ሀገራችን እስካሁን በመጣችባቸው
ሂደቶች በርካታ ውጣ ውረዶችን ማስተናገዷ እሙን ነው፡፡ በእነዚህ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህልና ወግ ብሎም
የተጻፈም ይሁን ያልተጻፈ ‹ህግ› በወቅቱ በነበሩ መሪዎች ወይንም ገዢዎች እየተሰናዱ አንድም ለእነዚሁ ግለሰቦችና ስርዓታቸው ማቆያ
የተሰናዱ፤ አንዳንድ ጊዜም የህዝቡን ስነልቦና ባህልና ወግ ብሎም እምነት የተከተሉ፤ በሌላ ጊዜም ደግሞ ከህዝቡ ስነልቦናና እምነት
ወግና ልማድ በወጡ አኳኸን ያሰናዷቸው ቢመስሉም፤ የህዝቡን በአንድ አቅጣጫ (ካለው የራሱ እምነትና ህሊናዊ ፍርድ ባሻገር) ለመምራት
አልያም ለመግዛት ሲጠቀሙባቸው እንደነበር ታሪክ ያወሳል፡፡
ሰው የማክበርን ባህል ኢትዮጵያዊ
(በሌሎች ሀገሮች የለም እያልኩ እንዳልሆነ ልብ ይሏል) በመሆን ብቻ የወረስነው፤ ሲወርድ ሲዋርድ የመጣ ልማድና ሰው የመሆን እውነተኛ
ማሳያ ከመሆኑም በላይ ከዕምነትም አንጻር ሲስተዋል ከፈጣሪ ትዕዛዛት መካከል አንዱ ነውና በሀገሬ በርከት ያሉ ሰዎች ሰውን በማክበር
ሲያምኑ ለማስተዋል ቀላል ሆኖ ይታያል፡፡ በየትኛውም የእምነት አስተምርሆዎችም ይኸው ተደጋግሞ እንደእምነት ህግጋት ትኩረት ተሰጥቶት
ሲሰበክ ይሰማል፡፡
በህግ የመዳኘቱ ነገር እንደተጠበቀ
ሆኖ፤ ህዝቡ ባለበት አካባቢና ከየብሔሩ ባህላዊ ልማድ አንጻር ሲስተዋል ከተለያዩ እውነቶች ጋር ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ
ህዝቡን ባማከለ ስነልቦናዊ ልኬት የሚራመድ፤ ህግና ስርዓትን ለማክበር የመንግስትን ወይም የአስተዳዳሪዎችን መልካም ፈቃድ የማይሻ
ስነምግባራዊና አእምሮዋዊ ብሎም ልቦናን ባገናዘበ መጠን ተቀባይነት የነበራቸው በርካታ እውነቶች ይስተዋሉበት የነበረ ማህበረሰብ
እንደነበር ለማወቅ ቀደም ያሉ ጽሁፎችንና ታላላቆች እና ወላጆችን ጠይቆ መረዳት ይቻላል፡፡
ሀገር ከድንጋይ ቁልል ባሻገር፤
ከሲሚንቶ ግግር ወዲያ፤ ከቴክኖሎጂ ምጥቀት በላይ፤ ከፖለቲካዊ አንድምታና እወደድ ባዮች ገቢር የሌለው ቀረርቶ ባሻገር፤ ለግብሩ
አጋዥ የሆኑ ቀደም ሲሉ የነበሩንና አሁንም ጨርሰው ያልጠፉትን የህገልቦና ብሎም የግብረገብ አስተምርሆዎች እንደሚያስፈልጓት ለመረዳት
አሁን በየአካባቢው እየተከሰተ ያለውን ሁነት ተከትሎ እየሆነ ያለውን ነገር በማየት መረዳት ቀላል ሆኖ ይታየኛል፡፡
በነገራችን ላይ የህግን ጉዳይ በተመለከተ
ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም በአንድ ጽሁፋቸው ያነሱትን ነገር እዚህ ለመጠቀም ልሞክርማ፤
‹‹ በየትኛውም ጥንታውያን አገሮች እንደነበረው ሁሉ በኢትዮጵያም በሕግ ከለላ የተሰጣቸው፣ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ በደል ያደረሱ እንደ ባሪያ ንግድና እንደ ባለርስትና ጭሰኛ የመሳሰሉ አጸያፊ ሥርዓቶችና ሕጋዊ ግንኙነቶች እንደነበሩ አይካድም። ይህም ሆኖ ግን ጥንታውያን ሕጎች፣ የኃይማኖት ድንጋጌዎችና ባህላዊ ሕጎች መኖርና በሥራ ላይ መዋል በጥቅሉ በሀገራችን ፍትሃዊነት በህዝብ አዕምሮ እንዲሰርጽ አድርገዋል። ህዝቡ ለሕግ ከበሬታ እንዲኖረውና ግፍና በደልን እንዲጠላ፣ በጠቅላላው ፍትሃዊነት እንደ አንድ ብርቅዬ ዕሴት እንዲቆጠር በህዝብ እምነት ውስጥ ተቀርጿል።
ህዝቡ ለሕግ ከፍተኛ ከበሬታ እንደነበረው የሚገልጹ አያሌ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ሁለት ባላጋራዎች መንገድ ላይ ቢገናኙ ተበደልኩ ባዩ ምንም ኃይል ሳይጠቀም “በሕግ አምላክ ቁም!” በማለት ብቻ ባላጋራውን አስቁሞ የነጠላዎቻቸውን ጫፍ ቋጥረው (ተቆራኝተው) ያለ ፖሊስ አጃቢ ወደ መረጡት ዳኛ ዘንድ ሄደው ፍርዳቸውን ይቀበሉ ነበር። ለዚህም ነው እስከዛሬ “በቆረጥከው ዱላ ብትመታ፣ በመረጥከው ዳኛ ብትረታ” እንዲቆጭህ አይገባም የሚባለው። “በሕግ አምላክ!” ሲባል ውሃ እንኳን ይቆማል ይባል ነበር።››
አሁን አሁን ግን በተለይም
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ ያለው የደቦ ፍርድ ምናልባትም ከላይ ከጠቃቀስናቸው ኢትዮጵያዊ ዕሴቶች ወጣ ያሉ ብሎም የህዝቡን
መልካም ስነልቦና የማይወክሉ ሆነው ይታያሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን፤ እንዲህ ያሉ ሁነቶችን በአደባባይ ማውገዝም ሆነ፤ ጉዳዩ
በሚፈጸምባቸው ቦታዎች ላይ ማህበረሰቡ ‹ተው/ተይ/ተዉ› የሚል ‹ከልካይ› መጥፋቱ ምን ይባል እንደሁ ለእኔ ግራ ነው፡፡
በሀገራችን ካለው በርካታ
‹ሐፍረት› መካከል ቀደም ሲልም ይደረግ እንደነበረው፤ አሁንም ከዶ/ር ያዕቆብ ጽሁፍ እንደጠቀስኩት ጥፋት ተሰርቶ እንደሁ እንኳ
‹በሕግ አምላክ› የሚለው ቃል ክብር ነበረው፡፡ ይህ እንግዲህ ህግና ስርዓት ምን ያህል ቦታ ይሰጣቸውን እንደነበር ማሳያ
ነው፡፡
እንዲሁ በተለምዶም ቢሆን፤ እናቱ ‹በጡቴ› ብላ የልመና ጥሪዋን በምታሰማበት ወቅት
የሚኖረውን የልጅ ስሜት መቀዝቀዝ ብሎም ከእናት መስመር ያለመውጣት ሁናቴ፤ በሌላም ሁኔታ ‹ስለባንዲራው› የሚል ምልጃና ልመና
የነበረበት ሀገር መሆኑን፤ የእናቶች ነጠላ ዘርግቶ ሰው የመገላገልና የመሸምገል፤ የመዳኘት ሁነቶች ከተወሰኑ አመታት ወዲህ
ሲስተዋሉ አይታይም፡፡ ወግና ልማድን በአንድ በኩል፤ ስልጣኔን በሌላ በኩል ማስታረቅ አቅቶን እንደህዝብ አንዳች አዙሪት ውስጥ
ገብተን ስንቃትት ይታያል፡፡
ይህም እንደሀገር
ሐፍረታችንን ጥለን በሌላ አቅጣጫ እየተጓዝን ስለመሆኑ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ከሕግ አንጻር ሊታዩ የሚገባቸውን ጉዳዮች ሁሉም
በየፊናው ፍርድ መስጠት ከጀመረ ግን፤ ዛሬም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሌላ አስጸያፊ፤ ሌላ ደግሞ ወደፊት አንዳች ጥግ ይዞ
እነዚህን ዛሬ የተከወኑ ጉዳዮች እያነሳ ‹መጥፎ› ታሪክ ሊጽፍ እንዲችል እንዳይሆን ያስፈራል፡፡
በተለይም እንዲህ ያሉ
የደቦ ፍርዶች ድግግሞሽ ማህበረሰቡንም እንደህዝብ፤ ኢትዮጵያንም እንደሀገር የታመነ መንግስታዊ ስርዓት፤ ብሎም በየደረጃው ያሉ
የፍትህ አካላትን መኖር እንድናጠይቅ ያደርገናል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያሉ ተግባራት በማህበረሰቡ ውስጥ በተደጋጋሚ ሊታዩ
የሚችሉት፤ ህዝቡ በመንግስት ተቋማት ላይ ያለው እምነት በሚሸረሸርበት፤ ወይንም ወደህግ በመሄዱ የሚፈልገውን ፍትሐዊነት
እንሚያጣጥምና በእስካሁኑ ቆይታው ያስተናገዳቸውን እውነቶች በማካተት ሊሆን እንደሚችል ስለደቦ ፍርድ የተጻፉ ጥናታዊ ጽሁፎች
ያስረዳሉ፡፡
ይሁንና በማናቸውም መለኪያ
እንዲያሉ የደቦ ፍርዶች ሰብዓዊነት የሚያራክሱ፤ የመኖርን ትርጉም የሚያሳንሱና በማናቸውም ሁኔታ በየትኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ላይ
ሊከወኑ የማይገባቸው እንደሆኑ በርካታች ይስማማሉ፡፡