2014 ሴፕቴምበር 7, እሑድ

‘‘ከመቃወም ባሻገር በኢትዮጵያ’’ ፪

ሀ. ለድምጽ የለሾቹ ድምጽ ስለመሆን

አንዳንድ ጊዜ በተወሠኑ ጉዳዮች ላይ የሚሠማው ጩኸት በጣም ይገናል፡፡ የጩኸቱ ብርታትም ይሠማል፡፡ የተወሰኑ ጉዳዮች ከሌሎች በተለየ መልኩ ትኩረት ይስባሉ፡፡ እኒህን ጉዳዮች ተጠቅመው የሚያራግቡ በርካታ ፓርቲዎች አሉ፡፡ በተለይ የብሔር፣ የሐይማኖት፣ የግዛትና መሠል ጉዳዮች ምድሩን ለመነቅነቅ ሲቻላቸው ይታያል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በአንድም ይሁን በሌላ ከማንነት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ሁሉም የራሱን ጽንፍ ለመያዝ ሲጮህ ይሠማል፡፡ በርካታው ጩኸት ግን ችግሩን ከማግዘፍ በዘለለ መፍትሔውን ለመጠቆም ያነሡ ይሆናሉ፡፡ ግለኝነት ይስተዋልባቸዋል፡፡ ሀገራዊ ፋይዳቸውን ከመጠቆም ይልቅ የራስን የግል ስሜት ወይም ‹‹በርካቶች ሊቀበሉትና ሊከተሉት ይችላሉ›› ተብሎ የሚታሠበውን ነገር ይዞ የመጓዝ ነገር ይስተዋላል፡፡ በእርግጥ የተቃውሞው ጎራ ጥንካሬም ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ማለት ነው፡፡ የህዝብን ድምጽ ለማስተጋባት የሚያስችል አቅም አለ ወይ? ሌላው ጥያቄ ይሆናል፡፡

ለ. ሁነኛ አማራጭ ስለመሆን

እንደኛ ባለው ሀገር የህዝቡን የፖለቲካ ዕውቀትና ብስለት ብሎም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች፤ ኢኮኖሚያዊ አቅምና፤ ከድሮ ጀምሮ ተያይዞ የመጣውን የፖለቲካ ልምድ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለህዝቡ ሁነኛ አማራጭ ነኝ ብሎ የሚቀርብ ፓርቲ ይዞ የሚመጣው አዲስ ነገር ምንጊዜም በህዝቡ ልብ ውስጥ ጥርጣሬ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ደግሞ ከንጉሱ ዘመን አንስቶ አሁን እስካለንበት የኢህአዴግ ዘመን ድረስ ያለው ልምድ በህዝብ ዘንድ አመኔታን ወዲያው ለማግኘት አዳጋች እንዳደርገው አስባለሁ፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ ምርጫ 97 እና በወቅቱ ሠፊ ተቀባይነት የነበረው ‹‹ቅንጅት›› ብሎም የምርጫው ውጤት በይፋ ከተገለጸ ወዲያ ያጋጠመውን ሁነት በፓርቲው አመራር አካባቢ የታየው የመፈረካከስ ዝንባሌ ከምርጫው አስቀድሞ ያልተሠሩ የቤት ሥራዎች ስለመኖራቸው በርካቶች እንዲያስቡ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከጊዜ በኋላም በአመራር ላይ የነበሩት አካላት በጽሁፍና በቃል በተለያየ አጋጣሚ የሠጧቸው ሀሣቦች ክፍተቶች እንደነበሩ ያሣያሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ራሳቸውን እንደአማራጭ ለማቅረብ ባሉበት ሁኔታ የውስጥ አሠራራቸውን በመፈተሸ አንዳች ለውጥ ለማምጣት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ እውነት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ዴሞክራሲያዊ ስለመሆናቸው የሀሳብ ልዩነቶች በተረጋጋና በሠከነ ሁኔታ ለመፍታት የሚሞክሩባቸውንና ለፓርቲ ዲሲፕሊን የሚያሳዩትን ተገዢነት ለህዝቡ የሚያሳዩባቸው መድረኮች ናቸው፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች በምንመለከተው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ልዩነቶችን በሠላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ሌላ ፓርቲ ማቋቋምና የግለሰቦችን ገመና ማውጣትና ‹‹ማራከስ›› ልማድ ሆኗል፡፡ በዚህ መንገድ ከላይ እንደጠቀስኩት ግልጽነት ያለው አሠራርና እውነትነትን የያዘ አስተዳደር መፍጠር ግድ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ጥርጣሬን በህዝብ ልብ ከማጠንከር ባሻገር ጠቀሜታው አንዳችም እንኳ አይታየኝም፡፡

ሐ. በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት መቃወም

የሀገሬ ተቃዋሚዎች መቃወሙን ችለውታል ለማለት የሚደፍሩ እንደማይጠፉ አስባለሁ፡፡ ተቃውሟቸው እስከምን ድረስ ነው? የሚለው ነው ወቅታዊው ጥያቄ፡፡ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የሚችል ተቃዋሚ ዕድሉን አንድ ደረጃ ከፍ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተቃራኒው በጣት ከሚቆጠሩት ፓርቲዎች (እነርሱም ቢሆኑ በርካታ ችግሮች ይነሱባቸዋል) ውጪ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለመቃወም ምርጫን የሚጠብቁትን ኢትዮጵያ ትቁጠራቸው፡፡

መ. አራተኛው ሚና

አራተኛውና አዲሱ ሚና በብዙ ረገድ ከእኛ የደረሰ አይመስለኝም፡፡ ገና ብዙ በርካታ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትና ቀደም ሲልም በበርካቶች የሚጠቀሱቱ ሚናዎች ላይ መሠራትና የዴሞክራሲ ባህላችንም መዳበር ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡

ውህደትን እንደአማራጭ

በርካታ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ያሉ ፓርቲዎች ቁጥር ሲያሳስባቸው ይስተዋላል፡፡ ብዙዎችም የፓርቲዎቹ ፕሮግራም የተቀራረቡ እንደሆኑ በመግለጽ ተባብረው አልያም ተዋህደው ቢሠሩ ጠቃሚ እንደሆነ ይመክራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በዚህ ረገድ ያለውን እውነት ለመቀበል አሁን ያለው የፖለቲከኞች አስተሳሰብ ገና ነው ብለው የሚሞግቱም አሉ፡፡ 

አብርሃም ተስፋዬ


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ