"እኛም
አለን ሙዚቃ"
“እናንት በዚያ ያላችሁ ሆይ! እነሆ እርቃናችሁን ትሆኑ ዘንድ የተፈቀደ፤ ወንድሞቻችሁንም
በወሲብ ፍላጎት ትፈትኑ ዘንድ የተወደደ ቢሆን ጊዜ ይኸው እርቃን መሆናችሁ ተፈቀደ’’ የተባለበት ቦታ ያለ መሰለኝ፡፡ ከዚህ ከአዲስ
አበባ አንዳች ነገር ገብቶ ይሆናል፡፡ እርቃን መሆን ሳይፈቀድ አልቀረም፡፡ ግን ስለምን እንዲህ እንዲሆን እንደተፈረደ/እንደተፈቀደ
አላውቅም፡፡
ከቅርብ ወዳጄ ጋር ጫማችንን ለማስጠረግ ከአንድ ካፍቴሪያ በር
ላይ ቁጭ ብለናል፡፡ ከእኛ በስተግራ አቅጣጫ ሁለት ሴቶች ይመጣሉ፡፡ ለአቀማመጣችን ከታች ወደ ላይ አይነት ጉዞ ነው፡፡ ሁለቱም
በጣም ያጠሩ ቀሚስ መሰል ጨርቆችን በላያቸው ጣል አድርገዋል፡፡ ብጣሽ ጨርቅ ነገር ልበልው ይሆን?
እንደ"ሽሮፕ"….
እያወሩ ነው፡፡ ምን እንደሚያወሩ በግልጽ አይሰማም፡፡ ስለሆነም እርሱን መገመት ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን እንቅስቃሴያቸው
ጤነኝነት ካለው አላውቅም፡፡ በተለይ አንደኛዋ ትውረገረጋለች፡፡ እየሄዱም ይደነሳል፡፡ በመንገድም ለካ ውዝዋዜ አለ፡፡ ንቅናቄዋ
መስመር ያለፈ አይነት ነው፡፡ ይህ ዘመንኛው የእነእንቶኔ <ድመታዊ> አካሄድ ከሆነ ብዬም አሰብኩ፡፡ (ሞዴል ምናምን ነን
የሚሉት ወ……. ያመጡብንን ነገር እያሰብኩ ነው፡፡ በቅርቡ እንደውም በብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ የተመለክቱት
ነገር ትውስ አለኝ፡፡ ወደታች እመለስበታለሁ፡፡) ነገር ግን ከእርሱም ለየት ይላል፡፡ ይህንን ስል በእርግጥም በእዚህች ሴት ላይ
ብቻ አይቸው አይደለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተመለከትን ያለውን ሰውነትን እንደ አዲስ ሽሮብ የመበጥበጥ አካሄድ በሴቶቻችን ዘንድ
እንደልማድ እየተወሰደ ያለና በጣም በብርቱ እየተከተሉት ያለ ነገር ስለሆነብኝ ነው፡፡ በእርግጥ ከበርካቶችም ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ
ሳወራ እንዳስተዋሉት ለመረዳት ችያለሁ፡፡ በጉዞዋ ላይ……… ግን እንደው ልክ የምትቀመጥበት አልያም ሌላ ማረፊያ ስታገኝ እንዴት
ልትቀመጥ እንደምትችል አሰብኩት፡፡ አንዳንድ ጊዜም ምናልባትም አንዳንዶች ከካፊቴሪያዎች ቶሎ የማይወጡት እንዲህ ባለው አካሄድ የተነሳ
ድካም ገብተው፤ እረፍት ከመሻት የመነጫ ይሆን? እየሄዱም መንቀጥቀጥ.....
ለወላጅ ማፈሪያ
አፍታም አልቆየም ሌላ ደግሞ ትዕይንት፡፡ እምብረትና ጡት መለየት የተሳናት
አይነት አንዲት ራቁት ደግሞ መጣች፡፡ ራቁት ነው፡፡ ምንም ልብስ የለም፡፡ ከወገብ በላይ አንዲት ቢጢል ያለች የሆነች ነገር ብቻ
ጣል አድርጋለች፡፡ በጣም ገራሚ አይነት ነው፡፡ ወዳጆችዋ አብረዋት አሉ፡፡ አይ ዘመናዊ ወዳጅ! እንዲህ ያለውንም ለማረቅ ጊዜ የሌለው
አይነት፡፡ የሚያስጠላውን ለመንገር የማይደፍር፡፡ የማይመርጥም፡፡ብኩን ወዳጅ፡፡ እርቃነ ስጋዋን በአሸናፊነት መንፈስ (መንፈስም
ቆሌም ሞራልም ያላት አይመስለኝም) ትንቀሳቀሳለች፡፡ በእርሳ ውስጥ ደግሞ ያለው የራስ ክህድት ከባድ ነው፡፡ (ራስን መካድ ማለቴ
በእምነት ቢሆን የሚወደደውን አይደለም፡፡ ራስን አለመሆንን ለመግለጽ እንጂ)፡፡ በራስ መተማመን እንዳልለው እርቃን መታየት……ስልጣኔ
እንዳልለው ልብስ እያለ አለመልበስ……. ማወቅ እንዳልለው ብርዱም…….አለማወቅም እንዳይሆን ሌሎች አብረው አሉ……. ግራ ነው፡፡
በዚህም ቅጽበት አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች የሚሉት ነገር ትውስ አለኝ፡፡ አሰዳቢ፡፡
ወዳጅማ ቢኖር እንዲህ ባለው እብደት ውስጥ ባንገኝ፡፡ እራስንም ትቶ ሌሎችን
ስለሚሆነው በእርግጥም ትክክለኛውን መንገር፤ መምከርና መገሰጽ ያስፈፈልግ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል አልሆነም፡፡
"ትዳር ማለት"
በአንድ ወቅት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ፤ የስነ ጾታና ተዋልዶ ስልጠና ይሰጣቸው
ተብሎ ከምንማርበት ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ኮሌጅ ተገኝተናል፡፡ ሥልጠናውን የሚሰጡን ዶክተር ሴት ናቸው፡፡ (አሁን ለጊዜው ስማቸውን
አላስታውሰውም):: “ትዳር ማለት ምን ማለት ነው?” ብለው ጠየቁ፡፡ “ትዳር ማለት ክቡር ነው፡፡……… ትልቅ የሆነውን ሀገር ለመመስረት
የምንጀምረው እዚህ ነው፡፡ …………” እና ሌሎችም ሰፋ ያሉ ሀሳቦች ተንሸራሸሩ፡፡ ተማሪዎች ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ዶክተር ምላሹን ይመዘግባሉ፡፡
ትዕይንቱ ቀጠለ፡፡ በመጨረሻም ሀሳቦችን ሰብስበው ሲጨርሱ፡፡ “ያላችሁት ሁሉ እውነት ነው” አሉ ዶክተር፡፡ “ግን ቀለል ባለ ሁኔታ
እወቁልን፤ ወሲብ በእኔና በእርሱ/በእርሳ መካከል መሆኑ አይግረማችሁ፡፡ አርግዛም ብታይዋት አትደነቁ ማለት ነው፡፡ ማሳወቂያ ነገር፡፡
እውቅናን የመሻት ጉዳይ ነው፡፡” ብለው መለሱልን፡፡ ይህ እንግዲህ በወቅቱ በነበረው ስልጠና የተሰጠው ትርጉም ነው፡፡
መሠረታዊው እውነት ታዲያ እውቅናውን ማህበረሰው ይሰጣል ማለት ነው፡፡ ይህ
ማህበረሰብ የሚሰጠውን እውቅና ግን ማዋረድ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ማርገዝ ከትክክለኛው ሰው ከሆነ ክብር ነው፡፡ የትውልድን ቀጣይነት
የምናረጋግጥበት ጸጋ፡፡ ለብቻ በሚሆን የተዘጋጀ፡፡ የተሰናዳ፡፡ ክብርን የሚሻ፡፡ የሚገባውም ሁሉ ነው፡፡ መጸነስ፡፡ ይህንን ጸጋ
ማዋረድና ማራከስ ግን የአንዳንድ ሴቶች ግብር ከሆነ ሰነባበተ፡፡ በተለይ በተለይ……. እነ እከሌ፡፡ ራቁት ለመሄድ በጣም በቀረበ
አለባበስ እርግዝናቸውን ቆሌ አሳጥተው ክብረቢስ ያደረጉ ሴቶች በከተማው አሉ፡፡ ፋሽን ነው በሚል ይሁን አልያም በሌላ እንዲህ ያለውን
ዋልጌነት መከተል ጤንነት አይመስለኝም፡፡
በአንድ አጋጣሚ በተወሰኑ አመታት በፊት ያገጠመንን ጉዳይ ላጫውታችሁ፡፡ አዲስ
አበባ፡፡ አንዲት ወዳጃችን አርግዛለች፡፡ እናም የማታ ትምህርት ትከታተል ነበርና አንዳች ሰፋ ያለ ለእርጉዝ ሴቶች የሚሆን ልብስ
ብቻ ለብሳ ወደ ትምህር ቤት ትመጣለች፡፡ ከላይ የሚለበሰውንና ሱሪውን ለብሳ ደብተር ይዛ፤ በመንገዱ ሰከም ሰከም እያለች ሳለ፤
“ውይ!” አንዲት ሴት ቁጣና እልህ በተቀላቀለበት ሁኔታ ይገላምጡዋታል፡፡ ደነገጠች፡፡ “ምነው እንዲህ ክብር አሳጣችሁት?” ሴትየዋ
ጠየቁ፡፡ “ምናለ እንደው ትንሽ ሻርፕ ብትደርቢ፤ በይ እንኪ ይህንን ሻርፕ” ሴትየዋ ሻፓቸውን አወለቁ፡፡ “ቀልብ የላችሁ መቼም፡፡
ሸፈን ይደረጋል፡፡ ነውር ነው፡፡” ብስጭት ብለው ሄዱ፡፡ ሁሌም የሴትየዋ ነገር ይገርመኛል፡፡ ምናልባት እንደሌላው ሰው ዝም ብለው
ተገርመው፤ በውስጣቸው ተሳድበው ማለፍ ባለመፈለጋቸው ይሆናል፡፡ እናትነታቸው ላቀብኝ፡፡ ሁሌም አስባቸዋለሁ፡፡ በተለይ እንዲህ ያለውን
ነገር ሳይ፡፡ ዛሬ ደግሞ ያሉትን እርጉዞች ሲያዩ (በተለይ አንዳንዶቹን) ምን ይሉ ይሆን/ነበር?
እማማ እኔ ደግሞ በተለይ ባለፈው ያዩሁዋትን አልነግርዎትም፡፡
የእርግዝና መቅለል
እርግዝና የምን ውጤት እንደሆነ መደስኮር ቁብ አይሰጥም፡፡ በየትኛውም አግባብ
እንካ ቢሆን፤ በልጅነታችን ጀምሮ ስለነገሩ እንዲህ ነው ተብሎ ማውራት ስለማይቻል ቃላት ተመርጠውለት ይጠራል፡፡ በጣም በርክቶ የሚሰማው
ግን የባለጌ ነገር የሚለው ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያዊያን አተያይ ነው፡፡ እኛም ብንሆን የዚህ ማህበረሰብ ውልድ በመሆናችን፤ ወሲብ
ለእኛ የብልግና/የባለጌ ነገር ነው ማለት ነው፡፡ ይህንን የባለጌ ነገር ደግሞ ማንም አያበረታታውም፡፡ ስለሆነም በግልጽ የሚፈጸም
ሆኖ አይታይም፡፡ ነውርም ነው፡፡ ስልጣኔው እዛ እስኪያደርሰው ድረስ፡፡ (ይህንን ስል ታዲያ አንዳንድ ስነምግባር የጎደላቸው ነውርን
አያደርጉም ማለቴ አይደለም፡)
ይቀጥላል፡፡
ተጻፈ ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ሌሊት 8፡00 ሠዓት
© አብርሃም ተስፋዬ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ