም እያደረጋቸው ያለው፡፡ ትንታኔ የሚሹ ጉዳዮች ባለሙያዎች በትክክል ሁነቶች ላይ አስፈላጊ የሚባሉ መረጃዎችን ሰብስቦ፤ ተንትኖና አጠናቅሮ ከማቅረብ ይልቅ በራሳቸው የግል መላምቶች ተውጠው ለሚያስተውል ሰው፤ “ሀገሬ ከወደየትኛው ነሽ?” ያስብላል፡፡

በባህሪ አስቸጋሪ የሚባል ህዝብ የሌለባት ኢትዮጵያ፤ ለመሪዎችም ሆነ ለገዢዎች በሌሎች ሀገሮች እንደሚታየው አይነት ከመስመር የወጣና አልታዘዝም ባይ ብሎም በብዙ ግፊት የሚናወጥ አይነት ህዝብ የሌላት ኢትዮጵያ ስለምን እንዲህ ባለው ሁነት ውስጥ እንድታልፍ በርካቶች ታተሩ? ስለምንስ ህዝቦችን ወደተለያየ አቅጣጫ ለመምራ ሻቱ? ህዝቡስ (ዜጎች) ስለምን እንዲህ ባሉት አስተምርሆ አቀንቃኞች መዳፍ ወደቀ? ፖለቲካችንስ ስለምን ለጥቂቶች ብቻ የተተወ በርካቶች ጀምረው የማይጨርሱት አይነት ሩጫ ሆነ?

ከላይ ያነሳኋቸው ሀሳቦች እንዳሉ ሆነው፤ ኢትዮጵያ እንደሀገር፤ ህዝቡም እንደዜጋ በተለይም የነበሩትን ባህሎች፤ አብሮ የመኖር ልማዱና እሴቶቹን ስለእኩይ አስተምርሆዎች ስለምን አውልቆ ጣለ? ከሐፍረታችን ባሻገር ያለው ጉዳይ በቅጡ መነገር መወያየትም የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ ሁሉን በዝምታ የምናልፍበት ሳይሆን የምንወያይ የምንነጋገርበት ጊዜም እንደሆነ አስባለሁና፡፡
ካልሆነ አሁን ባለው ጩኸት መጠን እስከመቼስ እንቀጥላለን? ስርዓት ለዘመናት የሚኖር ግብርም በልክ ለመከወን ሁነኛ መንገድ ነውና በኢያሪኮም የሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ቃል ታነቡማላችሁ፡-

‹‹መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ ምዕ. 6፡20
ህዝቡም ጮኹ፤ ካህናቱም ቀንደመለከቱን ነፉ፤ ህዝቡም ቀንደመለከቱን ድምጽ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፤ ቅጥሩም ወደቀ ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ወደፊቱ ወደከተማይቱ ወጣ፤ ከተማይቱንም ወሰዱ፡፡››

ወደፊት ከሐፍረታችን ባሻገር ባልኩዋቸው ሀሳቦች ዙሪያ እመለሳለሁ፡፡ ሰላም!!!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ