ዓርብ 28 ማርች 2014

ዝምታሽ አልበዛም ኢትዮጵያዬ?


‹‹ሀገርን ፍለጋ››


<<የተገነቡትና በመገንባት ላይ ያሉት የመታሰቢያ ሐውልቶች የሠማዕታት ወይስ የቅሱፋን?>> በሚል በሠዓሊ አምሳሉ /ኪዳን አርጋው የተጻፈ የተባለውንና ዕንቁ መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር113 መጋቢት 2006 ..ን ዋቢ ያደረገውን የhttp://www.goolgule.com/monuments-for-martyrs-or-victims/ ጽሑፍ አነበብኩና ዝምታን ለመምረጥ አልወደድኩም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዬ እራስሽን ልጠይቅሽ ባክሽ?
መቼም ታሪክሽ መያዣ መጨበጫ ያጣ ይመስላል፡፡ ሁሉም ተነስቶ የሚጽፈው አይነት ሆኖልሻል፡፡ አንዳች እውነት ውስጡ ለማግኘት በደንብ መበርበር የሚፈልግ፤ አንደኛው የሚጽፈውን ሌላኛው በእርግጥም ድብን አድርጎ አሳማኝ በሆነ ሁኔታ የሚሽርበት አይነት ነው፡፡ ሀገሬ ግን በመሀከል ቤት ቁጭ ብለሽ ታሪክ አልባ እየሆንሽ ያለሽ መሰለኝ፡፡ በ‹‹አዋቂነት እርሾ›› ሰበብ ሁሉም እየተነሳ የሚጽፍብሽ አይነት ሆነሽ፤ ቀራጺውም፤ ሰዓሊውም፤ የታሪክ ምሩቁም፤ ፖለቲከኛውም፤ ለቀስተኛውም፤ አላቃሹም፤ ታሪክ ጸሐፊ ሆኖብሽ የተቸገርሽ መሰለኝ ሀገሬ፡፡ ሀገሬ ምናባቴ ላርግሽ? ምን ይሻልሽ ይሆን? እኔም ታዲያ ልጠይቅሻ፡፡ እንደእናት አንድ በይኝ፡፡ መልስ ስጪኝ እናት አለም፡፡

አንድነትን ሰበብ አድርገው ማንነትን የሚሞግቱ ‹‹አዋቂዎችሽ›› ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡ አሁንም የሚሉት ያላቸው መሰለኝ፡፡ እያሉም ነው፡፡ በመከባበርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ አንድነትሽን የሚናፍቁና ቢሆን የሚወዱ እንዳሉ የተረዱት ‹‹አዋቂዎችሽ›› እናትነትሽ ለእነርሱ እንጂ ለሌላው እንዳልሆነ እየመሰከሩልሽ ነው፡፡ ሌሎችስ ማን አላቸው ያላንቺ? ሀገሬ ይገርምሻል አዋቂ የሚባሉት ሰዎችሽ ለሽምግልናና ለማሳያ የምንጠቀምባቸው የነበሩ ግለሰቦች ነበሩ፡፡ ዘቀጡ፡፡ ለልጆችሽ እልህ እንጂ ታሪክና መሰንበቻውን የሚያቆይሽ ነገር አላስቀምጥልሽ ብለው ይኸው አሰቃዩን፡፡ ‹‹አዋቂዎችሽ›› ግን ምን ነካቸው?

ሀገሬ ግን እውነት ታውቂናለሽ? እኛ በእርግጥም በውስጥሽ አለን? ነው ወይስ ተሳስተሸ ይሆን ያኖርሽን? አሁን መቼም አንቺ ስለሆንሽ እንጂ ሌላ ሀገር ቢሆን እንዲህ ይዘቀጣል? ይግረምሽ ብሎ አንደኛው ሠዓሊሽ ‹‹የታሪክ ምሁር›› ነኝ ብሎ ነው መሰለኝ ለህትመት ያበቃውን አየሁልሽና ከፋኝ፡፡ ስለዚህም እነግርሻለሁ፡፡ ቢያቅርሽም ቅሉ ስሚኝ፡፡ ወደድሽም ጠላሽም ጊዜ ስጪኝ ሀገሬ፡፡
ሠዓሊው ሰውዬሽ የመታሰቢያ ሐውልቶችሽ ለማን እና ለምን እንደሚሰሩ (ጠበቅ ተደርጎ ይነበብ) በሚሞግትበት (ምናልባት በተለይ ለኦሮሞ ህዝብ ያለውን የወረደ የክብር ልክና ስሜት ያሳየበት ይመስላል) ጽሁፉ ሕወሓት/ኢህአዴግን ሀገር አጥፊ ነው እያለ፤ በትጥቅ ትግሉም ግዜ ያለፉትን ታጋዮች በህይወት ካሉት እንደማይለዩ፤ ኢህአዴግ ለወደፊቱም እያኖረ ያለው ነገር መልካም አይደለም ሲል ያክላል፡፡ በዚህ ጽሑፉ ግን የአንቺ አንድነት ያሳሰበው መስሎ ልጆችሽን (በተለይ የኦሮሞ ተወላጆችና ብሔሩን በአጠቃላይ) ሙልጭ አድርጎ ያንቺ እንዳልሆኑ አስረድቶልሻል፡፡ ልጅሽ ከሆነ ገስጪው ሀገሬ፡፡

ሰዓሊው ‹‹ታሪከኛ›› ልጅሽ መሳይ ገንጣይሽ ትምክህቱን አራግፎታል አልኩሽ፡፡ መቼም አይተሽዋል፡፡ ሰምተሽውማል ብዬ አስባለሁ፡፡ እውነቴን ነው ዝም አትበይው፡፡ ጥሩ ልጅሽ አልመሰለኝም፡፡ እውነት ሀገሬ፤ ይህ ነገር ጥሩ አይደለም፡፡ ምን እንዳለ ታውቂያለሽ ኢትዮጵያዬ? አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ በሚል ለጨፈጨፉት ዜጎችሽ መታሰቢያነት የሚቆም ሀውልት ተገቢነቱን ሞገተ፡፡ በተለይ በአርሲ ለተከወነው የቆመውን የአኖሌን ሀውልት ጉዳይ ሲያነሳ፤ ኦሮሞዎችን በጅምላ ታሪካቸውን የማያውቁ ብሎ ተሳለቀባቸው፡፡ ምን ያለው ነው ታዲያ ይሄ ሀገሬ? ንገሪኝ ግድ የለሽም፡፡ እኔ እንደሁ ልጅሽ ነኝ፡፡ ግዴለም ንገሪኝ፡፡ ስለአንቺ አንድነት የሚዘምሩ መስለው መርዛቸውን የሚረጩብሽ በዙ እኮ፡፡ ሀገሬ ዝም አትበይ እንጂ፡፡ ምን ነክቶሻል፡፡ ግዴለም ያልለመደብሽን ዝምታ ከየት አመጣሽው? ቁጣሽ የት ሄደ እናትአለም? ሀገሬ ግድ የለሽም በርትተሽ ተቆጪ፡፡ ወኔሽን ሰለቡት እንዴ? አለን ብለው፤ መስለው አስኮረፉሽ እንዴ?

ሠዐሊው ልጅሽ ነኝ ባይ ‹‹ይታያችሁ ኢትዮጵያ አንድ እንዳትሆን ሲታገሉ ተገቢ እርምጃ የተወሰደባቸው የሀገር ጠላቶች፤ የአንድነት እንቅፋቶች ሆነው እያለ መስዋዕትንት የከፈሉ ይሉዋቸዋል›› ብሎ በግፍ የተጨፈጨፉ ዜጎችሽ ላይ ተሳለቀ፡፡ አንድነትሽ ሲናድ በወቅቱ ለመመለስ የተደረገ ነው ብሎ የሚያምነውን ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ተገቢ ነው ይልሻል፡፡ ቤታችን፣ መኩሪያችን ብለው በእናት መስለው የሚኖሩትን ብሔር ብሔረሰቦችሽን ‹‹ጎጦች›› አላቸው፡፡ ዜጎች ዛሬ ላይ ላሉበት ነገር ዋጋ የከፈሉላቸውን ወንድም እህቶቻቸውን ለማሰብ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ፤ ብሎም የመታሰቢያ ሐውልቶችን መስራታቸውን ሁሉ ‹‹አጥፊ›› ነው ብሎ ፈረጀልሽ፡፡ የእርሱን ስድብና ፉከራ ግን ‹‹ምርቃት›› ነው ሊልሽ ይሆን? እንደሁ ጠይቂልኝ፡፡ እባክሽ ሀገሬ ግድ የለሽም ጠይቂው፡፡

ሀገሬ መቼም አንቺ እንደ ልጅሽ ነይ ባዩ ሠዐሊ ልጆችሽ ታሪካቸውን የሚስቱ/የማያውቁ አይመስልሽም አይደል? እርሱን እርግጠኛ ነኝ፡፡ እንደው ይህ ሠዐሊ ሲስልሽ ባየሁት፡፡ እውነት ግን ሠዐሊ ነው ኢትዮጵያዬ? ግዴለሽም በደንብ አጣሪ፡፡ በአንቺ የዋህነት አይሆንም፡፡ ሠውየው ሌላ አጀንዳ ያለው ይመስላል፡፡ ታሪክን የ‹‹ፈጠራ ወሬ›› ነው ብሎ ይሞግታል፡፡ ፈጠራ ማለት ምንድነው እናት አለም? ሥዕል ሊፈጠር ይችላል፡፡ ታሪክ ግን እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል? ሰውየውን አስረጂልኝማ፡፡ ግዴለም ሠውየው አንዳች ነገር ሆኖ ይሆናል፡፡

ጭራሽ ብሎ ብሎ ኢትዮጵያዬ፤ ኦሮሞ ልጆችሽን ኢትዮጵያዊያን አይደላችሁ ብሎዋቸው አረፈ፡፡ እንግድነታቸውን ነገራቸው፡፡ አይገርምሽም ስላንቺ አንድነት የሚያስብ የሚመስለው ሠዐሊ አንቺን አንድ እንደሆንሽ ሲደሰኩር አርፍዶ ልጆችሽን ግን ያንቺ እንዳልሆኑ ነገራቸው፡፡ ‹‹ታዲያ ሀገራቸው የት ነው?›› ብለሽ ጠይቂው በሞቴ፡፡ እናት አለም እባክሽ ጠይቂው፡፡ በእኔ ሞት ይሁንብሽ ጠይቂው፡፡ ምን እንዳለ ልንገርሽማ ‹‹የኦሮሞ ህዝብ እነዚህን የልብ ወለድ ገጸባህሪያትንና ዓላማቸውን ምሳሌ አርአያ አንዲያደርጉ የሚወተውቱ የኦሮሞን ህዝብ ሊያሳስቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለውን አንድነትና ዝምድና ሊያራርቁ ሊሸረሽሩ፣ ሊያሻክሩ የሚችሉ መርዘኛ የፈጠራ ወሬዎች የሚሰበክበት የጥፋት ማዕከል እንደሚያደርገው በቀላሉ መገመት ይቻላል›› ይላል ስለ አኖሌ ሀውልትና ሙዚየሙ ሲያወሳ፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ያለው አንድነት ነው ልዩነት? ሀገሬ ግዴለም ጠይቂው፡፡ አትፍሪ እናት አለም ብቻ ጠይቀሽው ይውጣልሽ፡፡ ምን ይልሽ ይሆን እንስማው፡፡ ቀጠለና ምን ደግሞ አለ አትይኝም? እርሱ መች ትቶት ኢትዮጵያዬ ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ብዙ ባለአእምሮ ዜጎች ያሉት አስተዋይ የሕዝባችን አካል ነው›› አይል መሰለሽ? ገራሚ ነው፡፡
የኦሮሞን ህዝብ እንግድነት በግልጽ አስፍሮልሻል፡፡ ኢትዮጵያዬ መቼም እንዲህ ታሪክ አልባ የሚያረጉሽን ሠዐሊውንና መሰሎቻቸውን ምን ትያቸው ይሆን? ‹‹ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ባለው የሀገራችን ታሪክ ግን የሌሎቹ ብሔረሰቦች በሀገሪቱ መኖር በአንድም በሌላም አጋጣሚዎች ተጠቅሶ ሲገኝ የኦሮሞዎቹ ግን ጨርሶ የለም›› ይልሻል፡፡ እውነት እነርሱ ብቻ ነበር ያልነበሩት? ጨርሶ ደግሞ ሲያስረግጥልሽ ምን ቢልሽ ጥሩ ነው? ‹‹ይህም የሆነበት ምክንያት በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው በሀገሪቱ ስላልነበሩ ነው፡፡ የግራኝ ወረራ በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ከገቡ በላ ግን በሀገሪቱ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ ሚና ለመጫወት ሲበቁ እንደእንግድነታቸው አልነበረም›› ብሎሽ እርፍ፡፡ አክሎም ተሳትፎ ለማድረግ ፈጣን እንደነበሩ አትቶልሻል፡፡

ተመልሶ ደግሞ አንዳንዶች (በእርሱ አገላለጽ የጥፋት ኃይሎች) ኦሮሚያን እንገነጥላለን፤ ነጻ መንግስት እንመሰርታለን ገለመሌ ሲሉ የቅርብ ግዜ እንግዶች እንደሆኑ ማስታወስ ይኖርበት እንደሁ ይጠይቅማል፡፡ የማንን ሀገር እንደሚገነጥሉም ግራ የገባው መስሎ ይጠይቃል፡፡ ሀገር አልባ ናቸው እንዴ ልጆችሽ? እሰኪ ንገሪያቸው ባክሽ፡፡ ሀገራችሁ አይለሁም ካልሽም፤ የት እንደሁ መሆን የሚገባቸው አሳይያቸው ባክሽ፡፡ ምክንያቱም ልጅሽ ነኝ ባዩ ሠዐሊ ‹‹ኢትዮጵያዊ አይደለንም ካሉ ሀገሪቱን ለቀው ወደመጡበት የመመለስ መብታቸው የተጠበቀ ነው›› ብሎ አዋጅ ነግሮልሻል፡፡ በነገርሽ ላይ ኢትዮጵያዬ እርሱ ግን አዋጅ ነጋሪና ነጋሪት ጎሳሚ ያደረገው ማነው? ሹመት ሰጥተሽው ነው ወይስ? ግዴለም ግን ልጆችሽ ይከፉብሻል፡፡ መከፋታቸው ደግሞ ጥልቅ ይሆን ይመስለኛል፡፡ ይህንን ብሎ ያበቃ መሰለሽ? ‹‹አጼ ምኒልክ አደረጉ የተባለውን ሁሉ እውነት አድርገውት ቢሆን እን£ ልክ ነበሩ›› ብሎ እርፍ፡፡ ሀገሬ የልጆችሽ ጡት ሲቆረጥ አያምሽም እንዴ? እናት አለም ለምን ዝም ትያለሽ? ተናገሪ እንጂ እንዴት በልጆችሽ ቁስል ሲቀለድ ዝም ትያለሽ?

ሰውየው ሀሳቡ ምን እንደሁ እንጃ፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር ልጠቁምሽ እወዳለሁ፡፡ ካንቺ ባላቅ ሀገሬ፤ አንድነትሽን እየሰበኩ ልዩነትሽን የሚያሰፉ ልጆች ነን ባዮች እየበዙልሽም እየበዙብሽም ነው፡፡ አንድ ብትያቸው መልካም ይመስለኛል፡፡ ኦሮሞ ልጆችሽ ‹‹በሌለና ባልነበረ ቅዠትና የተረት ተረት ታሪክ እየፈጠሩ›› እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ግድየለም ሀገሬ ዝምታሽ እውነት ለመናገር ደስ አላለኝም፡፡
ታዲያ ሠዐሊው ሰውዬ ‹‹ከዘመን በፊት ኢትዮጵያዊ ያላቸው ሆኖ ለመገኘት ያላቸውን ቅን ፍላጎት ብናደንቅም ማንነት ባልነበረና በሌለ ታሪክ ላይ አይመሰረትምና እናዝናለን›› ብሎ አረፈው፡፡ አሁን አማረ አለ የሀገሬ ሰው፡፡ ምን ማለት ነው ታዲያ ኢትዮጵያዬ? ግዴለሽም ሠውየው ሌሎችን ይላል እንጂ እርሱ እራሱ ከእውቅ የሥነ-ልቦና ሐኪሞችሽ በአንዱ መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ እኔ አልድገመው እንጂ ሰውየው ብዙ ስድብም ተሳድቦ ነበር፡፡ ለነገሩ እዛው ታይዋለሽ፡፡ ‹‹የጨለማ እድሜ ጸሐይ እስክትወጣ ድረስ ነው›› ብሎ ዛቻ ቢጤም አስፍሮዋል፡፡ ማን እንደሁ እንጃ፡፡ እንደፍቅር ሠባኪም ያደርገዋል፡፡ እንዴት ነው ግን እናት አለም በስምሽ የሚነገደው? አስበሽዋል አንድነትሽን በማሳበብ እንዴት እንደሚዘባበቱብሽ? አይተሽ ዝም አትበያቸው ባክሽ፡፡ የደም እንባ የሚያነቡ መኖራቸውንም ተናግሮዋል፡፡ ነገ የእርሱና የመሰለቹ መሆኑን ይናገራል፡፡

ሲደመድም ደግሞ መድኃኔአለም ልቡና ይስጣችሁ ብሎ ነበር፡፡ ልቡና ተሰጥቶት የጻፈ ነው የሚመስለው፡፡ ግን ይመስልሻል ሀገሬ? እውነት ልቡና ያለው ሠው እንዲህ ይጽፋል? ዘላለማዊ ክብር እንደሻማ ቀልጠው ይህቺን ሀገር (አንቺን ማለቱ እኮ ነው፡፡ ድንቄም) ከነጻነትሽ ጋር ላቆዩ ለአርበኞቹ እናት አባቶቻችን ይሁን ይላል፡፡ ይህኛው አገላለጽ ከልብ ቢሆን ደግ ሀሳብ ነበር፡፡ ነገር ግን አይመስልም፡፡ ሰውየው ምን እንደነካው እንጃ፤ ብዙ ዘላበደ፡፡
ሀገሬ ልጅሽ መሆኑን፤ ካንቺ አብራክ መውጣቱን ተጠራጠርኩ፡፡ አንድነትሽን የሚፈትነው እራሱ እያለ፤ ሌሎችን አስታኮ የልቡን ነገረሽ እኮ፡፡ እርሱ እንደሻማ ቀለጡ የሚላቸው እነማንን እንደሆነ አልነገረንም፡፡ እውነት እውነት ግን ሀገሬ፤ እኔ ደስ አላለኝም፡፡ ለምን እንደሆነ መቼም ይገባሻል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይህንን በማለቱ አልተደሰትሽም፡፡

እኔ የሚገርመኝ ባንቺ አንድነት ላይ የሚከራከሩት ሰዎች ሌሎችን ማሰብ አይፈልጉም፡፡ አንድነትሽን የሚመኙና የሚያስቡት እነርሱ ብቻ እንደሆኑ ያስቡና ሌላውን ከጨዋታው ውጪ ያደርጉታል፡፡ ፓርቲዎችሽም ቢሆኑ እንዲሁ ይመስሉኛል፡፡ በስመ ተቃዋሚ ከያሉበት ይጠራሩና ስለአንድነትሽ የሚዘምሩ መስለው ልዩነትሽን የሚያፈካ መነጽር ያጠልቁልናል፡፡ ለምን እንዲህ እንድናስብ እንደሚወዱ አላውቅም፡፡ ግን በቃ እንዲህ ናቸው፡፡

አሁን አሁን ደግሞ አዋቂ ነን ባዮችሽ፤ ህዝብሽን የሚከፍል፤ የሚሰነጥቅና የጎሪጥ የሚያተያይ ሀሳብ ያራምዱ ይዘዋል፡፡ እኔ ግን ዝምታሽን እሞግታለሁ፡፡ ለምን ዝም ትያቸዋለሽ? ግድየለም ንገሪያቸው ስለልጆችሽ፡፡ እንግድነት የመጣህ ነህ፤ ቤተኛው እኔ ነኝ እየተባባሉ የሚዛለቁ ይመስልሻል? ግዴለም ሀገሬ አንድ ነገር አድርጊ እንጂ? ዝምታሽን ልሞግተው እማ፡፡

ክፉሽ መቼም ቢሆን አይመረጥም፡፡ ልጆችሽም መልካም ቢሆኑልሽ እመርጣለሁ፡፡ አሁን ግን መከፋቴ ባሰ መሰለኝ፡፡ ስላንቺ ያወሩ የመሰሉኝ ሰዎች ሁሉ ያሳምሙኛል፡፡ ከ80 በላይ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንዳሉ ንገሪያቸውማ፡፡ እኒህ ህዝቦች ተዋልደው እየኖሩ እንደሆነ ንገሪልኝማ፡፡ አይሆንም ካሉሽ ግን ሌላ ነገር እንዳይሆንብሽ እሰጋለሁ፡፡ መከፋትሽን እገምታለሁ፡፡ ለመኖር ግን እራስን መፈለግ ግድ የሚልበት ሁኔታ እንዳለ አለማውቅ፤ ልጆችሽ በእርሱ ተጠምደው እራሳቸውን ሲፈልጉ፤ አንድነትሽን የሰበኩ እየመሰላቸው ልጆቼ ብለሽ የምትናገሪላቸውን የሚያስቀይሙብሽን አንድ ካላልሽ ራስን በመፈለግ ውስጥ አንቺን እንዳያጡሽ እፈራለሁ፡፡ ታሪክ አዋቂ ነን ተብሎ የሚደሰኮረው፤ እሳት ሆኖ እንዳይበላሽ እፈራለሁ፡፡ ግን እኔ እልሻለሁ፤ ፖለቲካዊ ምልከታው የቱንም ያህል ይሁን ስፋቱ፤ አንቺነትሽን ለጥርጥር የሚዳርጉ የበረከቱ አዋቂዎችሽ ግን ብቅ ብለዋል፡፡ ትልልቅ ተብዬዎቹም ሆኑ ትንንሾቹ አዋቂዎችሽ ልብ ያሉት ያልመሰለኝ ነገር አለ፡፡ ሀገሬ በይ እንግዲህ ዝም አትበይ....ግድ የለም ዝም አትበይ.....እንደውም በዚህ ሙቀት ውስጥ ሀገርን ፍለጋ መሄድ ምኑ ላይ ይሆን ክፋቱ? ምክንያቱም ኢትዮጵያዬ አንደኛው ገጣሚ ልጅሽ እንዳለው፤
‹‹ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ
ሀገር ውስብስብ ነው ውሉ››
እኔ ግን እልሻለሁ ዝምታሽ የበዛ መሠለኝ፡፡ ቸር ያቆይሽ፡፡ እኔም ቸር መሆን ምኞቴ ነው፡፡ ስለሆነም ደህና ይግጠምሽ፡፡



አብርሃም ተስፋዬ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ