ሰኞ 12 ሜይ 2014

የተከበሩ የአቶ ግርማ ሠይፉ ተቃርኖ


ሰሞነኛው ወሬ የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ነው፡፡ አዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙት የፊንፊኔ ልዩ ዞኖችን ባማከለ መልኩ ተሰናዳ የተባለው ማስተር ፕላን በርከት ያለ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ በተለይ በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች እና በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ሁኔታውን በጣም አክርረው ተቃውመውታል፡፡ በዚሁም መነሻ አሳሳቢ የሚባል አይነት ተቃውሞና ግጭት ተከስቶ የሰው ህይወትና የንብረት ውድመቶችን እንዳስከፈለ ሰምተናል፡፡ በተለይ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ሁኔታውን ከቦታው የሚዘግቡት ስለነበሩ በምስል የተደገፉት መረጃዎች ልብ ይሰብሩ ነበር፡፡ በተለይ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉት ዜጎች ላይ የተፈጸመው ግድያና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን ጉዳይ አስመልክቶ መንግስት አንዳች ነገር መከወን አለበት፡፡ እንዲሁ ዝም ብሎ ሊታለፍ የሚገባው አይደለም፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ታዲያ ይመለከተናል ያገባናል ያሉና የሚሉ ግለሰቦች ኃሳባቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ኃሳባቸውን መስጠት መብታቸው መሆኑን አምናለሁ፡፡ ህገመንግስታዊ መብታቸውም ጭምር እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ስለሆነም፤ ኃሳባቸው አከብራለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ አንዳንድ በሀገሪቱ የሥልጣን እርከን ቁንጮ ከሆኑት አካባቢ ያሉትን ግለሰቦች ኃሳብ በብርቱ ማክበሬን ሳልጠቅስ ባልፍ ደስ አይለኝም፡፡ ስለሆነም ሙግቴ ሀሳባቸውን ብቻ ስለመሆኑ አስምሬ እናገራለሁ፡፡ አዋጅ! አዋጅ! አዋጅ! ሙግቴ ከኃሳባችሁ ብቻ ነው፡፡ እነሆ ለመጀመር ፈቃድ ሆነ፡፡

የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ ግንቦት 2 ቀን 2006 ዓ.ም. በወጣችው ፋክት መጽሔት ቅጽ 2 ቁ. 45 ላይ ያሰፈሩትን ሀሳብ አነበብኩኝ፡፡ ጉዳዩ ግራ ስላጋባኝ ደግሜ አነበብኩት፡፡ የተከበሩት የምክር ቤት አባል በአንድ ወቅት ጢስ አባይን ለማየት በሄዱበት ወቅት ካደረጉት ውይይት ጋር አስታከው በወቅቱ የነበረውን የ‹‹ቦታ››ውን ጎጃሜነትና ጎንደሬነት አንስተው ከተነጋገሩ ወዲያ ከወዳጃቸው ይልቅ፤ የአካባቢው እረኛ የተሻለ መረዳት እንዳለው ገልጸው ነው የሚጀምሩት፡፡ እረኛውን ቦታው ምዕራብ ጎጃም በመባሉ የተሰማውን ሲጠይቁት፤ ‹‹....ውሃውም መሬቱም እዚሁ ድሮ ያለበት አይደለ?›› ብሎ እንደጠየቃቸውና የዕድሜ ልክ ትምህርት እንደሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ ከእረኛ ለመማር ዝግጁ ለሆነ ሰው ሊማር እንደሚችል ነግረውናል፡፡ ግን ለጥያቄያቸው የተሰጣቸው መልስ ምናልባት አሁንም ድረስ በደንብ ያልተገለጠላቸው ከሆነ ምላሽ መስጠት ተገቢ መሰለኝ፡፡ ምናልባት እረኛውን ባልሆንም፤ የእርሱ አረዳድ እርሳቸው ካነሱት ጭብጥ ጋር ፈጽሞ የገጠመ ስላልመሰለኝ ነው ይህንን ማለቴ፡፡

እረኛው አለ ያሉት ‹‹....ውሃውም መሬቱም እዚሁ ድሮ ያለበት አይደለ?›› ነው፡፡ ውሃና መሬትማ የት ይሄዳል? ሂያጁ ሰው ነው፡፡ ድሃው ገበሬ፡፡ ይህ ድፍን ኢትዮጵያን ከሚቀልቡት በርካታ ገበሬዎች ተርታ የሚሰለፈው ድሃው የእናት አለም ኢትዮጵያ ገበሬ ነው፡፡ እረኛውም መልሱን ሲሰጥ ሊሰጥ የሚችለውና የቻለው በዛን ወቅት የነበረውን እውነት ተገን አድርጎ እንጂ አሁን አሁን በተለይ ከልማት ጋር በተያያዘ የመንግስትን የመሬት ፍላጎት ለመሙላት ሲባል ከ‹‹መሬታቸው›› ላይ የሚፈናቀሉትን ሰዎች ስሜት ያገናዘበ ባለመሆኑ ክቡር አቶ ግርማ ‹‹ክፉኛ›› ተሳስተዋል፡፡ ጋራ ሸንተረሩማ የት ይሄዳል፡፡ ያው የኢትዮጵያ ነው፡፡

እኑህ ገበሬዎችም ሆኑ፤ በየዩኒቨርሲቲው የሚገኙት ልጆቻቸው ታዲያ እንደው ልማትን በመጥላትና በመጠየፍ ተቃውመውታል ብዬ ለማሰብ ይከብደኛል፡፡ ልማትማ የሚጠላ አንዳችም እንዳለ እጠራጠራለሁ፡፡ የህዝቡ ጥያቄ የልማቱ ተካፋይ የመሆን መስሎም ይታየኛል፡፡ እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች ደግሞ በአንድም ይሁን በሌላ አጋጣሚ ገበሬዎቹ እራሳቸውና ዘመዶቻቸው፤ ብሎም በሌላ አካባቢ የሚገኙ ዜጎች ላይ ከደረሰውና ከሚደርሰው በመነሳት የሚመነጭ ጥያቄ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ህዝብ እንደ ህዝብ በይፋ ልማትና ለመጥላት የሚያስችል አንዳችስ ምክንያቱ እርሱ ምን ይሆን?

ክቡርነትዎ፤ አሁን በየዩኒቨርሲቲው የሚገኙት ተማሪዎች የኢህአዴግ ትውልዶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ጎጠኝነትን በሚያሞግስ አጠቃላይ የፖሊሲ አቅጣጫ እየተመሩ የመጡ ናቸው ብለው ደምድመዋል፡፡ የኢህአዴግ ፖሊሲም ይሁን የማን አሁን ባለው ሁኔታ ብሄርን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተዋናይ መሆን ግድ የሆነ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ በመሠረቱም እኔ በግሌ የብሔር ጉዳይ ተፈጥሯዊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ማንም ቢሆን ስለማንነቱና እርሱ ከየትኛው ግንድ እንደሆነ ለመጠየቅ ገና ስለuuና ስለuu ነገዶች ሲማር መመርመር እንደሚጀምር እገምታለሁ፡፡ ኩሽ፤ ሴሜቲክ፤ እየተባለ ሲማር ከየት ነኝ ብሎ መጠየቁ ሰዋዊ ነው፡፡ ከዚያም ወዲህ ባለው ጉዳይ የኢትዮጵያን ታሪክ ፍጹማዊነት አበክረው ካላመኑ በቀር በደል ደርሶብኛል የሚል የትኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ፤ በአንድ አጋጣሚ ተነስቶ እኔ ለምን እንዲህ እንዲፈጸምብኝ ሆነ ብሎ በጠየቀ ቁጥር ጎጠኛ እየተባለ የሚፈረጅ ከሆነ፤ ጎጠኛ የሚሉትም አካላት በእራሳቸው አግባብ መጠየቅ ያለባቸው ይመስለኛልና ነው ይህንን ማለቴ፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት ሊጠናከር የሚችለው ሌሎችን በመደፍጠጥ ነው ብዬ ስለማላስብ ነው ይህንን ማለቴ፡፡

ጎጥም፤ ጎሳም፤ ብሔርም፤ ምንም ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ ሁሉም ግን ተፈጥሮ ለሰው ልጅ የቸረችው ነው፡፡ ወደእራሱ በቀረበ ቁጥር የሚታወቀው፤ አንዳች የማንነት ቁስል ነው ይሄ፡፡ ስለሆነም፤ ጥያቄ መነሳቱ ስህተት ነው ብዬ አላስብም፡፡

ባይሆን፤ የእርስዎ ትንታኔ ጥያቄውን ምናልባት በትክክል ካለመረዳት የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ የሚነሱት ሀሳቦች ከበርካታ ጽሁፎች ላይ ለመረዳት እንደቻልኩት፤ እንዲሁም ከድረ-ገጾች ላይ ባገኘሁት መረጃ መሰረት፤ (ሌሎቹ ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው እርስዎ ባነሱት የማስተር ፕላኑ ጉዳይ ላይ ብቻ አተኩራለሁ) ኢትዮጵያችን የጋራ አይደለችም ከሚል የመነጨ አይደለም፡፡ እንዲህም ነው ብዬ አላስብም፡፡ መነሻው የህዝብ ጥቅም ይመስለኛል፡፡ ህዝቡ ደግሞ ይጠቅመዋል ብሎ እዚህ ሆኖ መደምደም በእኔና በእርስዎ አያምርም፡፡ ምክንያቱም እዛው ያሉ፤ በዚህ ሁነት ውስጥ የሚኖሩት ዜጎች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሃሳብ በግልጽ ማስተጋባት የሚችሉበት ሁነት መኖር ነበረበት፡፡ እርስዎም እንደሌሎቹ ሁሉ (በጉዳዩ ላይ የኮሚቴ አባል ናቸው ተብለው በብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ የቀረቡ ባለሥልጣናት) አሁን ያለው ዓለም አቀፍ ልምድ የሚያሳየው ይህንን እንደሆነና በጋራ የመልማት ስትራቴጂም የግድ መሆኑን አንስተው ሞግተዋል፡፡ ሙግትዎ አለማቀፋዊውን ልምድ በተመለከተ ጥሩ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ ሀገራዊውም ልምድ ታዲያ በእርግጥም ከታሰበበት መወሰዱ ግድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከልማት ጋር በተያያዘ ከመኖሪያቸውና ከቀዬያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች አሁን እየከፈሉ ያሉትን ዋጋ እነርሱን ሆኖ ማሰብ ያሻል፡፡ እኛ ምናልባት ሞልቶልን ቢሆንም ቅሉ፤ የእነዚህ ዜጎች መፈናቀል የወር ቀለባችንን እንዴት ብለን ከወደየት ልንሸምት እንደምንችል አያስጠይቀን ይሆን? ነገን ማን ያውቃል? አለማ አቀፋዊውም ልምድ ታዲያ በርካታ ጥያቄዎች መመለስ አለበት፤ የተገበሩት እነማን ናቸው? ሲተገበርስ እንዴት ነው የተተገበረው? እንዲህስ ያለው ታላቅ ዕቅድ እንዴትና ከየት ነው መመንጨት ያለበት? ማንስ ነው በማን ላይ መወሰን ያለበት?... እኒህና ሌሎችም መሰል ጥያቄዎች መመለስ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

ዘመናዊው የሥራ አመራር ሂደት በተለይም አሁን ወደተሳትፎአዊው ምልከታ ያመዝናል፡፡ ይህን ምልከታ በርካታ የሙያው ታላላቅ ምሁራን መስክረውለታል፡፡ ይህንን ጉዳይ ማንሳቴ ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ህዝብ በእራሱ ላይ ሊወሰንበት፤ ሊተገበርበት ያለውን ነገር ማወቅ አለበት፡፡ ከማንም በላይ ቀድሞ ማወቁ ግድ ነው፡፡ ይህንን ማወቅና ማሳወቅ ደግሞ የመንግስት ድርሻ ነው፡፡ ውይይትም ሲደረግ ደግሞ ከባለስልጣናቱ ጋር ብቻ ሳይሆን ታች ወርዶ ከህዝቡ ነው መጀመር ያለበት፡፡ ወደድንም ጠላንም፤ ህዝብ ያልፈቀደው ነገር ተግባራዊነቱ ባያጠራጥር እን£ ቅቡልነቱ ጥያቄ ውስጥ ስለሚገባ አደገኛነቱ አብሮን ይዘልቃል፡፡ ስለሆነም ቆም ብሎ ማሰብ ግድ ነው፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ እርስዎ አባል የሆኑበት ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ለአሜረካ ድምጽ ራዲዮ በሰጡት ቃለመጠይቅ በተወሰነ ደረጃ ስህተቱን ማመናቸው (ሌሎች የሚነሱ ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው) ከመሪ የሚጠበቅ ማጽናኛ ቢሆንም፤ አሁንም ወደላ መለስ ብሎ ማሰብ እንደሚገባ ባለዎት አጋጣሚዎች ሁሉ ቢነግሩ፤ ብሎም ቢመክሩ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ጥያቄው ግን በቀና መንፈስ ለተመለከተው ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በቦታው ያሉት ገበሬዎች መፈናቀል በእርግጥም ያሳስባል፡፡ ገበሬዎቹን ብቻ አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ላይ ለመኖር ተፈትኖ ሲያበቃ ጥግ ፍለጋ ወጣ ያለውም ህዝብ ቢሆን፤ በልማት ሰበብ መገፋቱ የማይቀር ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ ከማንም በላይ ህመሙ ከእነዚህ ዜጎች በላይ ሊሰማው የሚችል ይኖር ይሆን? ወላጆቻቸው በመፈናቀል uፍ ላይ ያሉ ተማሪዎችስ እንዴት ዝም ብለው ሊማሩ ይችላሉ? የሆነው ሆኖ፤ አሁን ያለው ነገር መርገቡ ጥሩ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ለወደፊቱ የምናስቀረው ቂም እንዳይኖር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት ያለብን ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡


አክባሪዎ አብርሃም ተስፋዬ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ