እሑድ 17 ኤፕሪል 2016

የኦሮሞ እናቶች ትርክት

‹‹እንወልዳለን! ወልደን ለሞት እነገብራለን! ከመንግስት ያለንን ሀሳብ የሚያዳምጥ፤ በእኛ ልክ የሚረዳን አጥተናል፡፡ እኛነታችንን ተነጥቀናል፡፡ ስለምን ዋጋ እንደምንከፍል አናውቅም፡፡ እኛም ስለምን እንዲህ እንደሆንን እንጃ! ብቻ ጭቆናው ብሶብናል፡፡ መዳበሪያ ፍለጋ መታተራችን ለጉድ ነው፡፡ ሙግታችን ነጻነት ነው፡፡ መብታችንን ፍለጋ ነው፡፡ እኛ ለምንኖርለት አላማ የሚኖሩ፤ ጭቆናን የማይታገሱ ልጆች ወልደናል፡፡ ብናልፍ ምን ይቆጨናል? ሞትንስ እንኳ ቢሆን ስለምን እንፈራዋለን? ልጆቻችንስ ቢሆን በጥይት አረር ከፊታችን፤ ከእጃችን ላይ ሲወድቁ አይተን የለም ወይ? ስለምን ኑሮንስ እንወዳታለን? የልጅን ሞት ያህል ነገር፤ የልጅን ደም ያህል ነገር፤ የልጅን ነፍስ ያህል ነገር እያዩ ማጣት ምንስ ቢመጣ ለመቀብ አያዘጋጅም ወይ? ሀገር ይፍረደና!››

እንዲሁ ሳስብ የኦሮሞ እናቶች እንዲህ ከላይ የገለጽኩትን የሚሉ ይመስለኛል፡፡ እኒህ እናቶች ታዲያ ጀግኖች ናቸው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ልጆቻቸውን እየገበሩም እንኳ እጅ ሊሰጡ አይደፍሩም፡፡ በፍጹም ተቃራኒ ከሆነ መንገድ አይሰለፉም፡፡ ልጆቻቸውን ስለፍትህ፣ ስለነጻነት፣ ስለእኩልነት ይሰብካሉ፡፡ ሰርተው፤ ሆነው፤ ተግብረው፤ ከውነውም ያሳያሉ እንጂ በቃል፣ በወሬ አይኖሩትም፡፡ የኦሮሞ እናቶች፡፡

በዚህች ሀገር ታሪክ ደማቅ ታሪክ ተጽፎላቸው ያሉ፤ ገቢራቸው ከሁሉ በላይ የገዘፈና የላቀ ሆኖ የሚታዩ በርካታ የኦሮሞ ልጆች አሉ፡፡ እኒህ ግብራቸው ከሁሉ በላይ የተቀመጡ ኦሮሞዎች ስለብሔራቸው ሲያነሱ/ሲናገሩ ሁሉም በጥርጣሬ ስለምን እንደሚመለከታቸው አይገባኝም፡፡ ክብራቸውን ክብሬ ነው ብሎ የሚቀበለው ሁሉ፤ ኢትዮጵያዊነታቸውን ብቻ እንዲሰብኩ፤ ከዛ ባሻገር ያላቸውን ማንነት እንዳይናገሩ የሚፈልግበት ሁኔታ ለእኔ ግራ ነው፡፡ በምንም መልኩ ይሁን፤ አንዳች እውነት ይዘን መነሳት ካልቻልን ይህ ሀቅ በፍጹም ልብ እውነተኛና ተዐማኒውን ኢትዮጵያዊነት አያመጣውም፡፡

ከሰሞኑን የኦሮሞ ልጆች ጥያቄ ጋር በተያያዘ በርካታ ነገሮችን እያየን፣ እየሰማን፣ እየታዘብንም ጭምር ነው፡፡ ገራሚ ሁነት፡፡ አስደናቂ ነገርም ነው፡፡ በጣም አስደንጋጭም ልንለው የምንችለው አይነት፡፡ ከላይ የጠቀስኩት ነገር፤ የኦሮሞ እናቶች ሊሉት ይችላሉ ብዬ ያሰብኩትን ቢሆን አይገርምም፡፡ እኒህ እናቶች ስለምን ልጆቻቸውን እንደሚገብሩ በደንብ የተረዱ ናቸው፡፡ ለእኔ ጥግ ይዞ መከራን ከሚቆጥረው በላይ የጀገኑ፤ አንደኛ!

እነዚህን እናቶች ለሚመለከት ሰው፤ እነዚህን እናቶች ለሚያስብ ሰው፤ እነዚህን እናቶች ለሚያውቅ ሰው፤  ስለምን ልቡ በጭካኔ እንዲሞላ እንደሚሆን አላውቅም፡፡ ስለኢትዮጵያ ‹አንድነት› ‹የሚሰብኩት› (እኒህ አካላት ውስጣቸው ያልጠራ መሠረታዊ ችግር እንዳለባቸው ይሰማኛል) አካላት ይህንን እውነት ስለምን ማደባበስ እንደሚፈልጉ፤ ስለምን ስለእነዚህ እናቶች በአንድም ሁነት ሊጨነቁ እንዳልፈለጉ፤ ስለህዝቡም ያላቸው እውነተኛ ስሜት እየተስተዋለ ያለበት ሁኔታ እንዳለ ለመረዳት ይቻላል፡፡

በኢህ ጉዳይ ላይ ዲ/ን ሙሉጌታ ወ/ገብርኤል የተባሉ ግለሰብ እ.ኤ.አ. 2013 ላይ የጻፉት ጽሁፍ ላይ ያሰፈሩትን ፍርሃታቸውን/ስጋታቸውን እዚህ መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ‹‹ከተራ ጩኸትና መፎከር ያላለፈ፤ መያዣና መጨበጫ የሌለው፤ ልብ አውልቅ ባለቤት ያጣ፤ ግልጽ የሆነ ራዕይና ግብ የሌለው፤ የተዘበራረቀና የተምታታበት፤ አይደለም ሰፊው ሕዝብ ለአንድ አላማ ሊያሰልፍ፤ ሊያሳምንና አግባብቶም ከጎን ሊያስከትል ቀርቶ እርስ በርስ መስማማትና መደማመጥ ያቃታቸው የሥመ ፖለቲከኞቻችን …. በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ፤ ጊዜያዊ ኃይማኖታዊና ማህበራዊ ጥያቄዎችና አለመግባባቶች …. ሳስብው ኢትዮጵያዊያን እስከ ዳግም ምጽዓት ድረስ የሚያስፈልገንን ሳናገኝ እንዲሁ እንደጮኽን፤ እንደናፈቀን….እንዳናልፍ እፈራለሁ››

‘Pseudo Ethiopians’

እውነት ለመናገር ስለኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያዊነት ያሉት ትርክቶች በሙሉ በአንድ ዥረት ብቻ እንዲፈሱ የመፈለጉ አዝማሚያ ከበርካታ ወገኖች የሚመላለሰው፤ አጉል መሀለኝነትን ለመከተል በማሰብ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከሁሉ በላይ ሊያስማማን የሚችለውና፤ ከማንም ጋር ሳያሻክር ሊያኖር የሚችለው ነገር ይህ ነው ብለው የሚያምኑ፤ ለራሳቸው ሀሳብ የማያድሩቱ ግብዞች የሚመርጡት ሀሳብ ይመስለኛል፡፡ በውስጣቸው የሚያስቡትና ከልብ የሚተጉለት ሌላ አጀንዳ እያላቸው፤ እነርሱ ግን የሚፈጽሙት ሌላ (በጣም ሌላ) ግብር ሆኖ ይታያል፤ ይህ ደግሞ በተለይም በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በሚሳተፉና፤ በሌላም ሁኔታ ለፖለቲካዊ እንቅስቃሴው ቅርብ ነን በሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ሲዘወተር ይስተዋላል፡፡

ኢትዮጵያ እንደሀገር፤ ሀገር ሆና እንድትቀጥል በእኔ እምነት እውነቱን መቀበል እና መዋጥ ግድ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የሚያደርጋት፤ በመጨፈላለቅ ላይ የተመሰረተ አንድነት ነው ብዬ አላምንም፡፡ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ እያሉ መደንፋት ብቻም ነው ብዬ አልቀበልም፡፡ የእውነት ከልብ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ብሔሮችና ብሔረሰቦች እውነት ተቀብለን ሊሻር የማይችለውን ለማቻቻል፣ ይቅርታ የሚያጠያይቀውንም ተጠያይቀን በግልጽ ስንነጋገረው ብቻ ነው፡፡ ሀገር ልታድግ፣ ሀገር ልትገነባ የምትችለውም እንዲህ ሲሆን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

እምነትና ጽናት ይስጠን እንጂ እውነቶችን ለማደባበስ በምንሞክርበት ወቅት እየከፈልን ያለውን ዋጋና፤ እያደረስን/እያኖርን ያለውን የነገ ጦስ በጊዜው ምንደርስበት ይመስለኛል፡፡ ታሪክ ዐዋቂዎች የሚሰሩት ስህተት፣ ታሪክ ተናጋሪዎች ከሚሉት በላይ ነው፡፡ የኖረው ህዝብ እያለ፤ አጥኚው ነኝ ባዩ ‹አንበሳ› መስሎ የሚታይበት ሀገር ነው ይሄ! ‹‹የምጣዱ እያለ……….›› እንዲሉ፡፡
ታሪክ በበርካቶች ተጽፎ ይገኛል፡፡ ብዙዎችም እንዲህ ነው፤ እንዲያ ነው እያሉ ዘግበዋል፡፡ ዜና መዋዕሎችም ለምስክርነት ቀርበዋል፡፡ ጎብኚዎችም ሳይቀሩ የጻፏቸው ድርሳናት ተገላብጠዋል፡፡ ንጉሶች ስለራሳቸው ያስጻፏቸውም ደርዞች በርክተው እንዲጠቀሱ ሆነዋል፡፡ (ነጋድራስ ገ/ህይወት ባይከዳኝ ታሪክ እንዴት ሊጻፉ እንደቻሉ ያነሳው ሀሳብ እዚህ ጋር ልብ ሊባል ይገባዋል)

ከኦሮሞ ህዝብ

ስለኦሮሞ ብዙ ተጽፏል፡፡ እኔ በዚህ ላይ የምጨምረው ብዙ አይኖርም፤ አስፈላጊ ከሆነ ወደፊት የምናጣቅሳቸው ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን፤ ‹‹ኦሮሞ ግንድ ነው›› ይህ የጄ. ጃገማ ኬሎ ንግግር ነው፡፡ በአንድ ወቅት ‹ፋክት› መጽሔት ላይ የሰጡት ቃል፡፡ ይህ ግንድ ነው እንግዲህ አሁን መፍለጫ የበዛበት፤ ሊቆርጡት የሚታገሉት ብዙ ናቸው፡፡ የሚታትሩት በርካቶች ናቸው፡፡ ትግሉን ለማኮላሸት የሚሹት ምክንያታቸው እንኳ ግልጽ አይደለም፡፡ ‹ስጋት› ነው፡፡ ተራ ስጋት፡፡


ስጋት ለምን?
በዘመን አዙሪት ዛሬ ላይ ከመድረሳችን በፊት ይህ ህዝብ እንደህዝብ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ለመኖር ሞክሯል፡፡ ሙከራ ብቻም አይደለም፤ አድርጎታልም፡፡ የኦሮሞን ጥያቄ (ማንኛውንም ጥያቄ ማለት ነው) በፍጹም ቀናኢነት ለመቀበል የሚያንቃቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች ስንመለከት፤ በርካታ ናቸው፡፡ በተለይም አንዳንድ ጊዜ እነርሱ ወደፊት የሚያስቡትን ነገር ፍንትው አድርጎ ሊያሳይ በሚችል መልኩ ጥያቄውን ለመሞገት ሲሞክሩ ይስተዋላሉ፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ውጤት ናት፡፡ ኢትዮጵያ ሲባል ህዝቡ ነው፡፡ ተራራና ሜዳው ብቻ አይደለም፡፡

ኦሮሞም እንደህዝብ የዚህ ሀገር ጉዳይ ያገባዋል፡፡ የዚህ ሀገር ነገር ይመለከተዋል፡፡ ይህ ማለት ታዲያ ኦሮሞን መቀበል በሚያቅታት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደማይሆን መጠርጠር አያሻም፡፡ ያገባኛል የሚባለው በሚመለከት ነገር ላይ ነው፡፡ ኦሮሞ ጥያቄ ሲያነሳ በሚበረገግበት ሁነት ውስጥ፤ እንዲህ ያሉ የህዝቡ ጥያቄዎች በሙሉ በጥርጣሬ እንዲታይ በሆነባቸው ሁነቶች ውስጥ በአንድ ስለመሆን ማሰብ ከባድ ሊሆን እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡

ኦሮሞን እንደህዝብ የዚህች ሀገር አካል፣ ባህሉም የኢትዮጵያ ባህል፤ ቋንቋውም እንደበርካታ ተናጋሪ ህዝብ ባለቤትነቱ የሚገባውን ቦታ አግኝቶ፤ ውክልናው በሚገባው ደረጃ እንዲሆን ሁሉም ሊሰራ ግድ ነው፡፡ ‹ተራ› ስጋቶችን በየሁነቱ እያነሱ የኦሮሞን ህዝብ ከማስከፋትና፤ በተለይም እንደህዝብ የሚደርስበትን በደልና ስቃይ አብሮ መካፈል የሚችል አመለካከትና ህሊና ሊኖረን ግድ ነው፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ፤ አንድነት የሚባል ነገር ዝም ብሎ እየደሰኮሩ የሚመጣ አይመስለኝም፡፡ በመከባበርና፤ በመተዋወቅ ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲ፤ እውነቱን አደባብሰን የምንዘምረው ‹አንድነት› አሁን ካለው አካሄድ ብዙም ልዩነት ያለው አይመስለኝም፡፡

ስለሆነም፤ የኢትዮጵያን አንድነት ስናስብ፤ በእርግጥም ባህሉን፣ ቋንቋውን፣ ማንነቱን፣ ሁለመናውን አምና የምትቀበል፤ በዚሁም እንደህዝብ የሚገባውን ቦታ አግኝቶ ሊኖር የሚችልበትን ሁኔታ የምታመቻች ሀገር እንዲኖሩ መሻት ተገቢም አስፈላጊም ይመስለኛል፡፡ በአንድ ወገን ትግልና ደም ብቻ የምትቆም፤ በአንድ ወገን የምትደምቅ ብቻ ሀገር የምትሹ ካላችሁ እርሱ በፍጹም ሊታሰብ የማይገባው ሀሳብ እንደሆነ አበክሬ ለመንገር እወዳለሁ፡፡

የእነዚህ የኦሮሞ እናቶች እንባ፣ መቀነታቸውን ጠበቅ ያደረጉበት ስሌት፤ ልጆቻቸውን የከፈሉበት ሁነት ግን በሁላችንም ልብ እንዲኖር ግድ ነው፡፡ ስለመሞትማ ከእነርሱ በላይ፤ ትግል ሜዳ ላይ ስለሚኖር ከፍታና ዝቅታማ ከእነርሱ ወዲያ እስኪ ማን?
ክብር ለኦሮሞ እናቶች!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ