ዓርብ 13 ጁን 2014

አደባባዩን ፍለጋ


የግብጹን ታህሪር አደባባይ አልረሳውም፡፡ በፍጹም የበላይነት፤ ህዝብ ተቆጣጥሮት እንደነበር አውቃለሁና፡፡ የቱኒዚያውን የህዝብ ማዕበል ያስተናገዱ ጎዳናዎችንም አልረሳቸውም፡፡ ሊቢያውያንም የተዋደቁባቸውን ጎዳናዎች ለመርሳት ይከብደኛል፡፡ የእነዚህንም ሀገራት መሪዎች ብረሳ ዋጋ አይኖረኝም፡፡ እንዴት ይረሳሉ? በፍጹም፡፡

ቦአዚዝ የሚባልንም ወጣት አልረሳውም፡፡ ለዛውም ቱኒዚያዊ ወጣት፡፡ ኑሮን ለማሸነፍ የከፈለውን ዋጋ ብረሳ ነፍሱ ትቀየመኛለች፡፡ እንዲህም ላለው ጀግና፤ መረሳት ክብር አለመስጠት ነው፡፡ በወጣትነት ዕድሜው ለሀገሩ (ባያየውም) ታላቅ ግብር የከወነ የለውጥ አባትና አምባሳደር ነው፡፡ ተጨቆንን ያሉ ሁሉ የተከተሉት የእርሱን ቁጣ ነበር፡፡ በእራሱ ላይ የወሰደው እርምጃ በጣም ከባድ የሚባል ውሳኔ ነው፡፡ እዚህኛው ስሜት ላይ ለመድረስ የሚያስችለው ስሜት የትኛው ይሆን? (በቅርቡ በእራሱ እጅ ያለፈው ወዳጄን አስታወስኩ፡፡ ከማለፉ ከጥቂት ቀናት በፊት ወደቤት እየገባሁ ሳለሁ አግኝቼው ያጫወተኝ ሁሉ ከልቤ አለ፡፡ ማለፉን ስሰማ ማመን አቅቶኝ ነበር፡፡ እርሱ ሲቀር ሁሉም ነገር አብሮ ቀረ፡፡ ቴዲ (ገጀራው) ነፍስህን ይማረው፡፡ ከርዕሴ እንዳልወጣ ወደዋናው ጉዳዬ ልመለስ፡፡)

ባህሬይን፣ የመን፣ ሊቢያና ሌሎችም የአረብ ሀገራት ከጥቂት አመታት በፊት በህዝብ ተቃውሞ ማዕበል ተመትተው ነበር፡፡ ዜጎች አደባባዮችን (ገላጣና በጣም የተንጣለሉ) ‹ምሽግ› አድርገው ከርመውባቸዋል፡፡ ይህ ኹነት ታዲያ በቀጥታ በተለያዩ መገናኛ ብዙኸን ለአለም ህዝብ ሲደርስ ሰንብቷል፡፡ አስደናቂ ጊዜያት አልፈዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት በእኛም ሀገር ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ዜጎች የየዕለቱን ሁኔታ በተለያዩ ድረገጾች ይከታተሉ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

አደባባይ ላይ ውሎ የማደርን ጥበብ ለአረብ የሠጠው ማነው; ብለን ጠይቀንም ነበር በወቅቱ፡፡ ታዲያ በርካቶች ማለትይቻላል በአንድም ይሁን በሌላ ጊዜ በርካታ የደም ዋጋ ተከፍሎበት ለውጥ ሆነ፡፡ በግብጽ የነበረው ደግሞ በተለይ ወታደሩ አካባቢ የታየው ገለልተኝነት አስደናቂ ተብሎ ነበር፡፡ (ከልብ ይሁን አይሁን አስካሁን ግልጽ አይደለም፡፡ ምክንያቱንም ወታደራዊው ቡድን ስልጣን ከያዘ ወዲያ በጣም ጨከን ያሉ እርምጃዎችን ታዝበናልና ነው፡፡) በጊዜ ሂደት አላስፈላጊ ነገሮች መሆናቸው ቢታመንም፡፡ አሁንም ድረስ የሚታዩት ነገሮች አንዳንድ ጊዜ በጥልቀት መታየት እንዳለባቸው ያመላክታል፡፡ አሁንም ድረስ በወታደራዊው ክንፍ ያለው ሁኔታ ድጋፎች እንዳሉት ሁሉ ቅዋሜም እንዳላጣ እየተመለከትን ነውና፡፡

አደባባይ የወጡት ዜጎች አደባባይ ውለው፤ አደባባይ አድረው ለውጥ አመጡ፡፡ (አደባባይ ስለነበራቸው፡፡) በዚህ ሁሉ ውስጥ ታዲያ የሆነው ሆኖ ዛሬ ላይ ብንሆንም የለውጥ ማደሪያው የት እንደሆነ በብርቱ መልዕክት አስተላልፎ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ ቀደም ሲል በሀገራችን ኢትዮጵያ 1997 ላይ የሆነውን ሁነት ለሚያስታውስ ሰው ደግሞ የአደባባይ ትርጉሙ በእርግጥም ይገባዋል ለማለት ይቻላል፡፡ መቼም ያንን አመት መናፈቅ ሀጥያት እንደማይሆን አስባለሁ፡፡ ‹ነጻ› ‹ፍትሐዊ› እና ‹ዴሞክራሲያዊ› ሂደት የነበረው ምርጫ ለማካሄድ በሚል የተደረገው ሁሉ ግሩም ነበር፡፡ አድባባዩም በወቅቱ ክፍት ነበር፡፡
ወደቀደመውም ዘመን እንመለስ ካልን ተማሪዎችም ሆኑ ዜጎች ሠልፍ ለማካሄድ በፈለጉ ወቅት አደባባዩን መፈለጋቸው ግልጽ ነበር፡፡ የቀድሞ ተማሪዎች ንቅናቄን በተለያየ ወቅት የተጠቀሰ ጉዳይ ስለሆነ መመለስ አይሁንብኝ፡፡ ታሪክ በእራሱ መንገድ ያስተናግደዋልና፡፡

ይህንን ሁሉ ማለቴ ታዲያ ያለነገር አልነበረም፡፡ ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. በመድረክ ፓርቲ መሪነት የተጠራውንና፤ የተካሄደውን ሠልፍ ተመልክቼ ነበር፡፡ ከመነሻው ሠልፉን አልተመለከትኩትም ነበርና ሠልፉ የሚካሄድበትን ቦታ ለማጣራት ወዳጆቼን ጠየቅኩ፡፡ ቦታውን ነገሩኝ፡፡ አካባቢውን ቀደም ሲልም ስለማውቀው፤ ሰፈሩ አልጠፋኝም፡፡ ‹አደባባዩን› ግን አላውቀውም፡፡ ስለሆነም አንድ መላ ዘየድኩ፡፡ ጠንከር ያለውን የአካባቢውን ጥበቃ አየሁኝ፡፡ ግራ ቀኙን መመልከት ጀመርኩ፡፡ በሁለቱም በኩል ያሉትን የጸጥታ ኃይሎች ይዤ ብሄድ እንደምደርስ አሰብኩ፡፡ ‹አደባባዩን› ፍለጋ ላይ ነኝ፡፡ ጉዞዬ አላበቃም፡፡ በመንገዴ ሁሉ ‹አደባባይ› እናፍቃለሁ፡፡  ከቦታው ደርሼም ታዘብኩኝ፡፡

የሠልፉ ተሳታፊዎች ከመድረኩ የሚነገረውን እየተቀበሉ ያስተጋባሉ፡፡ ዞር ዞር ብዬ ለመቃኘት ሞከርኩ፡፡ በተቻለኝ አቅም ዙሪያዬን ለማየት ችያለሁ፡፡ ሁሉም ዞሮ የሚመለከተውን ይመለከታል፡፡ የፍርኃት ድባቡ ከባድ ነበር፡፡ ሁሉም ሰው ያያል፡፡ ጥርጣሬው ሌላ ነበር፡፡ እኔ የማስበው አደባባይ ሌላ ነበር፡፡

የተሳታፊዎቹን ሁኔታ ለተመለከተ፤ እውነት ለመናገር አስገራሚ ነበር፡፡ ከልባቸው ሆነው ሁኔታውን በብርቱ የሚሳተፉ ነበሩ አንዳንድ ደግሞ ሰዎችንና የግለሰቦችን እንቅስቃሴ በትኩረት ሲከታተሉ የነበሩ እንደነበሩም ታዝቤያለሁ፡፡ ሞባይላቸውን አውጥተው ሁኔታውን የሚቀርጹ ምስል የሚያስቀሩ እንደነበሩ ሁሉ ሞባይል ወይም ሌላ መሰል ነገር ወደአፋቸው አስጠግተው በጣቶቻቸው መሀል የምስል መመልከቻና ማቅረቢያ (ሌንስ) ብቻ እያሳዩ የጎሪጥ ሁነቱን የሚመለከቱ ነበሩ፡፡ እነዚህኞቹ ምናልባት ምስል እያስቀሩ እንደሆነ ገመትኩ፡፡

የሰልፉ አስተባባሪዎች ህዝቡን ‹በጨዋ ደንብ› ይሉታል ደጋግመው፡፡ ይሄ የ‹ጨዋ ደንብ› ምንድነው? በቦታው የነበሩ ወዳጆቼን ጠየቅኩኝ፡፡ እነርሱም ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረውን ጨምረው ነገሩኝ፡፡ የተጻፉ መፈክሮችን ሳይቀር የእኛን ተጠቀሙ ይሉ ነበር፡፡ በሠልፉም መካከል አንዳንዶች መፈክር ሊያሰሙ ሲሉ የ‘እኛን ብቻ ቆይ’  ይሉ እንደነበርም ጭምር፡፡ ይህ እንግዲህ ከምን እንደመነጨ መገመት ከባድ አይደለም፡፡ (የዚህች ጽሁፍ አቅራቢ ታዲያ የሰልፉን አስተባባሪዎች አልያም ፓርቲውን እየተቸ አለመሆኑን ልብ ይባልልኝ፡፡) የፍርሃት ቀንበር ተጭኖብን፤ እንዴት ነው ጥያቄዎቻችንን በተገቢው ሁኔታ ለማቅረብ የሚቻለው?

ፈቃድ ተጠይቆበት፤ በቂ የጥበቃ ኃይል ተመድቦለት፤ ህጋዊ ዕውቅና ያለውን አንድ ሰልፍ ለማካሄድ፤ ህጋዊነቱን በጠበቀ ሁኔታ ማንኛውንም ጥያቄ ይዞ ቢነሳ ምን ችግር አለው? የሰልፉስ ታዳሚ የተሰማውን ቢገልጽ ምን ክፋት አለው? በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞና ጥያቄውን የሚያሰማ ህዝብ ፈር ባልለቀቀ ሁኔታ በተገቢው መልኩ ጥያቄውን ቢጠይቅ ምን ችግር ይኖነው ይሆን? እንዲህስ ያለው ስጋት እስከመቼ አብሮን ይቆይ ይሆን?

በቦታው ከነበሩት ተናጋሪዎች መካከል አንደኛው፤ ለሠልፉ የጥሪ መልዕክት ሲያስተላልፉ የነበሩና ቅስቀሳ ላይ የነበሩ አስተባባሪዎች መታሰራቸውን ተናግረው ነበር፡፡ እንዲህ ባለው ወቅት ላይ እነዚህ ግለሰቦች የታሰሩት ለም ይሆን; ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ፈጽመው ከሆነም መንግስት እንደመንግስት ስለምን ቀድሞ ለህዝቡ አያሳውቅም? ይህንን የምጠይቀው ሰልፎችና ተቃውሞዎች ብዙ ጊዜ በእስር መታጀባቸው ስለሚያስገርመኝ ነው፡፡ ሰልፍ ካለ እስር አለ አይነት ነገር ይስተዋላል ብዙ ጊዜ፡፡ መንግስትስ ዜጎችን በማሰር የሚያተርፈው ስንት ይሆን?

ወደ አደባባዩ ልመለስ፡፡ ሠልፉ እየተካሄደ ያነበረበት ቦታ ላይ ብሆንም፤ በሀሳብ ነጎድኩ፡፡ ጉዞ ወደ1997፡፡ መለስ ብዬ ደግሞ ወደውስጥ አልፌ ያለሁበትን ቦታ አየሁና፤ አደባባዩን መፈለግ ጀመርኩ፡፡ አደባባዩስ? አነስተኛ በምትባለው ሜዳ ላይ ነው ያለሁት፡፡ ዳር ቆመው የሚታዘቡትን ጨምሮ ሌሎችም ንግግር ከሚያደርጉት የመድረክ አመራሮችና አባላት የሚባለውን ያዳምጣሉ፡፡ በቅርቡም በተከታታይ ሠልፎቹ የተካሄዱት እዚሁ እንደሆነ ገመትኩ፡፡ አካባቢው ሲጠራ ሰምቼያለሁ፡፡ ስለሆነም ሠልፍ መካሄዱን አወቅኩኝ፡፡

እኔ ግን በቦታው ሆኜ ባላውቀውም ታህሪር ላይ የነበረውን ጀብድ አሰብኩት፡፡ 1997 ላይ ራሴን አስቀምጬ መስቀል አደባባይን ናፈቅኩት፡፡ ያንን የህዝብ ማዕበል በእዝነ ህሊናዬ ተመኘሁት፡፡ ዳግም ምልሰት ወዳለሁበት ሆነ፡፡ በዚህ ሜዳ የተካሄዱትን ሰልፎች እንደው ዝም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች የተከወኑ እንደሚሆኑ አስቤ፤ ሀሳብም፤ ድንጋጤም ሀዘንም ወረረኝ፡፡ የአደባባይ ናፍቆት ሆነብኝ፡፡ እኔም አደባባይ ብሆን ተመኘሁ፡፡ ስጋት ባረበበት ምድር ላይ ለካንስ አደባባይም ይጠፋል? ስለሰልፉ ማሰብ ስጀምር ፍርኃታችን የት እንደደረሰ በማሰብ እሳቀቃለሁ፡፡ ሀሳባችንን ለመግለጽ ምንና እንዴት ማድረግ እንዳለብን ማሰብ የጀመርን ‘ለት አንዳች ስህተት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ማንም በማንም ሀሳብ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የሚቻለው ቢኖር፤ እርሱ የተሳሳተ ነውና፡፡ ማሰብ፤ ያሰብነውን መግለጽም ሁሉ የእኛ የሰው ልጆች ጸጋ ስለሆነ፡፡ ለዚሁም የሚሆኑ፤ ገላጣ ምሽጎች (አደባባዮች) ያስፈልጉናል፡፡

አደባባዮች ጌጦች ናቸው፡፡ አደባባዮች ህዝብ ያለውን ብሶት የሚያሳይባቸውና ያሳየባቸው ገላጣ ምሽጎች ናቸው፡፡ ሀገሬም ታዲያ ይህንን መሰሉን አደባባይ ናፈቅኩት፡፡ ህዝብ በይፋ ያለምንም መሳቀቅ ወጥቶ ሀሳቡን የሚገልጽበት ግልጽ ምሽግ፡፡ የእኛነታችንን ጥያቄዎች በግልጽ የምናሰፍርባቸው፤ ልዩነቶቻችን ላይ የምንማከርባቸው፤ የእኛ ምሽጎች፡፡


ከዚህም ወዲያ ሠልፎች እንደሚኖሩ አስባለሁ፡፡ ታዲያ የትኛው አደባባይ በግልጽ ሊያተያየን ይችል ይሆን? ስለሆነም አደባባዩን ፍለጋ ላይ ያለን ይመስለኛል፡፡ ገላጣውን፤ በስርዓት ያለመሸማቀቅ ሆ ብለን ድምጻችንን የምናሰማበት፡፡ ከፍርሃት ተላቀን በቀና መንፈስ ተረዳድተን የምንከራከርበት፤ የምንነጋገርበት፤ ሀሳብ የምንለዋወጥበት፤ ለውጥ የምንጠይቅበት፤ ለውጥ የምናመጣበትም አደባባይ፡፡ ሠልፉ እየተካሄደ ነው፡፡ እኔ ግን አደባባዩን ፍለጋ ላይ ነበርኩ፡፡ አሁንም ፍለጋ፡፡ አደባባዩን፡፡ 

አብርሃም ተስፋዬ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ