ጋዜጠኝነት፣ ጽንፍና
ኢትዮጵያ
(ሙያ፣ ወገንተኝነትና ሀገር)
፩
የህዝብ ልሳንና አንደበት መሆን መታደል ነው፡፡ የህዝብን ብሶትና ምስጋና ለማስተጋባት
ያለአንዳች ሀፍረት በእውነት ለእውነት ለማቅረብ መመረጥም እንዲሁ ነው፡፡ ህዝብ ብዙ ያስባል፡፡ ህዝብ ብዙ ይመኛል፡፡ ህዝብ የመበርከቱን
ያህል ሀሳቡም እንዲሁ ሊሆን ግድ ነው፡፡ የተለያዩ ሀሳቦች፤ የተለያዩ ምልከታዎች፤ የተለያዩ እውነቶች፤ የተለያዩ ማንነቶችም ጭምር፡፡
በእነዚህ ውስጥ ታዲያ የህዝብ አንደበት የመሆን አደራ የሚጣልበት፤ በተለይም አንደበታቸው ለተያዘ/ለተገታ ብርቱ አንደበት የመሆን
ድርሻ የሚጣልበት፤ አደራውን በግብሩ እንዲያሳይ የሚጠበቅበት አንዳች ባለሙያ አለ፤ ጋዜጠኛ፡፡
ጋዜጠኝት ያለውን እውነት ተቀብሎ ለህዝብ መልሶ የማቅረብ፤ ብሎም ህዝቡ የሚያነሳቸውን
ጥያቄዎች የማስተጋባት፤ አዲስ የተፈጠሩ ክስተቶችን የማሳወቅ እና አድማጭ፣ አንባቢውና ተመልካቹ በሚመለከቱት ጉዳዮች ላይ የበቃ
መረጃ እንዲኖረው ለማድረግ የሚከወን ሙያ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ታዲያ የአድማጭ፣ አንበባ ወይም ተመልካቹን ቀልብ ለመግዛትና የእርሱን
ሀሳብ እያስተጋባ እንዳለ ለማሳወቅ፤ ጋዜጠኛው ብርቱ ፈተና ይጠብቀዋል፡፡ እንዲህ ባለውም ጊዜም ስህተቶች እንዳይከሰቱ የጋዜጠኝነት
መሠረታዊያንን ጠንቅቆ መረዳትና መጠበቅ ግድ ይላል፡፡
እኒህም የጋዜጠኝነት መሠረታዊያውን የተለያዩ ጸሐፍት በተለያየ ቁጥር ቢያስቀምጧቸውም፤
በዋናነት ግን ገለልተኝነትና፣ በእውነት ላይ የተመሰረቱ መሆንን፣ ሚዛናዊነት ወይም ከወገንተኝነት መጽዳትን እና ገለልተኝነትን፣
የተለያዩ ሀሳቦችን ወይንም ምልከታዎችን ማስተናገድን፣ ከህዝብ ጋር መቀራረብን ብሎም ቁርኝት ያለውን ጉዳይ በትኩረት መስራትን በዋናነት
ሁሉም ይስማሙባቸዋል ለማለት ይቻላል፡፡
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ ጽሁፎች እንደሚያስረዱት ከሆነ፤ ጋዜጠኞች ኦፊሴላዊ
የሆኑትን መረጃዎች እንደወረዱ መቀበል የለባቸውም ብለው ይከራከራሉ፡፡ ጋዜጠኞች የህዝብ አይንና ጆሮ ናቸው፡፡ ስለሆነም ሁሉንም
ነገር እንዲጠይቁ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም በስልጣን ላይ ያሉትን፡፡ ምክንያቱም ስልጣናቸውን ለማቆየት/የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም
ሲሉ ያለውን እውነት እነርሱ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ ዘወር አድርገው ስለሚያቀርቡት፡፡ ስለሆነም ጋዜጠኞች ጠንካራና በሳል ጥያቄዎችን/መጠይቆችን
በማቀረብ ሁነቱን ለህዝብ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ጋዜጠኞች ስለሚጠይቁት ጉዳይ መለስተኛ ዳሰሳ በማካሄድ ተጠያቂዎች
በፍጹም የማይፈልጉትን አይነት መጠይቆች ማንሳታቸው ይጠበቃል፡፡ ይህ ሁሉ እንዲሆንም የጋዜጠኛው ተገቢ የሚባለውን አስተሳሰብ ተላብሶ፤
ሁለንተናዊ ዝግጁነቱን ጠብቆ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡
ሙያዊ ስነምግባራትን ጠብቆ፤ ከወገንተኝነት በጸዳ መልኩ ሥራዎችን ማከናወን ከየትኛውም
ጋዜጠኛ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ጋዜጠኛው ወደደም ጠላም፤ ሁኔታው እርሱን (በግል) ይመልከትም አይመልከትም ነጻ ሆኖ ሁኔታዎችን
ለህዝብ፤ የማድረስ ግዴት ይጣልበታል፡፡ ይህንን ግዴታ ነው እንግዲህ በቅጡ መወጣት የሚገባው፡፡ በዚህ መካከል ታዲያ እንቅፋቶች
ይጠፋሉ ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከጋዜጠኛውም አቅም በላይ የሆኑ እርሱን በጣም ሊፈትኑ የሚችሉ ነገሮች ሊገጥሙት እንደሚችሉ
ይገመታል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሁኔታዎች በጥንቃቄና የሙያውን ክብር በጠበቀ መልኩ ማለፍ ይጠይቀዋል፡፡
በተለያዩ ሀገሮች ጋዜጠኞች ይዋከባሉ፡፡ ጋዜጠኞች ላይ እንግልት ይደርሳል፡፡ ድብደባውም
አይቀርም፡፡ ጥድፊያውም እንደዚያው ነው፡፡ በአንዳንዶች ላይ የሚኖረው እምነት ሠፋ ያለ ነው፡፡ አንዳንዶችም አይታመኑም፡፡ አንዳንዶች
በዕውቀት ይሰሩታል፡፡ አንዳንዶችም በድፍረት፡፡ ማይክራፎኑንና አየር ሞገዱን ስላገኙ ብቻ ጋዜጠኛ የሚባሉ፡፡ ብዕርን ከወረቀት አዋደድኩ
ብለው፤ አንባቢ ነኝ ብለው ስለሚያስቡ ነገሮችን አጣቅሰው ስለጻፉ ብቻም ጋዜጠኛ የሚል ማዕረግ የተጫነላቸው አሉ፡፡
(ይቀጥላል)
ሚያዚያ 01 ቀን
2007 ዓ.ም.
© አብርሃም ተስፋዬ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ