2015 ፌብሩዋሪ 27, ዓርብ

ስደት ዕጣ የሆነው ትውልድ

አድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል፡፡ እውነት ነው፡፡ አለም ወደደም ጠላም ያወቀው ድል፡፡ እኩይ ተግባር የተሸነፈበት ድል፡፡ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ክፍላተ አለም ላሉ ጭቁን ህዝቦች እንዲህም ይቻላል ብለው ማሠብ እንዲችሉ ያስቻለ ድል ተጎናጽፈዋል፡፡ ደስ የሚል እውነት፡፡ ደስ የሚል ታሪክ፡፡ የእውነት ኢትዮጵያዊ ድል፡፡ 

ሠሞኑን ብዙሀን መገናኛዎቻችንም እኛም ስለአንድ ነገር ብቻ ማውራት ይዘናል፡፡ የአድዋ ድል፡፡ ግን ሠሞነኞች ነን፡፡ ከአመት አመት ማስተጋባትና መዘከር እየተገባን ሁለትና ሶስት ቀን ብቻ እናወራዋለን፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በርካቶቻችን አድዋ ሲነሣ ኢትዮጵያዊነታችን ደርሶ ይሰማናል፡፡ ደርሰን ወኔያም እንሆናለን፡፡ አድዋ! 

ሰሞኑን የማነባቸው ጽሁፎች ግርም ቢሉኝ ነው ይህችን ልበል ማለቴ፡፡ ወራሪን መመከት የቻለ ኢትዮጵያዊ ስደትን መርጧል፡፡ አድዋ ላይ ድል ያደረገው ኢትዮጵያዊ ባርነትን ሽቷል ነው ያነበብኳቸው ጽሁፎች መንፈስ፡፡ እንደኔ ግን በርካቶች በተለይም ኢትዮጵያውያን ስደትን ለምን መረጡ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው ዋናውና መሠረታዊው ጉዳይ፡፡ ስደትማ እንደሚያንገሸግሽ ስደትማ እረፍት እንደማይሰጥ ለኢትዮጵያዊ ለመንገር መሞከር ለቀባሪው ማርዳት አይነት ይሆናል፡፡ በሀገር መኖር' በሀገር ማጌጥ' በሀገር መስራትና መበልጸግ የማይፈልግ ማን አለ; ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህንን የሚጠላ አይመስለኝም፡፡ 

ሠዎች ነንና ሌሎች ያደረጉትን አይተን ከነሱ ጥሩ የምንለውን ወስደን መተግበር እንፈልጋለን፡፡ ህይወታችን በድህነት የታጠረ ነውና ብዙዎቻችን ቤተሰቦቻችን እኛን ለማሳደግና ለማኖር ብሎም ለማቆየት የከፈሉትን ዋጋ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን (ምንም እንኳ የነርሱን (የቤተሰቦቻችንን ማለቴ ነው) ያህል ባይሆንም) ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ 

ብዙ ጊዜ ደግሞ በአቅራቢያችን ያሉና ከሀገር ውጭ ያሉ ወንድምና እህቶቻችን ናቸው ይህንን ሲያደርጉ የምናየው፡፡ ስለሆነም በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ከሀገር መሠደድ ያስመርጠናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለይ አሁን እንደ ቀበሌ (ወረዳ) ባሉ አገልግሎት መስጫ ተsማት አካባቢና በየመንደሩ ባሉ የገዢው ፓርቲ #ሁነኛ$ ሰዎች ነን ብለው በሚያስቡና የፖለቲካ እውቀት ባሉበትም ያላለፈ በርካታ ሰዎች እየፈጠሩ ያሉት ተጽዕኖም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ለእያንዳንዱ በዜግነታችን ብቻ ማግኘት ለሚገባን አገልግሎት ከብዙ ቢያንስ በአንዱ የቀበሌና የራሳቸው ብቻ ግለሰቦቹ በሚፈጥሯቸው አደረጃጀቶች ውስጥ መታቀፍ #ያልተጻፈ ህግ$ ሆኖ ያገለግላል፡፡ 

ከአድዋ ድል 100 ኛ ዓመት ክብረ በዓል ጋር ተያይዞ ከድሮ ጀምሮ አብሮን የመጣውን ወኔ ቀመስ ሁነት ሁሉም መወርወር ይዟል፡፡ #ጣሊያንን ያባረረ ኢትዮጵያዊ እንዴት አሁን ስደትን ይመርጣል;$ ነው የብዙዎቹ ይዘት፡፡ 

በእርግጥ ኢትዮጵያውያን አድዋ ላይ ድል አድርገዋል፡፡ እውነት ነው ኢትዮጵያውያን አልነካ ብለው ሆ ብለው ለወረራ የመጣውን ጠላት አባረዋል፡፡ ግን ዛሬ ላይም አሁን ያለውን ወጣት ለምን ተሰደድክ ብሎ ከመውቀስ የዘለለ አንዳች ሌላ አማራጭ ማቅረብ አለመቻሉ ያስገርመኛል፡፡ ለምን ብሎ መጠየቅ በሚያስወግዝበት ሁነት& ሀገር ውስጥ መቆየት ምናልባት አያስደስትም ይሆናል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ብዙዎች መሠደድን የሚመርጡት፡፡ 

ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ዜጎች አሁን ያላቸው ብቸኛ አማራጭ የገዢው ፓርቲ አባል መሆን ብቻ እንደሆነ አምነው ወደ ህይወት መድረክ ብቅ ማለት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ህይወት እንኳ ከብዙ በጥቂቱ በፓርቲ ሥራ የሚጠመዱ ወጣቶች በርካቶች መሆናቸውን ይናገራል፡፡ እያየንም ነው፡፡ አሁን አሁንማ የቅጥር ማስታወቂያዎች እንኳ ከዕውቀት በዘለለ ከትምህርት ማስረጃ ይልቅ የቀበሌ የድጋፍ ደብዳቤ ይመርጡ ይዟል፡፡ 

ሀገሬ በእኔ ላይ ብዙ ኃብት (Resource) አፍስሳለች፡፡ እኔ ደግሞ ተምሬ ላገለግላት ካልቻልኩ እኔ ብቻ ሳልሆን ሀገሬም ባክናለች ማለት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ አሁን አሁን በዜጎች ላይ የምናየው በራስ መተማመን ማጣት በነጻነት የፈለግነውንና ያሰብነውን እንዳንከውን ያደርገናል፡፡ 

ስደትን ባላበረታታም የሚሠደዱ ዜጎችን እንደሀገር ከዳተኛ መቁጠር ግን አልደፍርም፡፡ አልደግፍምም፡፡ በትምህርት ቤቶችም ቢሆን መምህራን ጊዜያቸውን በቀበሌዎች እንደሚያሳልፉ ይስተዋላል፡፡ በጊዜው ያላስተማሯቸው ልጆች ቤት ገብተው ግራ ሲጋቡ ማየት የተለመደ ነው፡፡ የትምህርት ጥራት ከምን ይጀምራል; የሚለውን በሌላ ጊዜ ብመለስበት ይሻላል፡፡ 

ግን እኔ መምህራን በየትኛውም የትምህርት መስክ ሊሆን ይችላል (አለማዊውንም መንፈሳዊውንም) የእውነት አባቶች እንዲሆኑ እሻለሁ፡፡ መሻት ብቻ አይደለም አምናለሁም፡፡ በራሱ የሚተማመን ሀገሩን የሚወድና ጠንካራ ትውልድ መፍጠር የሚችል& በቅቶ የሚያበቃ - መምህር፡፡ 

አሁን ግን እየሆነ ያለው የተለየ ይመስለኛል፡፡ መምህራኑ በሌላ ሥራ ከተጠመዱ እንዴት ነው; የትምህርትስ ጉዳይ; ስደት የመምረጣችን አንዱ ምክንያት ምናልባትም ተስፋ ማጣት ሊሆን የሚችለው ለዚህ ይሆናል፡፡ 

መምህራን ብቁ ዜጋ ከመፍጠር ይልቅ አማራጮችን ከማቅረብ ይልቅ ብቸኛ መንገድ የሚሉትን መስመር ማሣየት መጀመራቸው ተማሪዎቻቸው በተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎች ከሚያገኙት መረጃ ጋር በማነጻጸር ውጭን አስመርጦም ይሆናል፡፡ ለነገሩ አካላችን እንጂ መንፈሳችን ከሸፈተ ሰንበትበት ብLDል፡፡ የምናገኘው መረጃ እንኳ የውጭውን ካልሆነ ለብዙሃን መገናኛዎቻችንም ቢሆን ጆሮም አይንም ከልክለናቸዋል፡፡ 

ልባዊ የሀገር ፍቅር ስሜት በሁላችንም ዘንድ ቢኖር ይመረጣል፡፡ ካልሆነ ትውልድ ይኮላሻል፡፡ በርካታ ጀግኖች ነበሯት ኢትዮጵያ፡፡ ጅግንነቱ የት ገባ; ምላሹን እንግዲህ ለሁላችንም በየራሳችን እንየው፡፡ ግን ከላይ የጠቀስኳቸው ነገሮች ሳስብ እንደው ጠቅለል ለማድረግ በራስ መተማመን ማጣትና ፍርሃት ይመስሉኛል ለስደታችን ዋነኛ ምክንያቶች፡፡ 

ፈሪ ትውልድ ደግሞ ለማንም አይበጅም፡፡ የፈሪ ትውልድ ታላቅ ግብር ፈርቶ ማስፈራራት ብቻ ነው፡፡ እናት ጀግና ትውለድ፡፡ ለዛውም ኢትዮጵያ፡፡ ለዛውም ኢትዮጵያዊ እናት ከጀግናም ጀግና መውለድ ትችልበታለች፡፡ 

በርካቶች ብንመኝም ጥቂቶች ባለው ስለተደሰቱ ቢመርጡትም እንኳ፡፡ ሀገር ለሀሉም እኩል ናት፡፡ ይህንን ከጽንሰ ሀሳብ በዘለለ በተግባር ማየት የሁላችንም ምኞትና ፍላጎት መሆን አለበት፡፡ ስደተኛ ትውልድ እያሉ መውቀስ ትርጉም የለውም፡፡ ቅኝ አልተገዛንም ብሎ ማውራት ትርጉም የለውም፡፡ አሁን አሁን በእጅ አዙር ቅኝ ስላለመገዛታችን ማሣያ እየጠፋ ነው፡፡ ስለስደት ሲነሣ መሠደድን ከመውቀስና ከማብጠልጠል የዘለለ ለምን ስደት እንደብቸኛ አማራጭ ተወሰደ ብለን ለመፍትሔው ብንረባረብ ሳይሻል እንደማይቀር ይሠማኛል፡፡ 

ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ተገቢውን ክብርና ነጻነት ማግኘት ይፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ በሀገሩ መሸማቀቅ የሚፈልግ የለም፡፡ ሀገራችን ከማንም በላይ ተከብረን የምንኖርባትና የምንኖርላት ብትሆን ይመረጣል፡፡ ለነጻነታችን ከሀገራችን በላይ ማንንም አንመርጥም፡፡ ሀገራችን ከማንም በላይ በየኛነት ስሜት የምንኖርባት ብትሆን መልካም ነው፡፡ ለእኔ ከተመቸኝ ምን ገዶኝ የሚል ስግብግብነት የፈሪ ትውልድ መለያ ነው፡፡ 

ከፈሪ ትውልድ ይሰውረን፡፡ ለምን ብሎ የሚጠይቅ ትውልድ ያስፈልጋታል ኢትዮጵያ፡፡ የሚያየውን ያልተገባ አካሄድ የሚቃወም አማራጮችን የሚያመላክት ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚያስብ ትውልድ ያሻታል፡፡ ካልሆነ አደጋው የከፋ ነው፡፡ ዛሬን እንጂ ነገን የማያስብ ትውልድ የሚያጋጥመውን ላለማወቅ የሚፈልግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከፍርሃት የመነጨ ነው፡፡ ምክንያቱም በጥቂቱም ቢሆን ሲያስብ የሚያጋጥመውን አዘቅት ያውቀዋል፡፡ ከዚህ ፍርሃትና ጭንቀት ለመውጣት እንደብቸኛ መፍትሔ የተያያዝነው ደግሞ ስደትን ነው፡፡ 

እርግጥ ነው ሀገር ሀገር ለሚል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የስደት ጉዳይ አንገብጋቢ ነው፡፡ ሀገር ላይ አለመከበር ያሳምማል፡፡ ክብርና ኩራት ብለን የምንፎክርበት ኢትዮጵያዊነት በፍርሃትና ልፍስፍስነት ተተክቷል፡፡ ስደትን መፍትሔ ማድረግ ይዘናል፡፡ መወቃቀስ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ለምን ብለን መጠየቁ ነው የተሻለው፡፡ ሲደረግ እያየን ስላልተደረገልን ለምን ብለን ብንጠይቅ ቁጣ አያሻውም፡፡ 

ስደትን እያበረታታሁ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን ያለኛ ማሠብ አይደለም ለማሠብ መሞከር በራሱ ሀጢያት ይሆንብኛል፡፡ ግን የምናያቸው ነገሮች ያስገደዱንም ይመስለኛል፡፡ ለነገሮች ብቃት ኖሮን አለመመረጣችን ያሳምመኛል፡፡ መገፋት ማንንም አያስደስትም፡፡ እንሰደድ ባልልም ቢያንስ ለውድድር ብንቀርብና በአንድ አይነት የውድድር መስፈርት ብንመዘን መልካም መሆኑን ሳልገልጽ አላልፍም፡፡ ማንም መድሎ ሲደረግብት እያየ መቀመጥ አይፈልግም፡፡ ለዚህም ስደትን ያስመርጠዋል፡፡ 

የኤርትራው ፕሬዜዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ አንድ ጊዜ ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የሰጡትን መልስ አስታወስኩ፡፡ ዜጎች ከኤርትራ በየቀኑ ወደ ጎረቤት ሀገሮች ይሠደዳሉ፡፡ ሀገርዎን የወከሉ ስፖርተኞች እንኳ በሄዱበት ቀርተዋል ለምንድነው; ብላ ጠየቀች ጋዜጠኛዋ፡፡ ፕሬዜዳንት ኢሣያስ ተገረሙ፡፡ ይሄ ለእኔ አዲስ ነው ብለው መለሱ፡፡ ለነገሩ ማንም ሠው የተሻለ ነገር ፍለጋ የትም ቢሄድ እንደማይገረሙ አከሉበት፡፡ 

© አብርሃም ተስፋዬ  
This article was publish in "Awramba Times" newspaper on March 12, 2011.

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ