እሑድ 13 ኤፕሪል 2014

የደብተራው አምሳሉ ጡዘት!!!

http://www.goolgule.com/my-reply/ ሠዓሊ (ደብተራ) አምሳሉ ገ/ኪዳን ለቀደመው ጽሁፉ አስተያየቶች የሠጠውን ምላሽ በመንተራስ የተጻፈ፡፡

ለምላሽህ ምላሽ ቢሆን

ደብተራው አምሳሉ የቅድመ አያቶቹን ታሪክ ይዞ ፉከራና ቀረርቶውን ያስነካዋል፡፡ ነጻነትህ ጥሩ ሆኖ ሳለ፤ ደብተራነትህ ሳይጎዳህ የቀረ አልመሰለኝም፡፡ ግድ የለህም ጎድቶሃል፡፡ ምላሽ ይሁናችሁ ብለህ የደገምከው የመሰል አያቶችህን ተረት ነው፡፡ የዛን ዘመን ተረት ደግሞ ታሪክ እንዲሆን ትወዳለህ፡፡ በሌላ ወገን ያለውን ለማመን ግን አሻፈረኝ ባይነትህ ገርሞኛል፡፡ በመሠረቱ የወደዱትን ጽፈው ታሪክ አስብለው ያለፉት ያንተው ነገስታት እነሆ ዛሬ ላይ ታሪክ አልባ ሀገር ብትኖረን ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስባለሁ፡፡ የእራሳቸውን ማንነት ለማግዘፍ ሲሉ፤ ቅራቅንቦዋቸውን ሁሉ በመዝገብ ሲያኖሩ ከርመው፤ አንዳች እውነት ፍለጋ ምን ያህል እያደከሙን እንዳሉ ሳስብ አዝናለሁ፡፡ ነገስታቱ በረባ ባልረባው ሁሉ የእነርሱን ጀብድና መልካምነት አስፍረው አልፈዋል፡፡ አንዳንዴም ሳስበው በንግስናቸው ወራት ጦርነት ባልነበረበት ሁሉ ጀብድ ያስመዘገቡ ይመስለኛል፡፡ ገራሚ ናቸው ብቻ፡፡ እነርሱን በመሀከሉም ማንሳቴ ስለማይቀር ወዳንተ ልመለስ፡፡

በ‹‹እነሆ ምላሻችሁ›› ጽሁፍህ ለማንሳት የሞከርካቸው ሀሳቦች በዋናነት ለአንድ ግለሰብ ጽሁፍ ላይ የተንተራሰ ቢሆንም፤ ለሁላችሁም መልስ ይሆናል በማለትህ አንብቤዋለሁ፡፡ ነገር ግን አሁንም ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ሀሳብህ የኦሮሞን ህዝብ ኢትየጵያዊነት ለመጠራጠርህ በድጋሚ ከማረጋገጥ የዘለለ አልሆንልህ ቢለኝ ደጋግሜ አነበብኩት፡፡ ሀሳብህን በእርግጠኝነት ስሜት ስታነሳ ጥንቃቄ የሚጎድልህ መሰለኝ፡፡ አንብበህ ያወቅከውን ነገር ከነማስረጃው ብትናገረው መልካም የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው ካልክም በዛው መልክ ብናውቀው ጥሩ ነበር፡፡ አንተ ግን ከወቅቱ ‹‹ታሪክ›› ጸሐፍት አንዱን ወክለህ አልያም ሆነህ የምትጽፍ ይመስላልና ምናልባት ደግመህ ብታየው፡፡ ሆኖም ታዲያ የቃላት ድርድር በዛበትና አሰለቸ፡፡ አንዱን ሳትጨርስ ወደአንዱ ትዘላለህ፡፡ መልክ አሳጣኸውና ግራ ለማጋባት ያደረግከውም መሰለኝ፡፡ ስለምን አንተ ያልከው ሁሉ ተቀባይነት እንዳለው እንዳሰብክም አላውቅም፡፡ እራስህን ግን ምን ይህል እንደምትወድ አስታውቆብሃል፡፡

ለዘመናት ከኦሮሞነት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ማናቸውም የታሪክ ክርክሮች ማሳያ ተደርገው የሚነሱትን ‹‹አለቃ›› የሚል ቅጥያ የተሰጣቸው አድርባዮች የጻፉትን ይዘን እስከመቼ እንደምንዘልቅ አላውቅም፡፡ እነርሱ ላንተና ለመሰሎችህ እንዲመች አድርገው ባሰናዱት አይነት ሳይሆን፤ ሌሎች ምሁራን ደግሞ ጉዳዩን መርምረው ያሰፈሩትንም ማጣቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

በመሰረቱ፤ ዋናው አጀንዳ የነበረው የአኖሌ የመታሰቢያ ሐውልት ይመስለኛል፡፡ ይህ ደግሞ በእርግጥም ሰማዕታትን ለማሰብ የሆነ ስለሆነ መልካም ነው ብሎ ማለፍ ክፉ አያስብልም፡፡ ያንን ዕልቂት በቅጡ የሚያስታውሱት፤ ህመሙ የሚሰማቸው፤ ቁስሉ እስካሁን የሚኮሰኩሳቸው እኒያ የዛው አካባቢ ተወላጆችና፤ በዚሁ ዳፋ እልቂት ያስተናገዱት የአርሲ ልጆች፣ እናቶች፣ አዛውንቶችና መላው ማህበረሰቡ ነው፡፡ ስለሆነም ይሁነኝ ልጆቼን፣ ወንድሞቼን፣ እናቶቼን፣ አባቶችን፣ በአጠቃላይም ወገኖቼን ላስብ ያለው የአርሲ ብሎም የኦሮሞ ህዝብ ወገኖቹን ለማሰብ ለምን ይከለከላል? በመሠረቱስ አፍን ሞልቶ ተረት ነው ለማለት መድፈር ህዝብን ‹‹ታሪክህን አታውቅም›› ከማለት በምን ያለይ ይሆን?

የኦሮሞ ጥናት ማህበር እ.ኤ.አ. በ1995 ባሳተመው የጥናት መድብል ሁለተኛው ቅጽ ላይ አባስ ሀጂ (ዶ/ር) የአርሲ ኦሮሞ ህዝብ አጼ ምኒልክ ላይ ያሳየውን ፖለቲካዊና ወታደራዊ ጥንካሬ አስመልከቶ ባሰፈረው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ‹‹የአርሲ ህዝብ ለምን እና እንዴት ያን ያህል ብዛት ያለው ተዋጊ ኃይል ለረዥም አመታት በማንቀሳቀስ፤ ኢጣልያን በወቅቱ በአንድ ጦርነት ለመርታት የቻለውን ምኒልክን ለመuuም ተቻለው?›› የሚለው ጥያቄ ማንም ሊጠይቀው የሚችለው እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡
በወቅቱም የአርሲ ኦሮሞ እራሱን ለመከላከል የወሰዳቸውን እርምጃዎች ያትታል፡፡ የምኒልክን አቅም በቅጡ የተፈተነበትም እንደነበር ያሳያል ይኸው ከላይ የተነሳው ጥያቄ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ታዲያ አርሲዎችን ጠቅሞዋቸው ነበር ያላቸውን ምክንያቶች ዘርዝሮዋል፤ ከእነርሱ ውስጥም የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

የቦታውን አቀማመጥና አርሲዎች በዚህ ያገኙትን ጠቀሜታ በአንደኝነት እንደምክንያት ያነሳዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተፈጥሮም ታዳላለች የሚባለው አይነት ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ታዲያ ምንም እን£ በርካቶች የአርሲ ህዝብ በወቅቱ በአዋሽና ሸበሌ ወንዞች መሐል ብቻ የሚኖር አድርገው ቢገምቱም፤ ከዛም ባሻገር አርሲ ከኦሮሞ ብሔር ውስጥ አንዱና ትልቁ ‹‹ቅርንጫፍ›› መሆኑን የዘነጉት ይመስላል፡፡ በዚህም መነሻነት የህዝቡ ቁጥር ከፍተኛ የነበረ መሆኑም አግዞታል ማለት ነው ይለናል ዶ/ር አባስ፡፡

የውስጥ ሰላምና አንድነቱ ለአርሲ ሌላኛው ጥንካሬው ነበር፡፡ ወራሪውንም በብርቱ የሞገተው ለዛም ነው፡፡ እንደጎረቤቱ ቦረና የውስጥ ሽኩቻ አልነበረበትም፡፡ በአንድ ወቅት እንደውም በተለይም ከቀደምቶቹ መካከል የሆኑት ቃቃ ኦሮሞ በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት ኦሮሞ ኦሮሞን እንደማይገድልና አርሲም ለዚሁ ትዕዛዝ ተገዢ እንደነበር ያነሳል ዶ/ሩ፡፡ ሆኖም፤ እንደሌሎቹ የኦሮሞ ታሪኮች ሁሉ ይህም ታሪክ በጊዜ ሂደት እንዲጠፋ ሆነ፡፡

ተያይዞም፤ አርሲ ምንም እን£ በጎሳ የተለያየ ቢሆንም ለወራሪና ሌላ ባዕድ ሊነካው ሲሞክር በአንድነት ሆኖ ይመክት እንደነበርና ለዚሂም ያሳይ የነበረውን መነሳሳት ነው ጥናቱ የሚያወሳው፡፡
በአርሲ ወገን ሆነው ህዝቡን ሲያስተባብሩና አመራር ሲሰጡ ከነበሩት መካከል በጥናቱ ሶስቱ ተጠቅሰዋል፡፡ እነርሱም፤ ሱፋ ቁሶ፣ ሌንጂሶ ዲጋ እና ሮባ ቡታ ናቸው፡፡ እኒህ ጀግኖች ታዲያ በአልደፈርም ባይነት ለህዝብ ጥቅም የተዋደቁ ናቸው፡፡ በእነርሱ መሪነት በሺዎች የሚቆጠር የአርሲ ኦሮሞ ላለመወረር ሲል ህይወቱን ሰጠ፡፡ እኒህ ግለሰቦች ጥሩ የጦር መሪዎች፤ ፖለቲከኞችና ህዝብን መምራት የሚችሉና የቻሉ ነበሩ በወቅቱ፡፡ የአርሲን ብርታት ያየው ምኒልክ ታዲያ ያለርህራሄ ሁሉንም ባሻውና ይጠቅመኛል ባለው መልክ አደረገ፡፡ ጭፍጨፋው ዘግናኝ እንደነበር መዛግብት ያወሳሉ፡፡ አንተ እንደምትለው አይደለም፤  ደብተራ አምሳሉ፡፡ ነገሩ ብርቱ ነው፡፡
በአንድ አጋጣሚም ስለመገንጠል አንስትሃል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ትግልና ጥያቄ ሲነሳ ለምን ከመገንጠል ጋር ብቻ ተያይዞ እንደሚነሳ አላውቅም፡፡ ይህም ስህተት ነው፡፡ ለአሁን እንተወውና በሌላ ጊዜ ካልሆነ እመለስበታለሁ፡፡

ለማንኛውም፤ጸሐፍት ተብለው የሚነሱትን ሰዎች አስመልክቶ ነጋድራስ ገ/ህይወት ባይከዳኝ፤ ከዚህ በፊት በሌሎች ጽሁፎቼም እንዳነሳሁት በወቅቱ (ያን ጊዜ ማለት ነው) የነበሩትን ጸሐፍት ለሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚገባ በአንድ መጽሐፋቸው ላይ ጥሩ አድርገው ገልጸውታል፡፡ ሲያብራሩም የመጀመሪያዎቹን ሊቃውንት ቤተመንግስት ሲላ;ቸው፤ እንጀራን ሲፈልጉ ከቤተመንግስት ተጠግተው በንጉሱ የታዘዙትንና ንጉሱን የሚያወድሱ ነገሮችን ታሪክ ብለው በመጻፍ ለላው ትውልድ የሚያስቆዩ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ መነኮሳት መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ መነኮሳቱ የሚጽó<ቸው ታሪኮች አድልዎ ይበዛበታል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ እራሳቸውን ለማዋደድ ሲሉ የወቅቱ ‹‹ተዓማኒነታቸውን›› ተጠቅመው ታሪክ ብለው የእራሳቸውን የውስጥ ጥላሸት ታሪክ ብለው አስፍረውታል፡፡ የራሳቸውን እንጂ የህዝቡን ጥቅምና ጉዳት ከቶ አይቆጥሩምና፡፡ ስለዚህ የልባቸውን የሚፈጽምላቸው ንጉስ ቅዱስ ይሉታል፡፡ ከድንቁርናቸው ወጥቶ ከፍ ባለ ህሊና ተመርቶ ስለዜጎቹ ልማት የሚጥር ግር እርኩስ፡፡ አንተስ ደብተራ አምሳሉ እንዴት ትላቸው ይሆን?

ሌላውና በጣም ገራሚው ነገር ደግሞ የሐይማኖት መዛግብቱም ውስጥ ጉዳዩ እንዲካተት መሆኑ ነው፡፡ ይህንን በማድረግ ሀይማኖቱንም ሌላ መልክ ለማስያዝ ይጥራሉ፡፡ በጣም የሚገርመው ታዲያ ስለጉዳዩ አቶ አጽመ ጊዮርጊስ የተባሉት ግለሰብ በአንድ ወቅት ያሰፈሩት ከዚህ እንደሚከተለው ነው፡፡ ‹‹በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ጋላ ሁሉ ተገዛ፤ ባማራ ሕግና ሥርዓት ሄደ፤ ካህናቱ ግን አንድ ጋላ አስተምረው አላጠመቁም፡፡ ይልቅስ ተፊተኛው ቂም የበለጠ ቂም በልቡ አኑረውበት መሬቱን በቀላድ ወሰዱበት፡፡ አንድ ቀላድ የቅስና አንድ ቀላድ የአወዳሽ እያሉ በዚሁ ስብከት ንጉሱን አሳመኑ፡፡ ስለመንግስት ያሰቡ መስለው ለንጉሱም አንድ ቀላድ፣ ለገባር አንድ ቀላድ፣ ለወታደር አንድ ቀላድ....መሬቱን ተካፍለው ጋላን አንደባርያ አድርገው ይገዙታል እንጂ የክርስቶስን መንገድ አላሳዩትም፡፡ እነሱም አልተማሩም፡፡ አስተማሪው ቢመጣ ይከለክላሉ፡፡ ከትልቁ ሁሉ ከንቱ ብላሽ የሚያደርገው በቁጥርም እርሱም እግዚአብሔርን አለማወቃቸው ነው፡፡ ማለት ሕጉንና ትእዛዙን በሁሉም ስፍራ መኖሩን አያውቁም፡፡››

አየህ አይደል ደብተራ አምሳሉ? ይህም የአንተና የእኔ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው ተብሎ ይጻፋል፡፡ እነዚህንም እናነባለን፡፡ አንተ ላንተ የሚመች የመሰለህን መሰል ነገር ታሪክ ነው ብለህ ልትሞግተኝ ትሞክራለህ፤ ብለህ ደግሞ ታሪክ ከእኔ ወዲያ ለማለትም ትዳዳለህ፤ እኔ ግን ልልህ ወድጃለሁ፤ በመሀከል ያለችው ግን ኢትዮጵያ ናት፡፡ ይህች ኢትዮጵያ ደግሞ እውነቱን አፍረጥርጠን ለጠፋውም ለለማውም የሆነውን ሁሉ ተነጋግረን አውቀን፤ እውነተኛውን ነገር እስካልያዝን ድረስ ዝም ብለን ተነስተን፤ የምንደነፋባት መሆን የለባትም፡፡

የተመቸንን በሰማን ቁጥር ‹‹እውነቱ ይሄ ነው›› ብለን በምንለው ልክ፤ እውነቱን ስንሰማ ታወቀብኝ በሚል ስሜት ከምንንደረደር፤ ሀገራዊውን የቆሸሸ ታሪክ አምኖ ተቀብሎ ወደፊት ስለማይኖረን ወይም እንዳይኖረን ከምንመርጠው መጥፎ ታሪክ ላይ ብንሰራ መልካም ነው፡፡ ‹‹ከእዛ ዘመን ደብተራ የዚህ ዘመን ደብተራ›› ብለን እንድንናገር አድረገን፡፡



አብርሃም ተስፋዬ

ዓርብ 28 ማርች 2014

ዝምታሽ አልበዛም ኢትዮጵያዬ?


‹‹ሀገርን ፍለጋ››


<<የተገነቡትና በመገንባት ላይ ያሉት የመታሰቢያ ሐውልቶች የሠማዕታት ወይስ የቅሱፋን?>> በሚል በሠዓሊ አምሳሉ /ኪዳን አርጋው የተጻፈ የተባለውንና ዕንቁ መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር113 መጋቢት 2006 ..ን ዋቢ ያደረገውን የhttp://www.goolgule.com/monuments-for-martyrs-or-victims/ ጽሑፍ አነበብኩና ዝምታን ለመምረጥ አልወደድኩም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዬ እራስሽን ልጠይቅሽ ባክሽ?
መቼም ታሪክሽ መያዣ መጨበጫ ያጣ ይመስላል፡፡ ሁሉም ተነስቶ የሚጽፈው አይነት ሆኖልሻል፡፡ አንዳች እውነት ውስጡ ለማግኘት በደንብ መበርበር የሚፈልግ፤ አንደኛው የሚጽፈውን ሌላኛው በእርግጥም ድብን አድርጎ አሳማኝ በሆነ ሁኔታ የሚሽርበት አይነት ነው፡፡ ሀገሬ ግን በመሀከል ቤት ቁጭ ብለሽ ታሪክ አልባ እየሆንሽ ያለሽ መሰለኝ፡፡ በ‹‹አዋቂነት እርሾ›› ሰበብ ሁሉም እየተነሳ የሚጽፍብሽ አይነት ሆነሽ፤ ቀራጺውም፤ ሰዓሊውም፤ የታሪክ ምሩቁም፤ ፖለቲከኛውም፤ ለቀስተኛውም፤ አላቃሹም፤ ታሪክ ጸሐፊ ሆኖብሽ የተቸገርሽ መሰለኝ ሀገሬ፡፡ ሀገሬ ምናባቴ ላርግሽ? ምን ይሻልሽ ይሆን? እኔም ታዲያ ልጠይቅሻ፡፡ እንደእናት አንድ በይኝ፡፡ መልስ ስጪኝ እናት አለም፡፡

አንድነትን ሰበብ አድርገው ማንነትን የሚሞግቱ ‹‹አዋቂዎችሽ›› ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡ አሁንም የሚሉት ያላቸው መሰለኝ፡፡ እያሉም ነው፡፡ በመከባበርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ አንድነትሽን የሚናፍቁና ቢሆን የሚወዱ እንዳሉ የተረዱት ‹‹አዋቂዎችሽ›› እናትነትሽ ለእነርሱ እንጂ ለሌላው እንዳልሆነ እየመሰከሩልሽ ነው፡፡ ሌሎችስ ማን አላቸው ያላንቺ? ሀገሬ ይገርምሻል አዋቂ የሚባሉት ሰዎችሽ ለሽምግልናና ለማሳያ የምንጠቀምባቸው የነበሩ ግለሰቦች ነበሩ፡፡ ዘቀጡ፡፡ ለልጆችሽ እልህ እንጂ ታሪክና መሰንበቻውን የሚያቆይሽ ነገር አላስቀምጥልሽ ብለው ይኸው አሰቃዩን፡፡ ‹‹አዋቂዎችሽ›› ግን ምን ነካቸው?

ሀገሬ ግን እውነት ታውቂናለሽ? እኛ በእርግጥም በውስጥሽ አለን? ነው ወይስ ተሳስተሸ ይሆን ያኖርሽን? አሁን መቼም አንቺ ስለሆንሽ እንጂ ሌላ ሀገር ቢሆን እንዲህ ይዘቀጣል? ይግረምሽ ብሎ አንደኛው ሠዓሊሽ ‹‹የታሪክ ምሁር›› ነኝ ብሎ ነው መሰለኝ ለህትመት ያበቃውን አየሁልሽና ከፋኝ፡፡ ስለዚህም እነግርሻለሁ፡፡ ቢያቅርሽም ቅሉ ስሚኝ፡፡ ወደድሽም ጠላሽም ጊዜ ስጪኝ ሀገሬ፡፡
ሠዓሊው ሰውዬሽ የመታሰቢያ ሐውልቶችሽ ለማን እና ለምን እንደሚሰሩ (ጠበቅ ተደርጎ ይነበብ) በሚሞግትበት (ምናልባት በተለይ ለኦሮሞ ህዝብ ያለውን የወረደ የክብር ልክና ስሜት ያሳየበት ይመስላል) ጽሁፉ ሕወሓት/ኢህአዴግን ሀገር አጥፊ ነው እያለ፤ በትጥቅ ትግሉም ግዜ ያለፉትን ታጋዮች በህይወት ካሉት እንደማይለዩ፤ ኢህአዴግ ለወደፊቱም እያኖረ ያለው ነገር መልካም አይደለም ሲል ያክላል፡፡ በዚህ ጽሑፉ ግን የአንቺ አንድነት ያሳሰበው መስሎ ልጆችሽን (በተለይ የኦሮሞ ተወላጆችና ብሔሩን በአጠቃላይ) ሙልጭ አድርጎ ያንቺ እንዳልሆኑ አስረድቶልሻል፡፡ ልጅሽ ከሆነ ገስጪው ሀገሬ፡፡

ሰዓሊው ‹‹ታሪከኛ›› ልጅሽ መሳይ ገንጣይሽ ትምክህቱን አራግፎታል አልኩሽ፡፡ መቼም አይተሽዋል፡፡ ሰምተሽውማል ብዬ አስባለሁ፡፡ እውነቴን ነው ዝም አትበይው፡፡ ጥሩ ልጅሽ አልመሰለኝም፡፡ እውነት ሀገሬ፤ ይህ ነገር ጥሩ አይደለም፡፡ ምን እንዳለ ታውቂያለሽ ኢትዮጵያዬ? አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ በሚል ለጨፈጨፉት ዜጎችሽ መታሰቢያነት የሚቆም ሀውልት ተገቢነቱን ሞገተ፡፡ በተለይ በአርሲ ለተከወነው የቆመውን የአኖሌን ሀውልት ጉዳይ ሲያነሳ፤ ኦሮሞዎችን በጅምላ ታሪካቸውን የማያውቁ ብሎ ተሳለቀባቸው፡፡ ምን ያለው ነው ታዲያ ይሄ ሀገሬ? ንገሪኝ ግድ የለሽም፡፡ እኔ እንደሁ ልጅሽ ነኝ፡፡ ግዴለም ንገሪኝ፡፡ ስለአንቺ አንድነት የሚዘምሩ መስለው መርዛቸውን የሚረጩብሽ በዙ እኮ፡፡ ሀገሬ ዝም አትበይ እንጂ፡፡ ምን ነክቶሻል፡፡ ግዴለም ያልለመደብሽን ዝምታ ከየት አመጣሽው? ቁጣሽ የት ሄደ እናትአለም? ሀገሬ ግድ የለሽም በርትተሽ ተቆጪ፡፡ ወኔሽን ሰለቡት እንዴ? አለን ብለው፤ መስለው አስኮረፉሽ እንዴ?

ሠዐሊው ልጅሽ ነኝ ባይ ‹‹ይታያችሁ ኢትዮጵያ አንድ እንዳትሆን ሲታገሉ ተገቢ እርምጃ የተወሰደባቸው የሀገር ጠላቶች፤ የአንድነት እንቅፋቶች ሆነው እያለ መስዋዕትንት የከፈሉ ይሉዋቸዋል›› ብሎ በግፍ የተጨፈጨፉ ዜጎችሽ ላይ ተሳለቀ፡፡ አንድነትሽ ሲናድ በወቅቱ ለመመለስ የተደረገ ነው ብሎ የሚያምነውን ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ተገቢ ነው ይልሻል፡፡ ቤታችን፣ መኩሪያችን ብለው በእናት መስለው የሚኖሩትን ብሔር ብሔረሰቦችሽን ‹‹ጎጦች›› አላቸው፡፡ ዜጎች ዛሬ ላይ ላሉበት ነገር ዋጋ የከፈሉላቸውን ወንድም እህቶቻቸውን ለማሰብ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ፤ ብሎም የመታሰቢያ ሐውልቶችን መስራታቸውን ሁሉ ‹‹አጥፊ›› ነው ብሎ ፈረጀልሽ፡፡ የእርሱን ስድብና ፉከራ ግን ‹‹ምርቃት›› ነው ሊልሽ ይሆን? እንደሁ ጠይቂልኝ፡፡ እባክሽ ሀገሬ ግድ የለሽም ጠይቂው፡፡

ሀገሬ መቼም አንቺ እንደ ልጅሽ ነይ ባዩ ሠዐሊ ልጆችሽ ታሪካቸውን የሚስቱ/የማያውቁ አይመስልሽም አይደል? እርሱን እርግጠኛ ነኝ፡፡ እንደው ይህ ሠዐሊ ሲስልሽ ባየሁት፡፡ እውነት ግን ሠዐሊ ነው ኢትዮጵያዬ? ግዴለሽም በደንብ አጣሪ፡፡ በአንቺ የዋህነት አይሆንም፡፡ ሠውየው ሌላ አጀንዳ ያለው ይመስላል፡፡ ታሪክን የ‹‹ፈጠራ ወሬ›› ነው ብሎ ይሞግታል፡፡ ፈጠራ ማለት ምንድነው እናት አለም? ሥዕል ሊፈጠር ይችላል፡፡ ታሪክ ግን እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል? ሰውየውን አስረጂልኝማ፡፡ ግዴለም ሠውየው አንዳች ነገር ሆኖ ይሆናል፡፡

ጭራሽ ብሎ ብሎ ኢትዮጵያዬ፤ ኦሮሞ ልጆችሽን ኢትዮጵያዊያን አይደላችሁ ብሎዋቸው አረፈ፡፡ እንግድነታቸውን ነገራቸው፡፡ አይገርምሽም ስላንቺ አንድነት የሚያስብ የሚመስለው ሠዐሊ አንቺን አንድ እንደሆንሽ ሲደሰኩር አርፍዶ ልጆችሽን ግን ያንቺ እንዳልሆኑ ነገራቸው፡፡ ‹‹ታዲያ ሀገራቸው የት ነው?›› ብለሽ ጠይቂው በሞቴ፡፡ እናት አለም እባክሽ ጠይቂው፡፡ በእኔ ሞት ይሁንብሽ ጠይቂው፡፡ ምን እንዳለ ልንገርሽማ ‹‹የኦሮሞ ህዝብ እነዚህን የልብ ወለድ ገጸባህሪያትንና ዓላማቸውን ምሳሌ አርአያ አንዲያደርጉ የሚወተውቱ የኦሮሞን ህዝብ ሊያሳስቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለውን አንድነትና ዝምድና ሊያራርቁ ሊሸረሽሩ፣ ሊያሻክሩ የሚችሉ መርዘኛ የፈጠራ ወሬዎች የሚሰበክበት የጥፋት ማዕከል እንደሚያደርገው በቀላሉ መገመት ይቻላል›› ይላል ስለ አኖሌ ሀውልትና ሙዚየሙ ሲያወሳ፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ያለው አንድነት ነው ልዩነት? ሀገሬ ግዴለም ጠይቂው፡፡ አትፍሪ እናት አለም ብቻ ጠይቀሽው ይውጣልሽ፡፡ ምን ይልሽ ይሆን እንስማው፡፡ ቀጠለና ምን ደግሞ አለ አትይኝም? እርሱ መች ትቶት ኢትዮጵያዬ ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ብዙ ባለአእምሮ ዜጎች ያሉት አስተዋይ የሕዝባችን አካል ነው›› አይል መሰለሽ? ገራሚ ነው፡፡
የኦሮሞን ህዝብ እንግድነት በግልጽ አስፍሮልሻል፡፡ ኢትዮጵያዬ መቼም እንዲህ ታሪክ አልባ የሚያረጉሽን ሠዐሊውንና መሰሎቻቸውን ምን ትያቸው ይሆን? ‹‹ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ባለው የሀገራችን ታሪክ ግን የሌሎቹ ብሔረሰቦች በሀገሪቱ መኖር በአንድም በሌላም አጋጣሚዎች ተጠቅሶ ሲገኝ የኦሮሞዎቹ ግን ጨርሶ የለም›› ይልሻል፡፡ እውነት እነርሱ ብቻ ነበር ያልነበሩት? ጨርሶ ደግሞ ሲያስረግጥልሽ ምን ቢልሽ ጥሩ ነው? ‹‹ይህም የሆነበት ምክንያት በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው በሀገሪቱ ስላልነበሩ ነው፡፡ የግራኝ ወረራ በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ከገቡ በላ ግን በሀገሪቱ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ ሚና ለመጫወት ሲበቁ እንደእንግድነታቸው አልነበረም›› ብሎሽ እርፍ፡፡ አክሎም ተሳትፎ ለማድረግ ፈጣን እንደነበሩ አትቶልሻል፡፡

ተመልሶ ደግሞ አንዳንዶች (በእርሱ አገላለጽ የጥፋት ኃይሎች) ኦሮሚያን እንገነጥላለን፤ ነጻ መንግስት እንመሰርታለን ገለመሌ ሲሉ የቅርብ ግዜ እንግዶች እንደሆኑ ማስታወስ ይኖርበት እንደሁ ይጠይቅማል፡፡ የማንን ሀገር እንደሚገነጥሉም ግራ የገባው መስሎ ይጠይቃል፡፡ ሀገር አልባ ናቸው እንዴ ልጆችሽ? እሰኪ ንገሪያቸው ባክሽ፡፡ ሀገራችሁ አይለሁም ካልሽም፤ የት እንደሁ መሆን የሚገባቸው አሳይያቸው ባክሽ፡፡ ምክንያቱም ልጅሽ ነኝ ባዩ ሠዐሊ ‹‹ኢትዮጵያዊ አይደለንም ካሉ ሀገሪቱን ለቀው ወደመጡበት የመመለስ መብታቸው የተጠበቀ ነው›› ብሎ አዋጅ ነግሮልሻል፡፡ በነገርሽ ላይ ኢትዮጵያዬ እርሱ ግን አዋጅ ነጋሪና ነጋሪት ጎሳሚ ያደረገው ማነው? ሹመት ሰጥተሽው ነው ወይስ? ግዴለም ግን ልጆችሽ ይከፉብሻል፡፡ መከፋታቸው ደግሞ ጥልቅ ይሆን ይመስለኛል፡፡ ይህንን ብሎ ያበቃ መሰለሽ? ‹‹አጼ ምኒልክ አደረጉ የተባለውን ሁሉ እውነት አድርገውት ቢሆን እን£ ልክ ነበሩ›› ብሎ እርፍ፡፡ ሀገሬ የልጆችሽ ጡት ሲቆረጥ አያምሽም እንዴ? እናት አለም ለምን ዝም ትያለሽ? ተናገሪ እንጂ እንዴት በልጆችሽ ቁስል ሲቀለድ ዝም ትያለሽ?

ሰውየው ሀሳቡ ምን እንደሁ እንጃ፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር ልጠቁምሽ እወዳለሁ፡፡ ካንቺ ባላቅ ሀገሬ፤ አንድነትሽን እየሰበኩ ልዩነትሽን የሚያሰፉ ልጆች ነን ባዮች እየበዙልሽም እየበዙብሽም ነው፡፡ አንድ ብትያቸው መልካም ይመስለኛል፡፡ ኦሮሞ ልጆችሽ ‹‹በሌለና ባልነበረ ቅዠትና የተረት ተረት ታሪክ እየፈጠሩ›› እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ግድየለም ሀገሬ ዝምታሽ እውነት ለመናገር ደስ አላለኝም፡፡
ታዲያ ሠዐሊው ሰውዬ ‹‹ከዘመን በፊት ኢትዮጵያዊ ያላቸው ሆኖ ለመገኘት ያላቸውን ቅን ፍላጎት ብናደንቅም ማንነት ባልነበረና በሌለ ታሪክ ላይ አይመሰረትምና እናዝናለን›› ብሎ አረፈው፡፡ አሁን አማረ አለ የሀገሬ ሰው፡፡ ምን ማለት ነው ታዲያ ኢትዮጵያዬ? ግዴለሽም ሠውየው ሌሎችን ይላል እንጂ እርሱ እራሱ ከእውቅ የሥነ-ልቦና ሐኪሞችሽ በአንዱ መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ እኔ አልድገመው እንጂ ሰውየው ብዙ ስድብም ተሳድቦ ነበር፡፡ ለነገሩ እዛው ታይዋለሽ፡፡ ‹‹የጨለማ እድሜ ጸሐይ እስክትወጣ ድረስ ነው›› ብሎ ዛቻ ቢጤም አስፍሮዋል፡፡ ማን እንደሁ እንጃ፡፡ እንደፍቅር ሠባኪም ያደርገዋል፡፡ እንዴት ነው ግን እናት አለም በስምሽ የሚነገደው? አስበሽዋል አንድነትሽን በማሳበብ እንዴት እንደሚዘባበቱብሽ? አይተሽ ዝም አትበያቸው ባክሽ፡፡ የደም እንባ የሚያነቡ መኖራቸውንም ተናግሮዋል፡፡ ነገ የእርሱና የመሰለቹ መሆኑን ይናገራል፡፡

ሲደመድም ደግሞ መድኃኔአለም ልቡና ይስጣችሁ ብሎ ነበር፡፡ ልቡና ተሰጥቶት የጻፈ ነው የሚመስለው፡፡ ግን ይመስልሻል ሀገሬ? እውነት ልቡና ያለው ሠው እንዲህ ይጽፋል? ዘላለማዊ ክብር እንደሻማ ቀልጠው ይህቺን ሀገር (አንቺን ማለቱ እኮ ነው፡፡ ድንቄም) ከነጻነትሽ ጋር ላቆዩ ለአርበኞቹ እናት አባቶቻችን ይሁን ይላል፡፡ ይህኛው አገላለጽ ከልብ ቢሆን ደግ ሀሳብ ነበር፡፡ ነገር ግን አይመስልም፡፡ ሰውየው ምን እንደነካው እንጃ፤ ብዙ ዘላበደ፡፡
ሀገሬ ልጅሽ መሆኑን፤ ካንቺ አብራክ መውጣቱን ተጠራጠርኩ፡፡ አንድነትሽን የሚፈትነው እራሱ እያለ፤ ሌሎችን አስታኮ የልቡን ነገረሽ እኮ፡፡ እርሱ እንደሻማ ቀለጡ የሚላቸው እነማንን እንደሆነ አልነገረንም፡፡ እውነት እውነት ግን ሀገሬ፤ እኔ ደስ አላለኝም፡፡ ለምን እንደሆነ መቼም ይገባሻል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይህንን በማለቱ አልተደሰትሽም፡፡

እኔ የሚገርመኝ ባንቺ አንድነት ላይ የሚከራከሩት ሰዎች ሌሎችን ማሰብ አይፈልጉም፡፡ አንድነትሽን የሚመኙና የሚያስቡት እነርሱ ብቻ እንደሆኑ ያስቡና ሌላውን ከጨዋታው ውጪ ያደርጉታል፡፡ ፓርቲዎችሽም ቢሆኑ እንዲሁ ይመስሉኛል፡፡ በስመ ተቃዋሚ ከያሉበት ይጠራሩና ስለአንድነትሽ የሚዘምሩ መስለው ልዩነትሽን የሚያፈካ መነጽር ያጠልቁልናል፡፡ ለምን እንዲህ እንድናስብ እንደሚወዱ አላውቅም፡፡ ግን በቃ እንዲህ ናቸው፡፡

አሁን አሁን ደግሞ አዋቂ ነን ባዮችሽ፤ ህዝብሽን የሚከፍል፤ የሚሰነጥቅና የጎሪጥ የሚያተያይ ሀሳብ ያራምዱ ይዘዋል፡፡ እኔ ግን ዝምታሽን እሞግታለሁ፡፡ ለምን ዝም ትያቸዋለሽ? ግድየለም ንገሪያቸው ስለልጆችሽ፡፡ እንግድነት የመጣህ ነህ፤ ቤተኛው እኔ ነኝ እየተባባሉ የሚዛለቁ ይመስልሻል? ግዴለም ሀገሬ አንድ ነገር አድርጊ እንጂ? ዝምታሽን ልሞግተው እማ፡፡

ክፉሽ መቼም ቢሆን አይመረጥም፡፡ ልጆችሽም መልካም ቢሆኑልሽ እመርጣለሁ፡፡ አሁን ግን መከፋቴ ባሰ መሰለኝ፡፡ ስላንቺ ያወሩ የመሰሉኝ ሰዎች ሁሉ ያሳምሙኛል፡፡ ከ80 በላይ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንዳሉ ንገሪያቸውማ፡፡ እኒህ ህዝቦች ተዋልደው እየኖሩ እንደሆነ ንገሪልኝማ፡፡ አይሆንም ካሉሽ ግን ሌላ ነገር እንዳይሆንብሽ እሰጋለሁ፡፡ መከፋትሽን እገምታለሁ፡፡ ለመኖር ግን እራስን መፈለግ ግድ የሚልበት ሁኔታ እንዳለ አለማውቅ፤ ልጆችሽ በእርሱ ተጠምደው እራሳቸውን ሲፈልጉ፤ አንድነትሽን የሰበኩ እየመሰላቸው ልጆቼ ብለሽ የምትናገሪላቸውን የሚያስቀይሙብሽን አንድ ካላልሽ ራስን በመፈለግ ውስጥ አንቺን እንዳያጡሽ እፈራለሁ፡፡ ታሪክ አዋቂ ነን ተብሎ የሚደሰኮረው፤ እሳት ሆኖ እንዳይበላሽ እፈራለሁ፡፡ ግን እኔ እልሻለሁ፤ ፖለቲካዊ ምልከታው የቱንም ያህል ይሁን ስፋቱ፤ አንቺነትሽን ለጥርጥር የሚዳርጉ የበረከቱ አዋቂዎችሽ ግን ብቅ ብለዋል፡፡ ትልልቅ ተብዬዎቹም ሆኑ ትንንሾቹ አዋቂዎችሽ ልብ ያሉት ያልመሰለኝ ነገር አለ፡፡ ሀገሬ በይ እንግዲህ ዝም አትበይ....ግድ የለም ዝም አትበይ.....እንደውም በዚህ ሙቀት ውስጥ ሀገርን ፍለጋ መሄድ ምኑ ላይ ይሆን ክፋቱ? ምክንያቱም ኢትዮጵያዬ አንደኛው ገጣሚ ልጅሽ እንዳለው፤
‹‹ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ
ሀገር ውስብስብ ነው ውሉ››
እኔ ግን እልሻለሁ ዝምታሽ የበዛ መሠለኝ፡፡ ቸር ያቆይሽ፡፡ እኔም ቸር መሆን ምኞቴ ነው፡፡ ስለሆነም ደህና ይግጠምሽ፡፡



አብርሃም ተስፋዬ

ሰኞ 17 ማርች 2014

ጉዞ ጎንደር (የተማሪነት) አጭር ማስታወሻ (ክፍል አንድ)

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ አመቱን ሊያከብር ነው፡፡ ልዩ ነው አቦ፡፡ እን£ን አደረሰን፡፡ ምናልባት ከቻልኩ እገኛለሁ፡፡ እርግጠኛ ነኝ በርካቶቻችን በዚህ ጊዝ እንደምንገናኝ አስባለሁ፡፡ የቀድሞ ተማሪዎች በዚህ ፕሮግራም ላይ ብትገኙ ደስ ይለኛል፡፡ እኔ በእርግጥም ከልቤ እሞክራለሁ፡፡ ስለሆነም ተውስ አለኝና ለምን ይህችን አልልም ብዬ ተነሳሁ፡፡ ከጉዞዬ ልጀምርና ስለጎንደር ከዚህ ጀምሮ በቻልኩትና ባስታወስኩት ብሎም በማስታወሻዬ ባገኘሁት ልክ እላለሁ፡፡ እነሆ የጎንደር ማስታወሻዬ አንድ ብሎ ቢጀምርስ፡፡

የዛሬ በርካታ ዓመት ወደ|ላ ብዬ የምናገረው ታሪክ ስለኖረኝ ደስ ብሎኛል፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ ከተወለድኩባት አዲስ አበባ 734 ኪሎ ሜትር ልንቀሳቀስ ነው፡፡ ጎዞ ጎንደር እነሆ ሊጀመር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የትምህርት ዕድል ነው፡፡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስጄ እድል እጣዬ ከጎንደር አድርሶኛል፡፡ በርካቶች በወቅቱ የት እንደሚደርሰን እንመርጥ በነበረበት በእዛ ሰዓት እኔ በእርግጥም ጎንደር የሚል ነገር አለመምረጤን አስታውሳለሁ፡፡ ከአዲስ አበባ ወጥቼ ስለማላውቅ አዲስ አበባ እንዲደርሰኝ በመመኘት፡፡

ነገር ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነ፡፡ በወቅቱ ባልሳሳት (በእኛ ግዜ ምደባ በጋዜጣ ይታወቅ ስለበር) ጥቅምት 18 ይመስለኛል ጋዜጣ ላይ ስሜን ያየሁት፡፡ ከዛ በፊት በነበሩት ተከታታ;ይ ሳምንታት በየቀኑ ስሜን ምዕራብ ሆቴል አጠገብ የነበረ ጋዜጣ አዙዋሪ ደንበኛዬ ጋር እየተመላለስኩ የማየው፡፡ ለጋዜጣ ማንበቢያ የምትሆነውን ሳንቲም ደግሞ አባቴ ይሰጠኝ ነበር፡፡ ለነገሩ ጋዜጣ አዙዋሪው፤ ቀደም ሲል አባቴ ይልከኝ ስለነበርና ፖሊስና እርምጃው የሚባለውን ጋዜጣ እየሄድኩ እገዛው ስለነበር አንዳንድ ቀን ሳንቲሙን አይቀበለኝም ነበር፡፡ እኔመ፣ ታዲያ ያቺን ሳንቲም አልተቀበለኝም ብዬ አልመልስም ነበር፡፡ ብቻ ያን ጊዜ፡፡

ከብዙ ጭንቀት ወዲያ ጥምቅምት 18 ቀን ወጣልኝና ስሜን በጋዜጣ አይሁት፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሚለው ውስጥ ዝርዝሬ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ብሎ አለሁበት፡፡ ስሜን በምን ፍጥነት እንዳየሁት አላውቅም፡፡ ግን አይሁት፡፡  በጣም ልዩ ስሜት ነበረው፡፡ ወላጅ አባቴን የት እንደደረሰኝ ለመንገር በየቀኑ ፈልጌ ግን ስላልወጣ አልነገረው ስለነበር፡፡ በውስጤ ምደባው አልፎኝ ይሆን እንዴ ብዬ መስጋቴ አልቀረም፡፡ ደርሼ ስመለስ አባቴ ይጠይቀኛል፡፡ አልወጣም የእኔ ብዬ እመልስለታለሁ፡፡ እንድጊህ ነገ ይወጣ ይሆናል ይለኛል፡፡ ይሆናላ እለዋለሁ፡፡ ስሜቴ እንዳይቀየር ያደርግ የነበረው ጥንቃቄ ዛሬም ድረስ ይገርመኛል፡፡ አባቴ በእርግጥም ልዩ ሰው ነበር፡፡ ሀይለኝነቱ ለእኔ ሲሆን አይሰራም ነበር፡፡ ብዙ ስሜቴ እንዲጎዳበት አይፈልግም ነበር፡፡ ስለሆነም ሁሌም ብርታቴ ነበር፡፡ የእናቴን ነገርማ አታንሱት፡፡ ስለእነርሱ ሌላ ጊዜ ብንጨዋወት ይሻላል፡፡

ብቻ እለቱ ደርሶ ስሜም ወጣ፡፡ ህዳር 27 መንቀሳቀሻ ቀን እንደሆነ ይናገራል ጋዜጣው፡፡ አስፈላጊ ያላቸውን ጉዳዮችም ያትታል፡፡ በጣም ምጥን ያለ አሪፍ ማስታወቂያ ነበር፡፡ ብርድልብስ፤ አንሶላ፤ የስፖርት ትጥ፤ ሌሎችም እንዲኖሩ ያዛል፡፡ ትራስ ግን እንዳት;ይዙ፤ ይትራስ ልብስ እንጂ ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡ (ለነገሩ ትራስ ይዞ የመጣም ነበር፡፡ የፍሬሽ ነገር)

ቤት ሄድኩ፡፡ እንደወጣ ተናገርኩኝ፡፡ ጎንደር እንደደረሰኝም ተናገርኩ፡፡ ይሄኔ ትንሽም ቢሆን ድንጋጤ በቤቱ ሰፈነ፡፡ ግን ግድ ነው፡፡ የሚ;ያስፈልጉ ነገሮች ተናገርኩ፡፡ በቃ፡፡ የጎንደር ልጅ ልሆን የቀረኝ ወር አካባቢ ነው፡፡ በመሀከሉ ግን ዩኒቨርሲቲው አዲስ ማስታወቂያ አወጣ፡፡ ወደ ታህሳስ 12 ተቀየረ፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ኮሜድያን ተስፋዬ ካሣ ያረፈበት ጊዜ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡  አንድ ሴት የኦሮምኛ ሙዚቀኛም ሙት አመት ታስቦ ይውል ነበር፡፡ እኒህ ክስተቶች ትውስ ይሉኛል፡፡
ጉዞ ጎንደር ታህሳስ 10 ቀን ሆነ፡፡ በዚሁ ዕለት ታዲያ መንገደኛ በመሆኔ አውቶብስ ተራ ከለሊቱ 11 ሰዓት ደርሻለሁ፡፡ መድረስ ብቻ አይደለም ነቃ ብያለሁም፡፡ ከት/ቤት ¹ደኞቼ ጋር ነኝ፡፡ እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ በመንገዱ ሁሉ ልናወራ፡፡ የእናቴንና የአባቴን የመጨረሻ ሽኝት አልረሳውም፡፡ ጉዞ ሆነ፡፡ በርካቶች ከወላጆቻቸው ጋር ሆነው ነበር፡፡ እኔና ¹ደኞቼ ግን ብቻችንን ነበርን፡፡ ስለሆነም ሄድን፡፡

ምሳ በላን፡፡ አሁንም ጉዞ፡፡ በነገራችሁ ላይ አባይ በረሃ ሁለት ሰዓት ወሰደብን፡፡ ተጠምዝዘን እዛው፡፡ ሄደን ሄደን እዛው፡፡ ምንም አይነቃነቅም፡፡ ከባድ ጉዞ፡፡ በእድሜም ልጅነት ስለነበረኝ ነገሮች ሁሉ ይገርሙኝ ነበር፡፡ ግራሞቴ ሳያበቃ ታዲያ ሌላ ግራሞት፡፡  መንገዱ ሰንሰለታማ ነው፡፡ ተራራ እና ገደሉን ማየት ከባድ ነው፡፡ ታንኮች በየቦታው አርጅተው ተጣመው ይታያሉ፡፡ የመኪናችን ረዳቶች (ሁለት ነበሩ) ማብራሪያ እየሰጡን ጉዞ ቀጥለናል፡፡ በውስጤ የቀሩ በርካታ ነገሮች ስላሉ በሌላ ጊዜ እንመለስበት ይሆናል፡፡ ነገር ግን የት ኖራ የሚባል ቦታ ያሉውን ሜዳማ መሬት አይቼ ጠየኩኝ፡፡ ሜካናይዝድ እርሻ እንደነበር ነገሩኝ፡፡ አሁንም ቢሆን ስል አሰብኩ፡፡ አሁን ያለበትን ሁኔታ አላውቅም፡፡ ነገር ግን በቅርቡ ወደ ጅግጅጋ ስሄድ፤ ከጅግጅጋ አልፎ ወደ ሶማሌ ላንድ ባለው መንገድ ላይ አውበሬ ይምትባል ቦታ እስከምደርስ ድረስ ያየሁትን ሜዳ አይቼ፤ ሜካናይዝድ እርሻን ስመኝ፤ የትኖራ ትዝ ብላኝ ነበር፡፡ ግሩም ነበር አቦ፡፡ ጎዞ ጎንደርን ጨርሰን ጎንደር ገብተና፡፡ ታህሳስ 11 ምሽት ላይ ጎንደር ገባን፡፡


በታሪኬ ለመጀመሪያ ጊዜ የሁለት ቀን ጎዞ ተጉዤ ጎንደር ገባሁ፡፡ ምሽት በመሆኑ፤ አብሮኝ የነበረው ወንድወሰን ለታ (ወንዴ) ማደሪያ እስኪፈልግ እቃ እንድጠብቅ ነግሮኝ ግለጋ ሄደ፡፡ ተመልሶ መጣ፡፡ አሁን ዕቃችንን ይዘን ወደ ማደሪያችን ልንሄድ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ መመስገን የሚገባቸው አካላት ነበሩ፡፡ ጉዞዋችን አድካሚ ቢሆንም፤ በወቅቱ የነበሩ ተማሪዎች እኛን ለመርዳት ያሳዩት ቁርጠኝነት ሀያል ነበር፡፡ ምስጋና ብቸራቸው ደስ ይለኛል፡፡ አደረጃጀቱ ምንም ይሁን ምን፤ እርዳታ ያስፈልገን ነበርና ተባብረውናል፡፡ እቃችንን ከማደሪያችን ካኖርን ወዲያ በወቅቱ ሞባይል ስላልነበረኝ በሰላም መድረሳችንን ለቤተሰብ አሳውቀን፡፡ ከዛም ጥቅልል ብለን ገብተን ተኛን፡፡ 

ሲነጋ ከነበረው ደግሞ እንቀጥላለን፡፡ የእዛ ሠው ይበለን፡፡

አብርሃም ተስፋዬ

ዓርብ 7 ማርች 2014

ኦቦ አለማየሁ አቶምሳ በተወለደ በ45 አመቱ አረፈ ስለተባለ!



‹‹ሲታመሙ መታከሚያ ገንዘብ እንኳ የሌላቸው እንደነ አለማየሁ አቶምሳ ያሉ ፖለቲከኞች አሉ›› የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ኦቦ አለማየሁ አቶምሳን አስመልክቶ ተናግረውት ነበር ተብሎ ሰሞኑን እየተነገረ ካለው የተወሰደ ነው፡፡

አንድ ሠው በተለይ እንደኛ አይነት ሀገር ላይ የስልጣን እርካብ ላይ ከወጣ በእርግጥም የሀብት መጠኑ እና የኩራት ጣሪው ገዘፍ እንደሚል ማሰብ አዳጋች አይመስልም፡፡ እንደው ለነገሩ አነሳሁት እንጂ፤ ሀገራዊና ክልላዊ ስልጣን ይቅርና የቢሮ ስልጣንም ስትኮፍሳቸው የምትከርም ግለሰቦች እናውቃለን፡፡ ይህንን ደግሞ ታዲያ በርካቶችን ሲያስከፋ ይስተዋላል፡፡ ኦቦ አለማየሁ ግን በዚህ ብዙም ሲታማ አልሰማሁም፡፡

ይልቁንም፤ ሙስናን ለመዋጋት የነበረውን ቁርጠኛ ፍላጎት ተከትሎ ሰዎች እንዳቄሙበት በሰፊው ይወራ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ዋጋ እንዳስከፈሉትና ይኸውም አሁን በተግባር የታየው የእርሱ ህልፈት የዚሁ ውጤት ስለመሆኑ በደንብ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ንግርቱ ታዲያ በተለይ ህልፈቱ ከተሰማበት ጊዜ ወዲህ በደንብ በርትቶ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡

ግለሰቦች ባሉበት ወቅት ማሞገስና ማመስገን የማይቀናን ለምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ግን ሁል ጊዜም ይገርመኛል፡፡ ሰዎች ሲያልፉ የምናጣው ነገር የሚታወሰን ያን ግዜ ነው መሠለኝ፤ ብዙ ነገር ማንሳት እንወዳለን፡፡  ሙት ላለመውቀስ ይሆን?
የኦቦ አለማየሁ ግን ይለያል፡፡ ስልጣን ላይ ወጣ፡፡ ሥራ ጀመረ፡፡ የተወሰኑ ታላላቅ ለውጦችን መከወን ጀመረ፡፡ ከዚያም ታመመ ተባለ፡፡ ህመሙ ደግሞ ከመመረዝ ጋር ተያያዘ፡፡ መመረዙ ደግሞ ስራ ካልተመቻቸው ግለሰቦች እንደሆነ በሰፊው ውስጥ ውስጡን ይነገር ነበር፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በደንብ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ግን በእርግጥ ከሆነ እውነት ለመናገር በጣም አሳዝኝም አሳፋሪም ነው፡፡ ሥራ ለምን ተሰራ በሚል እንዲህ ያለ ግፍ በአንድ ግለሰብ ላይ መሆኑም ያሳዝናል፡፡ ኦቦ አለማየሁ ለዚህ ካለፈም መስዋዕትነት ነው ብሎ መውሰድ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህንን መስዋዕትነት መክፈል ታላቅነት ነው ብዬም አምናለሁ፡፡ ስለሆነው ሁሉም ከማዘን ውጭ ምን ማድረግ ይቻል ይሆን፡፡

በሀገር ውስጥ ካሉት ባለስልጣናት ላይ የሚነሳው ሀሜት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በርካቶቹ በብዙ ነገር ይጠረጠራሉ፡፡ በርካቶችም ሲታሙ ሰምተናል፡፡ ኦቦ አለማየሁ አቶምሳ ግን በዚህ መልክ ስለመታማቱ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እንደውም በጣም በብርቱ ሲታዘንለት ይሰማል፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም መሞቱን ተከትሎም ቀደም ሲል በህመሙ ወቅት ሲወራ የነበረው ነገር ጎልቶ እየተሰማ ነው፡፡ 45 ዓመት እድሜው የተቀጨው ኦቦ አለማየሁ ከህመሙ ጋር እየታገለ ሀገሩንና ህዝቡን ለማገልገል የነበረው ቁርጠኝነት መልካም የሚባል እንደነበር እየሰማን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከአንድ ምርጥ መሪ የሚጠበቅ ነገር መሆኑን ለመገንዘብ ነብይነት አይተይቅም፡፡ ኦቦ አለማየሁ ማለፉ ሲነገር ከነበረው የህመም ስሜትና ስቃይ አንጻር ከታየ ከእርሱ በግል እረፍት ይመስለኛል፡፡ ሀገርና ህዝብ ግን እንዲህ ያለውን መልካም ሰው ማጣታቸው በእርግጥ ያስቆጫል፡፡ ግን እንዲህ ያለው ነገር እየተሰማ ዝም አይባልም፡፡

ስለሆነም መንግስት ( የክልሉም ይሁን ፌዴራል መንግስት) ስለነገሩ አንዳች አርግጠኛ ነገር ማጣራትና ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ይህ አካሄድ ለሌሎች ባለስልጣናትም አደገኛ ስለሚሆን፡፡ ስለሆነም ቢታሰብበት መልካም ይመስለኛል፡፡ አንድም ነገርየው ሌሎች ባለስልጣናት እንዲፈሩ ያደርጋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳች ነገር በውስጡ ስለሚኖር ተቀብሮ እንዲቀር ምክንያት መሆኑን መታዘብ ይቻላል፡፡ በመሆኑም ነው ታዲያ ጉዳዩ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ ቢሆን መልካም የሚሆነም፡፡ ባይሆን እንካ ለመገማገሚያነት መቅረብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ቢያንስ ወሬው በዚህ ልክ ለምን እንዲወራ እንደሚፈለግ መጣራት አለበት፡፡ መቼም ወሬው ዝም ብሎ ያለአንዳች ፍንጭ ሊወራ እንደማይችል በመጠርጠር ነው ይህንን ማለቴ፡፡ ቅያሜ እንደማይኖራችሁም በማሰብም ጭምር፡፡ (በእርግጠኝነት አትቀየሙኝም አይደል?)

ስለሆነም ኦቦ አለማየሁን ልለው ወደድኩ፡፡ ኦቦ አለማየሁ ሆይ በእርግጥም በዚህ ልክ ተወዶ ማለፍ መልካም ነው፡፡ ስለሰራሀቸው ስራዎች፤ ስለጥሩነት፤ ለጥሩ ነገርና ጥሩ ነገር ለመስራት ስለከፈልከው ዋጋ ሁሉ ክብር ይገባሀል፡፡ ነብስህን እግዚአብሔር በአጸደገነት ያኑራት፡፡ የምትወደው ህዝብህና ሀገርህም መልካሙን ሁሉ ይግጠማቸው፡፡
ሁነቱ ግን የፈጠረብኝ ስሜት ከባድ ነበር፡፡ ቀደም ሲል የኢህዴድ አመራር ለውጥ፤ የእርሱ በእራሱ ፈቃድ መልቀቂያ መጠየቁና መሠል ክዋኔዎች ሲገርሙኝ ሰንብተዋል፡፡ ታሪክ ሰሪው በእራሱ ፈቃድ መልቀቂያ ጠይቆ አረፈ፡፡ ለማንኛውም በእኔ አቅም ሊባል የሚችለውን ልበል መሠለኝ፡፡ በድጋሚ ነብስ ይማር፡፡ ለሶስቱ የስጋ ልጆችህ ለቤተሰብህና ለሌሎችም ሁሉ መጽናናትን ተመኘሁ፡፡



አብርሃም ተስፋዬ