ሐሙስ 25 ሴፕቴምበር 2014

ወይ አንቺ!

‹ደግሞ በእድሜሽ እንጣላ?›

ሠሞንኛ አጀንዳ ሆነሻል፡፡ በርካቶች እድሜሽን ሲጠይቁ እየሠማሁ ነው፡፡ አንዳንዱም ታሪክ ቀመስ ጉዳዮችን አክሎ ‹‹ይኸውላችሁ እወቋት የሚባለው ሁሉ ውድቅ ነው›› ይላል፡፡ ሌላውም ይህንኑ በመንተራስ ‹‹እርሱን በፍጹም አትስሙ/አትመኑ፤ እውነቱ ይህ ነው›› ይላል፡፡ ብዙ ጽሁፍ፡፡ በዚህ መካከል ነው ታዲያ የፌስቡክ ወዳጄ ሽንቁጥ አየለ ‹‹ኢትዮጵያዊ ውህድ ህዝብ ነው? የጋራ ኢትዮጵያዊነት ማንነት ያለውስ ህዝብ ነው?›› ብሎ የጠየቀበትን ጽሁፍ ያየሁት፡፡ እናም አነበብኩት፡፡ አንብቤም ዝምታን ለመምረጥ ተቸገርኩ ስለሆነም እንዲህ እጀምራለሁ፡፡ በቅድሚያ ግን ምስጢር፡፡

እንዳይገርምሽ፡፡ አንቺ ማለቴም እንዳይከፋሽ፡፡ በ‹አንቺ› የሚጠራኝ ይጠየቅልኝ ካልሽ ዘላለምን (ዘላለም ክብረት) ጠይቂው፡፡ ለምን አንቺ እንዳለሽ በቅርቡ ከእስር ቤት ጻፈው በተባለ ጽሁፉ ተንትኖልን ነበር፡፡ እንደውም ‹ይድረስ ላንቺ› ብሎ የጻፈልሽ ደብዳቤ፡፡ መቼም አንብበሽዋል አይደል ኢትዮጵያ? እኔም ተቀበልኩትና ‹አንቺ› አልኩሽ፡፡ አንቺ ደግሞ! አንቺ!
ሸንቁጥ አየለ በጽሁፉ በርካታ ነገሮችን አንስቶ ነግሮናል፡፡ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ፡፡ በእርግጥ ጥቂት የማይባሉ የቃላት ግድፈቶች ያዝ አላደረጉኝም ለማለት አይደለም፡፡ ቢሆንም አንብቤዋለሁ፡፡ ስላንቺ እድሜ ጀመረና፤ ስለማንነትም አንስቶ ውህደትን ሰበከ፡፡ መልካም ሀሳብ ይመስላል፡፡ ነገር ግን አቀራረቡ ትንሽ ተቀላቀለብኝኛ ነው፡፡

‹አንቺ ደግሞ እድሜሽ?

በእርግጥ በእድሜሽ ዙሪያ በርካታ የተዘበራረቁ እይታዎች እንዳሉ አንብቤያለሁ፡፡ እናም ይህንኑ ለመረዳት ሞክሬያለሁ፡፡ ክርክሮችም አሉ፡፡ በእድሜሽ ልኬት መጠን ላይ ብዙዎች የራሳቸውን ማሳመኛ እያነሱ ይከራከራሉ፡፡ በእውነት ግን እድሜሽ ስንት ነው?

እኔ ሳስብ አንቺነትሽን ለመውሰድ በእርግጥም የተወሰኑ የኋላ ታሪክሽን ማንሳት ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እርሱን ደግሞ ካነሳን፤ ከድሮ ጀምሮ ስንማር እንደመጣነው እውነት ለመናገር አርጅተሻል፡፡ የነአክሱም፤ የነላሊበላ፤ የነጀጎል፤ የነፋሲለደስ፤ የነሼከነሁሴን፤ የነአዋሽ መልካ፤ የነጃሺ፤ ………………………………… ታሪክ ማገላበጥ ምናልባት ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡

ዕድሜሽ ታዲያ ክርክር ውስጥ የሚገባው አሁን የያዝሽውን ቅርጽ አስመልከቶ ከሚሰጡት ማብራሪያዎች በመነሳት ነው፡፡ ‹ይህንን ቅርጽ የያዘው በዚህ ወቅት ነውና እድሜሽ እዚህ ላይ ነው› ብለው አንዳንዶች በመቶዎች ብቻ የተወሰነ እንደሆንሽ ይናገራሉ፡፡ እኔ ደግሞ አሁን የያዝሽን ቅርጽ የያዝሽው የግዛት ማስፋፋትን ተከትሎ ቢሆንም እንኳ ያው አምነሽ የተቀብለሽው የራስሽ ታሪክ ከሆነ፤ ነገር ከውልደት ይጀምራልና እድሜሽ ሄዷል አሮጊት ነሽ እልሻለሁ፡፡ በዚህም እርጅናሽ እስማማለሁ፡፡ እድሜሽ የበረከተ ነው፡፡ የሆንሽ ባለብዙ እድሜ ነገር ነሽ፡፡ ነገር ግን አባቶች የሚሉትን ልዋስና ከእድሜሽ አልተማርሽም፡፡ ነገር ግን በእድሜሽ ልክ አይደለሽም፡፡ ነገር ግን እንደእድሜ እኩዮችሽ አይደለሽም በታናናሾችሽም ልክ ለመሆን ገና ገና ይቀርሻል፡፡

ታሪክሽ

ከእድሜሽ ጋር ተያይዞም ታዲያ ታሪክሽ እንደተፈለገው የሚጠመዘዝ አይነት ነው፡፡ ሁሉም ያሻውን የሚልሽ፤ ሁሉም በልኩ ሊሰፋሽ የሚችል አይነት ነሽ፡፡ ደግሞ እኮ የሚገርመው ዝምታሽ!
በአንቺ ዝምታ ውስጥ ትዝብት ይታያል፡፡ በዝምታሽ ውስጥ ንቀትም አለ! ዝምታሽ አንዳንዴ ያስፈራል፡፡ ዝምታሽ አንዳንዴ ያስጠላል፡፡ ዝምታሽ………….በዚህ ብርቱ ዝምታሽ ውስጥ ደግሞ ታሪክሽን እናውቃለን የሚሉ እንዳሻቸው ሲያደርጉት ይስተዋላል፡፡

ሸንቁጥ ታዲያ ለጽሁፉ የጠቀሳቸው ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስኃቅ በአንድ ወቅት (ወቅቱን አልጠቀሰውም) ‹የማንነት ግጭት ውስጥ የገባው የዚህ ዘመን ትውልድ› ብሎ በገለጸው የእኛ ትውልድ አባላት ኢትዮጵያ ያላትን እድሜ አስመልከቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሰጡት ያለው መልስ እንዲህ የሚል ነበር፡-

‹‹ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ10ሺህ አመታት በላይ ነው፡፡ በዚህ ረዥም የታሪክ ሂደት ውስጥም የኢትዮጵያ ህዝብ ውህድና የጋራ መሠረታዊ እሴት ያለው ህዝብ ነው…››

እንደሸንቁጥ ጽሁፍ ከሆነ ፕሮፌሰሩ ንግግራቸው በዚህ አላበቃም፡፡ ‹‹የአሁኑ ትውልድ ታሪኩን በደንብ ከመረመረ በርካታ የሚያስተሳስረው አኩሪ ታሪክ የሚያገኝባቸው ታሪካዊ ኩነቶች አሉት›› ብለዋል ፕሮፌሰሩ፡፡

በእርግጥ የፕሮፌሰሩ ሀሳብ መልካም ነበር፡፡ ብዙ ታሪክ እንዳለሽ ይነገራል፡፡ ነገር ግን ይህንን ታሪክ ለመመርመር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አለ? እውነት አሁን ያለውና ያንቺ ነው የሚባለው ታሪክ ሁሉንም ዜጎችሽን ያካትታል? በቀደሙት ዘመናት የተከወኑ እኩይ ተግባራትስ የታሪክሽ አካል አይደሉም? መልካም መልካሙን እንጂ ሌላውን በተደራጀ መልኩ ማግኘት ይቻላል? የታሪክ ምሁሮች የሆኑ ልጆችሽስ ምን ያህል ለሙያቸውና ላንቺ የታመኑ ናቸው? ታሪክ አዋቂዎችሽም ጥያቄ ውስጥ የሚጥላቸው ነገር ሲከውኑ ይስተዋላል አኮ! ታሪክሽ እኮ እንዲሁ እንዳወዛገበ ዘለቀ፡፡ ለዚሁም ራስሽ ታሪከኛ ሆንሽ ማንን እንመን ታዲያ? አንቺ ስለምታውቂያቸው ንገሪን፡፡

‹ታላቋ›

ሙገሳ ቀለብሽ ነው መቼም፡፡ የበርካታ ልጆችም እናት ነሽ፡፡ የሠሩልሽ ግን እምብዛም ነው፡፡ ‹‹የታላቋ….›› እያሉ ይሸውዱሻል፡፡ ‹ታላቅ›ነትሽን ለማብሰር በአደባባይ ለመመስከር አይቦዝኑም፡፡ ዞር ብለሽ እያቸውማ………… የሉም፡፡ አንድም አውቁሽም……………… አልያም………… አጋጣሚው ስለፈጠረላቸው ብቻ ‹ታላቅ› ምናምን እያሉ ሊሸውዱሽ ይሞክራሉ፡፡
ስለቀደመውም ዘመን ሲነሳ በእርግጥ ሥልጣኔ የሚሉትን ነገር ያነሳሉ፡፡ ነገር ግን በብዙ አጋጣሚ ጦረኛ ልጆችሽ እና የጦር ሠራዊት ብዛታ ከሁሉ ገዝፎ ይታያል፡፡ ሸንቁጥ እራሱ መዛግብቱን ጠቅሶ ስለታላቅነትሽ ሲወሳ ‹‹……… አንድ ሚሊዮን ሠራዊት አዝምታ……›› ‹‹………እስራኤልን መውረሯ………›› አክሎም እስራኤላውያን ይፈሩሽ እንደነበር አውስቷል፡፡ ሲቀጥልም የእስራኤል ነገስታትና የታሪክ ጸሐፊዎች ስላንቺ ሲጽፉ ‹‹ታላቂቷ›› ‹‹ታላቅ›› ይሉሽ እንደነበር ነግሮናል፡፡ እንደውም በአንድ ወቅት የእስራኤልን ንጉስ ለመውጋት ሄደሽ እንደነበር ነግሮናል፡፡ ኧረ እንደውም በአንድ ወቅት የእስራኤልን ንጉስ ለመውጋት ሄደሽ የሠራዊትሽን ብዛት አይቶ የእስራኤሉ ንጉስ ወደእግዜአብሔር መጮሁንም መዛግብት አጣቅሶ ነግሮናል-ሸንቁጥ፡፡
ታዲያ እኒህን አንስቶልሽ ሲያበቃ ነው አንቺ ሆይ ወጣት አይደለሽም ያለሽ፡፡ በመሠረቱ ከእርጅናሽ ያተረፍሽውን እጠይቅሻለሁ እኔ፡፡ ስለምን እንዲህ ሆንሽ? ግድየለሽም ንገሪኝ፡፡

‹ውህድ›

ልጆችሽ ውህድ ናቸው ይልሻል ሸንቁጥ፡፡ እርሱ ራሱ የጠቀሳቸው ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅም ይህንን ሃሳብ እንደሚጋሩ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ነገር ግን የጋራ ነገር አለን ማለት ውህድ መሆን ነው ? እውነቱን ለማወቅ ጠየቅኩሽ፡፡ በተለይ በጽሁፉ ሸንቁጥ ውህደት ከድምር ይበልጣል ብሎሻል የሂሳብ ሊቃውነቱን አባባል ወስዶ፡፡ አንቺ እንዴት ታስቢያለሽ?

እኔ ግን እንደሚመስለኝ በርካታ ልጆች አሉሽ፡፡ የእነዚህ ልጆችሽ ልዩነት አያፈርስሽም፡፡ የተዋሃዱ ልጆች አሉሽ መባሉም አንድ አያደርግሽም፡፡ እንደውም ሲመስለኝ ይህ የመዋሃድ እሳቤ እንደተዳፈነ ፍም ሆኖ ይጎዳሻል፡፡ በአንድ እይታ ብቻ እንድትወሰኚ ያስገድድሻል፡፡ ስለሆነም በዚህ የማይስማሙ ልጆችሽ ደግሞ ወደዚህኛው እንዲመጡ ብርቱ ስራ ይጠብቅሻል፡፡ እንዲያው በደፈና ውህድ ነን ቢባል አንቺስ ደስ ይልሻል?

ባይሆን ያንቺን የጋራ እናትነት መካድ ከባድ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ታዲያ ልጆችሽ ላይ ይለሽ የምልከታ ልክ መታየት ይኖርበታል፡፡ በእርግጥ ቢለያዩም ሁሉንም በተቻለ አቅም ሊያስማማ የሚችል-መቻቻል፤ ሠው የመሆናቸውን ልኬት-እኩልነት ለማምጣት ብትሠሪ ይሻልሻል፡፡ እኔ እንዲህ ይሰማኛል፡፡

ይህንንም ስልሽ ግዛት ለማስፋፋት ሲባል ነገስታቱና መሳፍንቱ በየወቅቱ ያደረጉት ውጊያ እንዳለ ሆኖ የነገስታቱን ፍላጎት ብቻ ባማከለ መልኩ የተካሄደውንና ‹ተሸናፊው› ህዝብ የደረሰበትን የታሪክ፤ የሥነልቦናና የማንነት ‹መነቅነቅ› ግን የሚዘነጋ አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ አንቺም እንደማትዘነጊው አስባለሁ፡፡ በዚህ መካከል ‹ወራሪ› እና ‹ተወራሪ› ብሎ ማሰብ ይኖር ይሆናል፡፡ አሁን ጉዳዩ የመውረርና የመወረር ሳይሆን ከዚያ ባሻገር ነገስታቱ የወሰዱት እርምጃዎች፤ በሚወሩት ህዝብ ታሪክ ላይ ያሳረፉት ነገር ሁሉ በትክክል መነገር፤ መተረክም እንዳለበት አስባለሁ፡፡ ይህ ሲሆን አንቺነትሽ እውነት ላይ የተመሠረተ፤ እውነትሽ ገኖ የወጣ ይሆናል፡፡ ካለሆነ ለወደፊት ለልጆችሽም ፈተና እንዳትሆኚ እሰጋለሁ፡፡

እንዲህ ያለውን ታሪክም ቢሆን በግልጽ ተወያይቶ መግባባት ላይ ቢደረስ የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ ለነገሩ አንቺ ‹‹ስንቱን ሰብስቤ?›› ትይኝ ይሆናል፡፡ ግን ብትሞክሪው መልካም ነው፡፡ እኔ እንደውም ከውህድሽ ይልቅ በልዩነት ውስጥ በሚኖረው የልጆችሽ መስተጋብር ውስጥ መከባበርና መደጋገፍ ያለው ድምቀትሽ ይናፍቀኛል፡፡

ለዛሬ እንዲህ ብልሽ አይከፋሽ ይሆናል፡፡ ሸንቁጥ በማንነት ጉዳይ ላይ ስለተነሳው ሁነት ደግሞ በሌላ ጊዜ ልመለስበት፡፡

መልካም ይሁን፡፡


© አብርሃም ተስፋዬ

http://shenkutayele.wordpress.com/2014/09/24/%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB%E1%8B%8A-%E1%8B%89%E1%88%85%E1%8B%B5-%E1%88%85%E1%8B%9D%E1%89%A5-%E1%88%8A%E1%89%A3%E1%88%8D-%E1%8B%AD%E1%89%BD%E1%88%8B%E1%88%8D-%E1%8B%A8%E1%8C%8B/

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ