ቅዳሜ 30 ኦገስት 2014

‹‹ከመቃወም ባሻገር›› ፩

ሕገመንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በተለይም በአሁኑ ጊዜ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ባለው ሥርዓት ደግሞ በቋሚነት (ሁልጊዜም) ሊታወስ የሚገባውና መዘንጋት የሌለበት በየትኛውም አጋጣሚ ሀገርን ወደፊት ለማራመድና ሀገርን እንደሀገር ለማስቀጠል የሚችል ሁነኛ አማራጭ የፖለቲከኞች ስብስብ (ፓርቲ) መኖሩ ነው፡፡ ይህ አማራጭ ደግሞ በደምሣሣው ‘ተቃዋሚ’ በመባል ይገለጻል፡፡ ምሁራንም እንደሚስማሙበት በበርካታ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶች ተቃዋሚዎች ያነሠውን ስብስብ ወይንም የመንግስትነትን ሥልጣን ያልያዙቱ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ እኒህ ተቃዋሚዎች ታዲያ መንግስት ራሱን እንዲፈትሽበት ምክንያት መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ በዚህ ጉዳይ ላይ ጋናዊው ፖለቲከኛና ቀደም ሲልም የጋና የጤና ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት አልባን ባግቢን (Alban Bagbin) በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ፡፡ እኚሁ ፖለቲከኛ የተቃዋሚዎችን ሚና አስመለክቶ በአራት ከፍለው ይመለከቱታል፡፡ የተቃዋሚዎች ሚና፡
ሀ. ‹‹ለድምጽ አልባዎች ድምጽ መሆን››
ተቃዋሚዎች በዋናነት መንግስት ሊተገበር ይገባዋል ተብሎ በህዝቡ የሚታመነውንና የሚያጉረመርምበትን ጉዳይ በማስተጋባት የመንግስትን ትኩረት እንዲያገኝ የማድረግ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚም የድምጽ አልባውን ህዝብ ድምጽ እንዲሰማ አንደበት ይሆኑለታል፡፡ ይህ ታዲያ ለመንግስትም ቢሆን ጠቀሜታው የትየለሌ ነው፡፡ የህዝቡን ስሜት ለማዳመጥ ያስችለዋል፡፡ የህዝቡን ፍላጎት ለመረዳት አማራጭ ነው፡፡ ይህ የተቃዋሚዎች ሚና ታዲያ የህዝቡን ልበሙሉነትና በራስ መተማመን ከማሳደግና ከማረጋገጥም ባሻገር ህዝቡ ስሜቱ፣ ፍላጎቱና እሳቤዎች በተገቢው መንገድ ለሚመለከተው አካል መቅረቡን ስለሚያስብ (ተግባራዊነቱ እንዳለ ሆኖ) ሀሣቡን በእነርሱ (በተቃዋሚዎች) በኩል ማድረሱን ራሱ እንደትልቅ ነገር ያየዋል፡፡
ለ. ‹‹ሁነኛ አማራጭ ሆኖ መቅረብ››
ቀደም ሲል ከላይ እንደገለጽኩት ሁሉ ህገመንግስታዊ ሥርዓትን በተገቢው መልኩ በሚተገብር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ሀገርን እንደሀገር ወደፊት ለማስቀጠል የሚችል የፖለቲከኞች ስብስብ (ፓርቲ) ይኖራል፡፡ ስለሆነም የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ታዲያ በዚህ አግባብ ሀገርን ለመምራት ራሳቸውን ሁነኛ አማራጭ አድርገው ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በተገቢው አኳኸን የተቀየሠ መሪ ዕቅድ (ስትራቴጂ) ቀይሠው እንሟገትለታለን፤ ችግሩንም ለመፍታት ብሶቱን ወደመንግስት እናደርስለታለን የሚሉትን ህዝብ በእርግጥም ሊመሩት እንደሚችሉ አምኖና ተቀብሎ ከጎናቸው እንዲሠለፍ በአንድም ይሁን በሌላ አጋጣሚ ተገቢ ነው የሚሉትን የህዝቡን ችግር ለመቅረፍ የሚችሉ ፖሊሲዎችን ከመቅረጽ ይጀምራል፡፡ የህዝቡን ችግሮች ታዲያ ህዝቡ ድረስ ቀርቦ በማጥናት የህዝቡን ፍላጎት በማጤን በጥናት ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ በርካታ አለምአቀፍ የፖለቲካ ተንታኞችም እንደሚያስረዱት የህዝቡን ችግር ለመፍታት በስሚ ስሚ ከሚደርሱበትና በእልህ ከሚነዱት ይልቅ በሰከነ መንፈስ የህዝቡን ስሜት ጠልቆ ለመረዳት የሚያስችሉት በእርግጥም አማራጭ ለመሆን እንደሚችሉ ያስረዳሉ፡፡
ሐ. ‹‹በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት መቃወም››
ተቃዋሚ የሚለውን ስያሜ ከዚህኛው ሚና የመነጨ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ ይህኛው የተቃዋሚዎች ሚና በርካቶች የሚተገብሩትና እንደአንዳንድ ምሁራን አስተያየት አደናጋሪው ነው፡፡ ምክንያቱም ተቃዋሚዎች በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት የመቃወም ሚና አላቸው ሲባል፤ ‹‹ተቃውሞው እስከምን ድረስ ነው?›› የሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ የትኛውም ህዝብ ጎድሎብኛል ለሚለው ነገር ምላሽ ለማግኘት ይሻል፡፡ በሀገሪቱ ያለውም መንግስት የህዝቡን ምላሽ ለመስጠት በቻለው መጠን ይተጋል (ተብሎ ይታሰባል)፡፡ ይህ የመንግስት ምላሽ የህዝቡን ጥያቄ በተገቢው መልኩ ካልመለሠ፤ ህዝቡ አማራጭ መፈለጉ ግድ ይሆናል፡፡
በእርግጥም ጥያቄውን የሚመልስለት የሚያዳምጠውና ሀገሪቱን እንደሀገር ለማስቀጠል የሚችል አማራጭ ሀይል መሻት፡፡ በዚህ የህዝብ መሻት ውስጥ ደግሞ የተቃዋሚዎች ሚና ሊሆን የሚገባው በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት መቃወም ነው፡፡ የመቃወም ‹‹ድንበር ልኬት›› በበርካቶች የተለያየ ርቀት ቢወሰድም ብዙዎች የተለያየ ትንታኔ ቢሠጡበትም የተቃዋሚዎች የመቃወም ዓላማ ጣሪያ ህዝቡን በማሳመን፤ የራሳቸውን ምርጥ (የሚሉትን) ፖሊሲዎች ለህዝቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ህጸጾችን ለህዝቡ ከማሣወቅ ባሻገር ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማሣወቅና በራሳቸው የፓርቲ አደረጃጀት ውስጥ በማስረጽ በህዝቡ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ማድረግና ህዝቡ እንዲመርጣቸው ከፍተኛውን ሥራ መስራት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ በምርጫ በሚያገኙት ስልጣንም ተጠቅመው ለህዝቡ ጠቃሚ ነው ያሉትን ፖሊሲዊች ማስፈጸም ይጠበቅባቸዋል፡፡
ይህም እውን እንዲሆን ተቃዋሚዎች  አለን የሚሉት ፖሊሲና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከሀገርና ህዝብ ጥቅም አንጻር በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት እየተገበርኩ ነው ከሚለው የተሻለ ስለመሆኑ በውስጥ አሠራራቸው የሚያሣዩት ዴሞክራሲ ብርቱ ማሣያ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ በዚህም ተቃዋሚዎች በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ሊሸፍናቸው የሚፈልጋቸውንና በህዝብ ትኩረት እንዳያገኙ የሚያደርጋቸውን እውነታዎች ማጋለጥና አማራጭ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ሚና ህዝቡን በተለይም ከሙስናና ብልሹ አሠራር ለመታደግ ይጠቅማሉ፡፡
ይህንን በመተግበር ተቃዋሚዎች የመንግስትን ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀምን፣ ቢሮክራሲ፣ የሠብዓዊ መብት ጥሰትን፣ የህዝብ ሀብትና ገንዘብ ብክነትን እና ሌሎችንም የህዝብ ጥያቄዎች በማሳጣትና ሂስ በመስጠት ሀገራዊ ቁጥጥር ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ ይቻላቸዋል፡፡
መ. ‹‹አዲሡ የተቃዋሚዎች ሚና››
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በሉላዊነት (Globalization) ጋር በተያያዘ የመጣውን አለማቀፋዊ የሠብዓዊ መብቶች፣ የነጸነትና መልካም አስተዳደር ጽንሰሀሳቦች ጋር በተያያዘ የተቃዋሚዎችም ሚና አንድ ደረጃ አብሮ ከፍ ማለት አለበት የሚሉ አተያዮች ብቅ ብለዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በሥልጣን ላይ ያሉ መንግስታት የሕግ የበላይነትን እና የሰብዓዊ መብትና ነጻነት መከበርን ማረጋገጥ በርክቶ የሚነሣባቸውና እንዲያረጋግጡ በተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶችና መንግስታት ጫናዎች ይበረክቱባቸዋል፡፡ ተቃዋሚዎችም ታዲያ ይህንን በመንግስት ላይ የተጣለ ኃላፊነት በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የመከታተል ቦታና ጊዜ የመስጠትና በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሥልጣን ላይ ካለው መንግስት ጋር በትብብር የመስራትና ሀገራዊ መግባባት እንዲኖር መስራት እንዳለባቸው ይታመናል፡፡
ይህ አዲሱ የተቃዋሚዎች ሚና በተለይም ለሠላም፣ ጸጥታና ዴሞክራሲ በጣም አደገኛ ሁኔታዎች ባሉባቸው ጊዜያት አብዝቶ ይጠበቃል፡፡ በሥልጣን ላይ ካለው መንግስት ጋር በምን ጉዳይ ላይ መግባባት ላይ መድረስ ተገቢ ነው የሚለውን ውሳኔ ማሳለፍ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ሁሉ በሚሆንበት ጊዜ ታዲያ ብሔራዊ (ሀገራዊ) እና ህዝባዊ ጥቅም በየትኛውም አጋጣሚ ለድርድር የሚቀርብ አይሆንም፡፡
የሀገሬ ተቃውሞ
በኢትዮጵያችን በርካታ የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ እኒህ ፓርቲዎች በተለያየ አጋጣሚ ብቅ ጥልቅ የሚሉትንም ይጨምራል፡፡ በቁጥር ከመበርከታቸውም በላይ በርካቶቹን የምናውቃቸው የምርጫ ሠሞን ነው፡፡ ምንም እንኳ አንዳንድ ብርቱ የሚባሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢኖሩም የምርጫ ወቅት ላይ ራሳቸውን ዕጩ በማድረግ ብቻ አሸናፊነት የሚናፍቁ በርካቶች ናቸው፡፡ ከላይ ያስቀመጥኳቸውን የተቃዋሚዎች ሚና እንደመስፈርት ወስደን እንለካቸው ብንል ምን ያህሉ ይሆኑ በእርግጥም የተቃውሞውን ጎራ በተገቢው መልኩ ከህዝቡ ፍጆታ እያዋሉት ያሉት? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ምናልባት አንድ በአንድ ብናየው መልካም ይመስለኛል፡፡

(ይቀጥላል)

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ